ጃፓናዊው ቢሊየነር ጠፈር ላይ ጎልፍ የመጫወት ዕቅድ እንዳለው ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጃፓናዊው ቢሊየነር ዩሳኩ ማኤዛዋ ለጉብኝት ወደ ዓለም አቀፉ የሕዋ ምርምር ተቋም ያቀና ሲሆን ይህም በቅርብ ዓመታት ወደ ጠፈር ለጉብኝት የተጓዘ የመጀመሪያው ሰው ያደርገዋል።
ጃፓናዊውን ቢሊነር የያዘችው ሩሲያ ሰራሿ ሮኬት ከካዛኪስታን ተወንጭፋለች።
ዩሳኩ ማኤዛዋ በዓለም አቀፉ የሕዋ ተቋም ለ12 ቀናት ይቆያል። ይህ የቢሊየነሩ ጉዞ ብዙ ከተነገረለት እና እአአ 2023 ላይ ወደ ጨረቃ ለማድረግ ካቀደው በራራ በፊት የተከናወነ የመጀመሪያው ምዕራፍ ተደርጎ ተወስዷል።
ማኤዛዋ ዛሬ ረቡዕ ወደ ጠፈር ያቀናው ከሩሲያዊው ጠፈርተኛ አሌክሳንድር ሚሱረኪን እና ለዩቲዩብ ቻናሉ ቪዲዮ ከሚቀርጽለት ዮዞ ሂራኖ ጋር ነው።
ጃፓናዊው ቢሊየነር ከዚህ ቀደም ወደ ጠረፍ የሚደረገው ጉዞን በተመለከተ በሰጠው መግለጫ፤ "ሰዎች ተስፋ እና ሕልም አላቸው። እንደ እኔ ያለ ሰው ወደማይታወቅ ዓለም የመጓዝ ህልሙ ወደ እውነት ተቀየረ ማለት ነው" ሲል ተናግሮ ነበር።
ቢሊየነሩ በሰዎች ጥቆማ በምርምር ተቋሙ ሳለ 100 ተግባራትን ለማከናወን ማቀዱን አስታውቋል። ከእነዚህም መካከል ጎልፍ መጫወት እና ከወረቀት የተሰራ አውሮፕን መወርወር በጃፓናዊው ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ ተግባራት ናቸው።
ማኤዛዋ ለዚህ ጉዞ 88 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ማድረጉ ተገልጿል። ከጃፓናዊው በፊት የዓለማችን ቁጥር ሁለት ባለ ጸጋ ጄፍ ቤዞስ እና እንግሊዛዊው ሪቻርድ ብራንስን ከወራት በፊት በግል በገነቧቸው ሮኬቶች ወደ ጠረፍ ተጉዘው ነበር።

ዩሳኩ ማኤዛዋ ማን ነው?
ጃፓናዊው ሥራ ፈጣሪ በሙዚቃ ስራዎች ላይ ባለው ተሳትፎ ይታወቃል። የቀድሞ የድራም ተጫዋቹ እአአ 1998 ላይ የሙዚቃ ሲዲዮች እና ቅጂዎችን የሚሸጥ ኩባንያ መስርቶ ነበር።
ቀጥሎም መሠረቱን ኢንተርኔት ላይ ያደረገ ሽያጭ ኩባንያ መስርቶ እድሜው በ30ዎቹ አጋማሽ ላይ ቢሊየነር መሆን ችሏል።
ፎርብስ ጋዜጣ ዩሳኩ ማኤዛዋ 1.9 ቢሊዮን ዶላር በማፍራት የጃፓና 30ኛ ባለ ጸጋ ሰው ነው ብሎታል።
ማኤዛዋ ወደ ጠረፍ የመጓዝ ፍላጎት በቅርብ ዓመታት ሲዘገብ ቆይቷል። እአአ 2019 ላይ በስፔስኤክስ ፕሮጀክት አማካኝነት በግሉ ወደ ጨረቃ የሚጓዝ ግለሰብ መሆኑ ተገልጾ ነበር።
ወደ ጨረቃ የሚደረገው እና ዲርሙን የሚል ስያሜ የተሰጠው በረራ እአአ ሕዳር 2023 ላይ ለማካሄድ ቀጠሮ ተይዟል።
ማኤዛዋ ከአንድ ዓመት በፊት ወደ ጠፈር አብራኝ ልትጓዝ የምትችል አዲስ ፍቅረኛ እፈልጋለሁ ብሎ በርካቶች ማመልከቻ ካቀረቡ በኋላ ሃሳቡን መሰረዙ ይታወሳል።












