በሞስኮ አውሮፕላን ተከስክሶ የሰው ሕይወት ጠፋ

ከአውሮፕላኑ በእሳት ከተያያዘ በኋላ

የፎቶው ባለመብት, REUTERS/Nadezhda Polomoshnova

በሞስኮ አንድ የመንገደኞች አውሮፕላን የቴክኒክ ችግር ገጥሞት በረራውን አቋርጦ እንዲያርፍ ከተደረገ በኋላ በእሳት ተያይዞ 41 ሰዎች መሞታቸው ተሰማ።

ይህ የሆነው በሞስኮ ሼሬሜትይቮ አየር ማረፊያ ሲሆን አውሮፕላኑም ኤሮፍሎት የተሰኘ ኤር መንገድ ነው ተብሏል።

በማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን ላይ እየተዘዋወረ ያለ ተንቀሳቃሽ ምስል እንደሚያሳየው መንገደኞች በእሳት ከሚንቀለቀለው አውሮፕላን ለማምለጥ የአደጋ ጊዜ መውጫ በሮችን ሲጠቀሙ ይታያል።

በአደጋው ከሞቱት መካከል ሁለት ሕፃናት እና አንድ የበረራ አስተናጋጅ እንደሚገኙበት የራሺያ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

አውሮፕላኑ 73 መንገደኞችን እና አምስት የአውሮፕላኑን ባልደረቦች አሳፍሮ ነበር።

አንድ የአይን ምስክር እንደተናገረው ከአውሮፕላኑ በሕይወት ሰዎች መውጣታቸውን "ተአምር" ብሎታል።

"37 ሰዎች ከአደጋው ተርፈዋል፤ ከእነዚህ መካከል 33ቱ መንገደኞች ሲሆኑ አራቱ የአየር መንገዱ ሠራተኞች ናቸው።" ብለዋል የአደጋውን መንስዔ እየመረመሩ ያሉት ባለሙያ።

አምስት ሰዎች በሆስፒታል ተኝተው የሕክምና ክትትል እያገኙ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።

አውሮፕላኑ በረራ በጀመረ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የቴክኒክ ችግር ስላጋጠመው ተመልሶ ለማረፍ ተገድዷል። ነገር ግን ተመልሶ ለማረፍ እየተንደረደረ ሳለ ሞተሩ በእሳት መያያዙን አየር መንገዱ በመግለጫው ላይ ተናግሯል።

መግለጫው አክሎም የአውሮፕላኑ አብራሪዎች የተሳፋሪዎችን ደህንነት ለማረጋገጥ የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል ይላል። "መንገደኞቹ በ55 ሰከንድ ውስጥ አውሮፕላኑን ለቅቀው እንዲወጡ አድርገዋል" ሲል በመጥቀስ።