በኬንያ አንድ የፖሊስ አባል ሚስቱን ጨምሮ ስድስት ሰዎችን ተኩሶ ገደለ

የኬንያ ፖሊስ አባል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዛሬ ማክሰኞ ጠዋት አንድ የኬንያ ፖሊስ አባል ለጥበቃ በተሰጠው ክላሺንኮቭ ጠብመንጃ ባለቤቱን ጨምሮ ስድስት ሰዎችን ተኩሶ መግደሉ ተገለጸ።

የፖሊስ ሪፖርት እንደሚያሳየው ከፖሊስ አባሉ መኖሪያ ቤት አቀረቢያ የሚኖር አንድ ሰው ከፖሊሱ መኖሪያ ቤት ከባድ የተኩስ ድምጽ ሰምቷል።

በመዲናዋ ናይሮቢ ካቤቴ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚኖረው ይህ የፖሊስ አባል ባለቤቱን ተኩሶ ከገደለ በኋላ ሌሎች ተጨማሪ አምስት ሰዎችን ገድሏል።

ከትንሽ ቆይታ በኋላ ደግሞ የፖሊስ አባሉ የራሱን ሕይወት እንዳጠፋ የፖሊስ መግለጫ አመልክቷል።

የፖሊስ አባሉ ባለቤቱን ጨምሮ አምስቱን ሰዎች ለምን እንደገደለ እስካሁን በግልጽ ያልታወቀ ሲሆን ፖሊስ ግን በጥንዶቹ መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር ብሏል።

"ጥንዶቹ ከዚህ ቀደም የማይስማሙባቸው ጉዳዮች ነበሩ። አንዳንዴም ይጣሉ ነበር'' ሲሉ የፖሊስ ኃላፊው ፍራንሲስ ዋሆሜ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

ኮንስታብል ቤንሰን ኢምባሲ የተባለው የፖሊስ አባል ባለቤቱን ከገደለ በኋላ በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች ላይ ተኩስ ከፍቷል።

ሟች ባለቤቱ ካሮል የምትባል ሲሆን ጥቃቱ በተፈጸመበት ቦታ ወዲያውኑ ነበር ሕይወቷ ያለፈው።

ከሟቾቹ መካከል ሁለት የሞተርሳይክል ትራንስፖርት የሚሰጡ ሰዎች ይገኙበታል።

በተጨማሪም ሁለት ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን በአሁኑ ወቅት በሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ነው።