ማይናማር፡ አብራሪው አውሮፕላኑን ያለ ፊት ጎማው አሳርፎታል

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በማይናማር የፊት ጎማዎች የመዘርጋት ችግር ያጋጠመውን አውሮፕላን ያለ ፊት ጎማው በሠላም እንዲያርፍ የያደረገው አብራሪ አድናቆት እየተቸረው ነው።
ባለቤትነቱ የማይናማር ብሔራዊ አየር መንገድ የሆነው አውሮፕላኑ በማንዳላይ አየር ማረፊያ ችግር ካጋጠመው በኋላ በማኮብኮቢያው መም ላይ በዝግታ ነበር ያረፈው።
የዚህ ኢምብሬር 190 የተሰኘው አውሮፕላን አብራሪ፤ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ 89 ተሳፋሪዎች አንዳችም ጉዳት ሳያጋጥማቸው አውሮፕላኑን በሠላም በማሳረፉ አድናቆት ተችሮታል።
ከያንጎን የተነሳው ይህ አውሮፕላን ወደ ማንዳላይ መቃረቢያ ሲደርስ ነበር የአውሮፕላኑ የፊት ጎማዎች አልዘረጋም ያሉት። በዚህ ጊዜ ታዲያ አብራሪው እያንዳንዱን የአደጋ ጊዜ ጥንቃቄዎችን የወሰደ ሲሆን የአውሮፕላኑን ክብደት ለመቀነስም ብዙ ነዳጅ እንዳቃጠለ አየር መንገዱ አስታውቋል።
አብራሪው ምያት ሞ ኡንግ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎቹ የሚያርፍበትን ቦታ እስከሚወስኑለት ድረስም አየር ማረፊያውን ሁለት ጊዜ ዞሮታል ሲል አየር መንገዱ አክሏል።
አውሮፕላኑ ሲያርፍ የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስል አውሮፕላኑ አፍንጫው መሬት እስከሚነካ ድረስ በኋላ ጎማው ነበር ያረፈው። አውሮፕላኑም እስከሚቆም ድረስ ለ25 ሰከንዶች በመሬት ላይ በቀስታ ተንሸራቷል።
የማይናማር የትራንስፖርት ሚንስትር ዊነ ሃንት ለሮይተርስ የዜና ወኪል " አብራሪው በጣም ትልቅ ሥራ ነው የሠራው " ሲሉ አሞካሽተውታል።
በማይናማር በዚህ ሳምንት ብቻ እንዲህ ዓይነት ችግር ሲያጋጥም ለሁለተኛ ጊዜ ነው ተብሏል።
ባለፈው ረቡዕ ቢማን የባንግላዲሽ አየር መንገድ አውሮፕላን ባጋጠመው መጥፎ የአየር ሁኔታ በያንጎነ አውሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ በሚሞክርበት ጊዜ ማኮብኮቢያ መሙን ስቶ ተንሸራቶ ነበር። በአደጋውም በትንሹ 17 ሰዎች መጎዳታቸው ይታወሳል።
















