ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደሆነች ቤተሰቦቿ ገለጹ

የፎቶው ባለመብት, Meaza/fb
ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ በፀጥታ ኃይል አባላት ከአባቷ መኖሪያ ቤት ተይዛ መወሰዷንና በፖሊስ ቁጥጥር ስር መሆኗን ቤተሰቦቿ ለቢቢሲ ተናገሩ።
መዓዛ ከዚህ ቀደም አባይ ሚዲያ በተሰኘ የዩትዩብ ገጽ ብሎም በቅርቡ ራሷ ባዋቀረችው 'ሮሃ' የተሰኘ የዩትዩብ መድረክ ላይ በወቅታዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ዝግጅቶችን ስታቀርብ ቆይታለች።
ጋዜጠኛ መዓዛ ከአባቷ መኖሪያ ቤቷ የሲቪል ልብስ በለበሱ "ፖሊሶች ነን" ባሉ ግለሰቦች ዛሬ ቅዳሜ ታኅሣስ 02/2014 ዓ.ም ጠዋት ሦስት ሰዓት ገደማ መወሰዷን እህቷ አገኘሁወርቅ አበበ ለቢቢሲ ተናግራለች።
መዓዛ አባቷን ለመጠየቅ ቤታቸው ሄዳ እየወጣች ባለችበት ወቅት ግለሰቦቹ መጥተው ማንነቷን ካረጋገጡ በኋላ ይዘዋት መሄዳቸውን ታላቅ እህቷ ተናግራለች።
"ቤት ውስጥ ከአባታችን ውጪ ማንም የለም ነበር። ሁላችንም ወደ ሥራ ሄደን ነበር። አባቴ ደግሞ ታማሚ ስለሆን ማናችሁ ብሎ እንኳን ለመጠየቅ አልቻለም ነበር። አሁን ሁላችንም በየቦታው ተሰማርተን እየፈለግናት ነው" ስትል መዓዛ ወደየት እንደተወሰደች እንደማያውቁ ገልጻ ነበር።
ነገር ግን ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ የፀጥታ ኃይሎች ጋዜጠኛ መዓዛን ወደ መኖሪያ ቤቷ መለሰው ይዘዋት በመምጣት ፍተሻ ማድረጋቸውን ቤተሰቦቿ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጨምረውም ፖሊሶች ጎረቤት ጠርተው በቤቷ ውስጥ ፍተሻ ካካሄዱ በኋላ "ምንም ሳያገኙ ተመልሰው ይዘዋት ሄደዋል" ሲሉ ገልጸዋል።
ከዚህ በኋላም መዓዛ በተለምዶ ሦስተኛ ጣቢያ ተብሎ የሚጠራው የአዲስ አበባ ፖሊስ እንደምትገኝ መስማታቸውን ታላቅ እህቷ ተናግራለች።
ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ የአምስት ዓመት ልጅ ያለቻት ሲሆን አሁን ልጇ ከአያቶቿ በተመሳሳይ የኮንዶሚኒየም ብሎክ ላይ ከሚኖሩት አያቷ ጋር እንደምትገኝ እህቷ ገልጻለች።
የጋዜጠኛ መዓዛ ታናሽ እህት አገኘሁወርቅ ፖሊሶች ነን ባሉ ሰዎች መያዟን የሰማችው ከቅርብ ሰው ሲሆን፤ ጋዜጠኞች እየተያዙ መሆኑን መስማቷን ነገር ግን መዓዛ በምን ምክንያት እደተያዘች እንደማታውቅ ገልጻለች።
"አሁን ላይ ምንም ማለት አንችልም። እሷን ግዴታ ማግኘት አለብን" በማለት ስለመዓዛ አስር አጠቃላይ ሁኔታ ለማወቅ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን አመልክታለች።
ጓደኞቿና ባልደረቦቿ መዓዛ መሐመድ በፀጥታ ኃይሎች ስለመያዟ ከቤተሰቦቿ መስማታቸውን እንጂ በአሁኑ ወቅት የት እንዳለች እንደማያውቁ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አስካሁን የመዓዛ መሐመድን ፖሊሶች ነን ባሉ የፀጥታ ኃይሎች መያዝ በተመለከተ ከፖሊስ በኩል የተባለ ነገር የለም።
ጋዜጠኛ መዓዛ በዚህ ሳምንት ብቻ መታሰራቸው ከተነገረ ሦስት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች መካከል ነች።
ከእነዚህም መካከል የኡቡንቱ የዩቲዩብ መድረክ ባልደረባ የሆነው አክቲቪስት እያስፔድ ተስፋዬ ማክሰኞ ኅዳር 28/2014 ዓ.ም እስካሁን ምክንያቱ በይፋ ባልተገለጸ ምክንያት ከወላጆቹ መኖሪያ ቤት በፀጥታ ኃይሎች ተይዞ መወሰዱ የሚታወስ ነው።
እንዲሁም አርብ ታኅሣሥ 01/2014 ዓ.ም ረፋድ ላይ የቀድሞው የአዲስ ነገር ባልደረባና ተራራ ኔትወርክ የተባለው የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ መስራችና ዋና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ በተመሳሳይ ከመኖሪያ ቤቱ በፖሊስ ተይዞ መወሰዱ ተዘግቧል።
የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪው ተቋም ሲፒጄ ከቀናት በፊት ባወጣው ሪፖርት ጋዜጠኞችን በማሰር ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት ኢትዮጵያ በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ አመልክቷል።















