አሜሪካዊቷ ለአይሲስ ሴቶችን ታሰለጥን እንደነበር አመነች

የፎቶው ባለመብት, ALEXANDRIA SHERIFF'S OFFICE
አሜሪካዊቷ ለአይሲስ ሴቶችን ታሰለጥን እንደነበር አመነች
አሜሪካዊቷ አሊሰን ኤክረን በሶሪያ የአይኤስ አሸባሪ ቡድን ውስጥ ከ100 በላይ ሴቶችን ስታሰለጥን እንደነበር ለፍርድ ቤት አመነች።
የልጆች እናትና የሕይወት ሳይንስ (ባዮሎጂ) መምህርት የነበረችው አሊሰን፤ አሜሪካን ለቃ ወደ ሊቢያና ሶሪያ ለትጥቅ ትግል የገባችው በፈረንጆቹ 2011 ነበር።
በሶሪያ ቆይታዋ ታዲያ አንድ ባታሊዮን የሚሆን የሴቶች እዝ ስታሰለጥን፣ ስታስታጥቅና ስትመራ እንደነበረ ለፍርድ ቤት አምናለች።
ጥፋተኛ ሆና ከተገኘች እስከ 20 ዓመት እስር ይጠብቃታል።
ፍርድ ቤት ከወራት በኋላ በአሊሰን ጉዳይ ብይን ይሰጣል።
አሊሰን ኤክረን አሁን 42 ዓመቷ ሲሆን በግብጽና ቱርክ የተወሰኑ ዓመታትን ከኖረች በኋላ ነበር ወደ ሶሪያ የዘመተችው።
አይኤስን ከተቀላቀለች በኋላ ኻቲባ ኑሳይባ የተባለ ሴቶች ብቻ የሚገኙበት ባታሊዮን ስታሰለጥን ቆይታለች።
ይህም በሶሪያ የአይኤስ ዋና ከተማ ተደርጋ በምትታሰበው ራቃ ውስጥ የሆነ ነበር።
አሊሰን ዋና ሚናዋ የነበረው ታዲያ ሴቶችና ሕጻናት ኤክ-47 ክላሽንኮቭ መሣሪያና የእጅ ቦንቦችን መጠቀም እንዲችሉ ማስቻል ነበር።
አጥፍቶ ጠፊዎችንም የቦንብ ዝናር ስታስታጥቅ እንደነበር ተደርሶበታል።
ትናንት ማክሰኞ ቨርጂኒያ ላይ በተሰየመው ፍርድ ቤት አሊሰን ድርጊቱን መፈጸሟን ያመነች ሲሆን ነገር ግን ሕጻናትን ቦንብ አጠቃቀም አሰልጥነሻል መባሏን አስተባብላለች።
ቀድሞ ካሰለጠነቻቸው ሴቶች መካከል የተወሰኑት በቀጣይ ይመሰክሩባታል ተብሎ ይጠበቃል።
አሊሰን ከራቃ በኋላ በኢራቅ ሞሱል የተወሰነ ጊዜ ኖራለች።
በፍርድ ሂደቱ ላይ ዳኛዋ ለልጆቿ ስትል የቅጣት ማስተባበያ ትጠይቅ እንደሆን በጠየቋት ጊዜ አሊሰን በከፍተኛ ሁኔታ ስታነባ ታይታለች።
የአሊሰን ቤተሰቦች እሷን ማግኘት አይፈልጉም።












