ግብፅ የመስኖ እና የውሃ ሚኒስትርን ጨምሮ 13 አዳዲስ ሚኒስትሮችን ሾመች

ፕሬዝዳንት አል ሲሲ ከተሿሚ ሚኒስትሮች ጋር

የፎቶው ባለመብት, Egypt presidency

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት አል ሲሲ ከተሿሚ ሚኒስትሮች ጋር

የፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል ሲሲ ጥያቄን ተከትሎ የግብፅ ፓርላማ በአገሪቱ የካቢኔ ሚኒስትሮች ላይ ዋነኛ ለውጥ በማድረግ አዳዲስ ሹመቶችን አፀደቀ።

ፕሬዝዳንቱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በመመካከር በአገሪቱ የካቢኔ አባላት ላይ ከፍተኛ የተባለውን ለውጥ ለማድረግ በእረፍት ላይ የነበረው ፓርላማ አስቸኳይ ስብሰባ እንዲያደረግ የጠየቁት ባለፈው አርብ ነበር።

በዚህም መሠረት አብዛኞቹ ሚኒስትሮች በአዲስ የተተኩበት የአገሪቱ የካቢኔ ሚኒስትሮች ስብስብ 13 አዳዲስ ሚኒስትሮች ተካተውበት ለምክር ቤቱ ቀርቦ ዕሁድ ዕለት መጽደቁ ተዘግቧል።

በአዲሱ የግብፅ ካቢኔ ውስጥ ዋነኛ የሚባሉት የመስኖ እና የውሃ ሚኒስትርን ጨምሮ 13 ሚኒስትሮች በአዲስ ሲተኩ፣ የገንዘብ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በቦታቸው ቀጥለዋል።

የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል ሲሲ በሚኒስተሮቻቸው ላይ ለውጥ ያስፈለገበትን ምክንያት በማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር መድረኮች ላይ እንደገለጹት “በአገር ውስጥና በውጪ የአገሪቱን ጥቅም በማስጠበቅና ለዜጎች የሚሰጠውን አገልግሎት የበለጠ በማጎልበት የመንግሥትን የአፈጻጸም ብቃት ለማጠናከር ነው” ብለዋል።

ለዚህም በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ ሥራውን ለመጀመር ለሦስት ወራት ዕረፍት ተዘግቶ የነበረው የግብፅ ፓርላማ አባላትም “ለአስቸኳይ ጉዳይ” በሚል ለቅዳሜ እንዲሰበሰቡ ተጠርተው አዲስ የቀረቡትን ሚኒስትሮች ሹመት አጽድቀውታል።

ዕሁድ ዕለትም ተሿሚዎቹ ሚኒስትሮች ሥራ ለመጀመር በፕሬዝዳንቱ ፊት ቃለ መሐላ ፈጽመዋል።

ግብፅ ከፍተኛ ትኩረት ከምትሰጣቸው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶቿ መከከል አንዱ የሆነውን እና ኢትዮጵያ ልታጠናቅቀው የተቃረበችውን የታላቁ የኢትየጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይን ለዓመታት በቅርበት ሲከታተሉ የነበሩት የመስኖ እና የውሃ ሚኒስትሩ ሞሐመድ አብደል አቲ በአዲስ ተተክተዋል።

ባለፈው ሳምንት በሁለተኛ ተርባይን ኃይል ማመንጨት የጀመረውና ሦስተኛው ዙር የውሃ ሙሌቱን ያከናወነው በአፍሪካ ግዙፉ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የኢትዮጵያ ግድብ ላይ ግብፅ ለዓመታት ተቃውሞዋን ስታሰማ መቆየቷ ይታወቃል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የግብፅን የመስኖ እና ውሃ ሚኒስትርነት ቦታን የተረከቡት አዲሱ ተሿሚ ሃኒ ሴዊላም ሲሆኑ፣ አዲሱ ሚኒስትር በዘርፉ ሦስት አስርት ዓመታት የሚጠጋ ዕውቀትና ልምድ ያካበቱ መሆናቸው ተነግሯል።

