ፖሊስ ይግባኝ በመጠየቁ ጋዜጠኞቹ በዋስ ሳይፈቱ ቀሩ

የፎቶው ባለመብት, sm
ከሁለት ሳምንት በፊት በፀጥታ ኃይሎች ተይዘው ታስረው ከሚገኙት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች መካከል ፍርድ ቤት ሦስቱ በዋስ ከእስር እንዲለቀቁ ሲፈቅድ በሁለቱ ላይ ደግሞ ለፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ቀን ሰጠ።
ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብት በፈቀደላቸው ሦስቱ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ላይ ፖሊስ ይግባኝ የጠየቀ በመሆኑ ከእስር አለመለቀቃቸውን ጠበቃቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የፍትህ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ተመስገን ደሳለኝ፣ የገበያኑ ሚዲያ ባለቤት ሰለሞን ሹምዬ እንዲሁም የሮሃ ሚዲያ የዩቲዩብ ባለቤት መዓዛ መሐመድ ነበሩ የዋስትና ገንዘብ አስይዘው ከእስር እንዲለቀቁ ማክሰኞ ግንቦት 30/2014 ዓ.ም. ፍርድቤት የወሰነላቸው።
ጠበቃቸው አቶ ሄኖክ አክሊሉ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ፖሊስ በዋስትናው ውሳኔ ላይ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ የጠየቀ ሲሆን፣ ከሰዓት በኋላ ዳኞች ባለመኖራቸው ይግባኝ ሰሚው ችሎት ጉዳዩን ሳይመለከት ቀርቷል።
ስለዚህም በዚህ በዋስ እንዲለቀቁ የተወሰነላቸው ሰለሞን፣ መዓዛ እና ተመስገን ወደ አስር ቤት እንዲመለሱ መደረጋቸውንና ነገ ረቡዕ ሰኔ 01/2014 ዓ.ም. ጠዋት በይግባኙ ላይ ውሳኔ ይሰጣል ብለው እንደሚጠብቁ ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ፍርድ ቤቱ በተጨማሪም ፖሊስ በጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ እና በመስከረም አበራ ላይ እያደረገው ያለውን ምርመራ እንዲያከናውን ተጨማሪ የስድስት ቀናት ጊዜ ሰጥቷል።
የጋዜጠኞቹን ጉዳይ እየተመለከተ ያለው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው ታሳሪዎቹ እያንዳንዳቸው በአስር ሺህ ብር ዋስትና ከእስር ወጥተው ጉዳያቸውን ከውጪ እንዲከታተሉ ውሳኔ ያሳለፈው።
ጋዜጠኞቹ በቀጠሯቸው መሠረት ትናንት ሰኞ ግንቦት 29/2014 ዓ.ም. ችሎት በቀረቡበት ጊዜ ፖሊስ ምርመራውን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ቀን እንዲሰጠው የጠየቀ ሲሆን፣ የጋዜጠኞቹ ጠበቆች ግን ዋስትናቸው ተከብሮ ጉዳያቸውን ከውጪ እንዲከታተሉ ጠይቀው፣ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ለመስጠት ነበር ለዛሬ ማክሰኞ ቀጠሮ የያዘው።
ከፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላ የተመስገን ደሳለኝ፣ የሰለሞን ሹምዬ እና የመዓዛ መሐመድ ጠበቆችና ቤተሰቦች አስፈላጊውን ሂደት በመፈጸም ከእስር እንዲወጡ ጥረት ያደረጉ ቢሆንም ፖሊስ ባቀረበው ይግባኝ ምክንያት ታሳሪዎቹ በዋስ ከእስር ሳይወጡ መቅረታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ቁጥራቸው አስራ ስምንት የሚሆኑ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን መድረኮች ላይ የሚሰሩ ጋዜጠኞችና የሚዲያ ሙያተኞች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከቤታቸውና ከሥራ ቦታቸው በቁጥጥር ስር የዋሉት ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ነበር።
ፖሊስ በአብዛኞቹ ላይ በማኅበረሰቦች እና በሃይማኖቶች መካከል ግጭትና ሁከት በመቀስቀስ ጠርጥሮ በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው በተለያዩ ቀናት ፍርድ ቤት ባቀረበበት ወቅት መግለጹ ይታወሳል።
የጋዜጠኞቹ የጅምላ አስር የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንን ጨምሮ የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪዎችንና የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማሳሰብ መግለጫ በማውጣት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ላይ የተፈፀመው እስር በተመለከተ ስጋታቸውን የገለጹ ሲሆን “ይህ እስር በተለይ አሳሳቢ የሚሆንበት ምክንያት ከሚዲያ ሕግ በተቃራኒ መሆኑ ሳይሆን የሚያስከትለው ውጤት ከመገናኛ ብዙኃን ሐሳብን በነጻነት ከመግለጽ ባሻገር ስለሚሰፋ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ሲፒጄም የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት “ጋዜጠኞቹን ያለምንም ክስ በአስቸኳይ እንዲፈቱ እና የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች የዘፈቀደ እስራት፣ ጭቆና እና ሳንሱር ሳይፈሩ ሪፖርት እንዲያደርጉ መንግሥት ማረጋገጥ አለበት" ብለዋል።
እነዚህ በፀጥታ ኃይሎች የተያዙት ግለሰቦችን በተመለከተ ከመንግሥት በኩል የታሰሩት ጋዜጠኞች ሳይሆኑ በተለያየ በሕገወጥ ድርጊት ላይ የተገኙ ናቸው ብሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት “ከሙያቸው ጋር በተያያዘ የታሰሩ ጋዜጠኞች የሉም” በማለት፣ ጋዜጠኞቹ እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎቹ “ፖሊስ ወንጀል ስለመፈፀማቸው መረጃ ስላለው” በቁጥጥር ሥር እንዳዋላቸው የፌደራል ፖሊስ ቃል አቀባይ መናገራቸው ይታወሳል።












