የአፍሪካ ሕብረት በኦሚክሮን ምክንያት በአባል አገራቱ ላይ የጉዞ እቀባ መደረጉን አወገዘ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአፍሪካ ሕብረት ምዕራባዊያን አገራት በአዲሱ የኮቪድ ዝርያ ኦሚክሮን ምክንያት በአፍሪካ አገራት ላይ የጣሉትን እቀባ ተቃወመ።
ኦሚክሮን የሚል ስም የተሰጠው አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ በደበብ አፍሪካ መገኘቱን ተከትሎ ምዕራብ አገራት በአባል አገራት ላይ የጣሉት የጉዞ እቀባ ተቀባይነት እንደሌለው ሕብረቱ ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።
ደቡብ አፍሪካ አዲሱን ቫይረስ ማግኘቷና በተገቢው ፍጥነት ለዓለም ማሳወቋ የሚደነቅ ነው ያለው የሕብረቱ መግለጫ፤ ነገር ግን ደቡብ አፍሪካ ይህን በምታደርግበት ጊዜ ቫይረሱ በሌሎች የአውሮፓ አገራት እንደነበረ ፍንጮች መኖራቸውን ገልጧል።
ያም ሆኖ ደቡብ አፍሪካ ተህዋሲው መኖሩን በማጋለጧ መቀጣት አይገባትም ይላል መግለጫው።
እንደ ዩናይትድ ኪንደግም፣ አሜሪካ እና ካናዳ ያሉ አገራት የኦሚክሮንን መገኘት ተከትሎ ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ ሌሎች የደቡባዊ አፍሪካ አገራት ላይ ጉዞ እቀባ ጥለዋል።
ምዕራባዊያን በደቡብ አፍሪካ አገራት ላይ የጣሉት የጉዞ እቀባ የምጣኔ ሀብት ፈተና እንደሚፈጥርም ሕብረቱ በመግለጫው ጠቅሷል።
ኦሚክሮን እና የሚሰራጭበት ፍጥነትና ጠቅላላ ባህሪያቱ ገና በመጠናት ላይ ያለ ሆኖ ሳለ ሥርጭቱ አደገኛ ነው በሚል አባል አገራቱ ላይ እቀባ መጣል ተቀባይነት ስለሌለው በአስቸኳይ የጉዞ እገዳ ይነሳላቸው ሲል የአፍሪካ ሕብረት አሳስቧል።
አሁን በአባል አገራት የተጣሉ የጉዞ ክልከላዎች ከምጣኔ ሀብት ተግዳሮቶች ባሻገር የሕክምና ቁሳቁሶች ወደ አፍሪካ እንዳይገቡ ሌላ ፈተና ይደቅናልም ብሏል።
ይህም ብቻ ሳይሆን የደቡብ አፍሪካ ተመራማሪዎች ለምርምር የሚያስፈልጓቸውን ቁሳቁሶች እንዳያገኙም ያደርጋቸዋል።
በዚህና ሌሎች ምክንያቶች የተነሳ የአፍሪካ አገራትን መርጦ የጉዞ እቀባ ማድረግ ተቀባይነት የሌለውና አሳፋሪም ነው ሲል መግለጫው ይቋጫል።
የደቡብ አፍሪካ ባለስልጣናት በተመሳሳይ ይህን በአፍሪካ አገራት የተጣለውን እቀባ መኮነናቸው ይታወሳል።












