በቡሩንዲ ማረሚያ ቤት በደረሰ ቃጠሎ በትንሹ የ38 ሰዎች ህይወት አለፈ

የፎቶው ባለመብት, SOS MEDIAS VIA REUTERS
በቡሩንዲ ማረሚያ ቤት በደረሰ የእሳት አደጋ በትንሹ የ38 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በርካቶች ደግሞ ቆሰሉ።
የሃገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮስፐር ባዞምባንዛ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት የእሳት አደጋው በዋና ከተማው ጊቴጋ በሚገኘው እና በተጨናነቀ ማረሚያ ቤት ላይ የደረሰ ሲሆን በትንሹ 69 ሰዎች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በማሕብራዊ ሚዲያዎች በተዘዋወረ ቪዲዮ ላይ የማረሚያ ቤቱ ህንጻ ሲቃጠል እና የታራሚዎች ነው የተባለ የአስከሬን ክምር ታይቷል።
አንድ ታራሚ ለቢቢሲ በስልክ "በእውነቱ በጣም አስከፊ ነው" ሲል ሁኔታውን ገልጿል።
"በእኔ ግምት 90 በመቶ የሚሆኑት የመኝታ አዳራሾች ተቃጥለዋል" ብሏል።
የጊቴጋ ሆስፒታል ነርሶች ተጎጂዎችን ለመርዳት ወደ ማረሚያ ቤቱ ገብተው ህይወታቸው ያለፈውን እና የቆሰሉትን እያወጡ ነው ሲሉ ከእስር ቤቱ ውጪ ያለ ጋዜጠኛ ለቢቢሲ ተናግሯል።
እሳቱ በሃገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር 10፡00 ሰዓት ገደማ ነው የተቀሰቀሰው።
አንድ ታራሚ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል "እሳቱ በጣም ከፍ እያለ ሲሄድ እንቃጥላለን ብለን መጮህ ጀመርን። ነገር ግን ፖሊሶች "የደረሰን ትዕዛዝ ነው" በማለት የክፍሎቹን በሮች ለመክፈት ፈቃደኛ አልሆኑም" ሲል በስልክ ገልጿል።
"እንዴት እንዳመለጥኩኝ ባላውቅም ሙሉ በሙሉ የተቃጠሉ ታራሚዎች አሉ" ሲልም አክሎ ተናግሯል።
እሳቱ በቁጥጥር ስር መዋሉን የዓይን እማኞች ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።
400 እስረኞችን የመያዝ አቅም ያለው የጊቴጋ ማረሚያ ቤት ካለፈው ወር ጀምሮ 1,539 እስረኞችን መያዙን ክርስቲያን አሶሴሽን አጌነስት ቶርቸር የተባለ ተቋም ገልጿል።
የቡሩንዲ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በትዊተር ገጻቸው ቃጠሎው በኤሌክትሪክ ገመድ ምክንያት መፈጠሩን አስፍረዋል።
በነሐሴ ወር በተመሳሳይ ማረሚያ ቤት ሌላ የእሳት ቃጠሎ ደርሶ ነበር። በተመሳሳይ ባለሥልጣናቱ የኤሌክትሪክ ችግርን በምክንያትነት አቅርበዋል። የነሐሴው ቃጠሎ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት አላደረሰም።