ሃኒ ሴዊላም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በአውሮፓውያኑ 1991 እዚያው ግብፅ ውስጥ ከሚገኘው ዛግዚግ ዩኒቨርስቲ የምህንድስና ፋክልቲ በውሃ እና በአካባቢ መህንድስና አግኝተዋል።

ሴዊላም ካይሮ ውስጥ በሚገኘው የአሜሪካ ዩኒቨርስቲ በዘላቂ ልማት እና በውሃ ሃብት አስተዳደር ዘርፍ ቋሚ ፕሮፌሰር ሆነው አገለግለዋል። በዩኒቨርስቲው ውስጥም ሁለት ዘርፎችን በመመስረት እና በዳይሬክተርነት በመምራት አገልግለዋል።

በተጨማሪም በጀርመን ዩኒቨርስቲ ውስጥ በሃይድሮሎጂ ምህንድስና አካዳሚክ ዳይሬክተር ሆነው ሰርተዋል እንዲሁም የዩኔስኮ የውሃ እና የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ዋና ዳይሬክተርም ነበሩ።

ሃኒ ሴዊላም በዘላቂ ልማት፣ በውሃ ሀብት፣ በውሃ - በኃይል - በምግብ ተያያዥ ጉዳዮች እንዲሁም በደለል እና በሌሎችም የውሃ አስተዳደር ዘርፎች ከ25 ዓመታት በላይ የዘለቀ የማስተማርና የተግባር ልምድ እንዳላቸው ይነገራል።

መንግሥታዊው አል አህራም እንዳለው አዲሱ የግብፅ የመስኖ እና የውሃ ሚኒስትር የሚጠብቃቸው ቀዳሚ ሥራ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለው የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ይሆናል።

ኢትዮጵያ ግብፅ እና ሱዳን በሕዳሴው ግድብ የውሃ አሞላልና አጠቃላይ አስተዳደር ዙሪያ ለዓመታት ሲያደርጉት የነበረው ድርድር ምንም አይነት ስምምነትን ሳያስገኝ ግድቡ ወደ መጠናቀቁ እየተቃረበ ነው።

ምንም እንኳን ግብፅና ሱዳን አስገዳጅ ሕጋዊ ስምምነት ላይ ሳይደረስ ኢትዮጵያ የግድቡን ውሃ የመሙላት ሥራ እንዳትጀመር ግፊት ቢያደርጉም፣ ይህንን ዓመት ጨምሮ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ግድቡ በውሃ መሞላቱን ኢትዮጵያ አስታውቃለች።

ባለፈው ሳምንትም ኢትዮጵያ ግድቡ ከሚኖሩት 13 የኃይል ማመንጫ ተርባይኖች መካከል ሁለተኛውን ሥራ በማስጀመር፣ ቀደም ሲል በየካቲት ወር ኃይል ማመንጨት ከጀመረው ጋር በመሆን ከ500 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ከሕዳሴው ግድብ መመንጨት መጀመሩ ታውቋል።

ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን በግድቡ ዙሪያ ሲያደርጉት የነበረው ድርድር ከተቋረጠ የቆየ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ድርድሩ እንዲቀጥል በተደጋጋሚ ስትጠይቅ ቆይታለች።

ባለፈው ሳምንትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሁለተኛውን የኃይል ማመንጫ ተርባይንን ሥራ ባስጀመሩት ወቅት በግድቡ የውሃ ሙሌትና አጠቃላይ ሥራ ላይ ተቃውሞ እያሰሙ ካሉት ከግብፅ እና ከሱዳን ጋር ኢትዮጵያ ድርድር ለመቀጠል ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ኢትዮጵያ የታችኛው የአባይ ተፋሰስ አገራትን የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላት በመጥቀስ “ከድርድር ውጪ ያሉ አማራጮች የግድቡን ግንባታ አያስቆሙትም” በማለት በአገራቱ መካከል ሲካሄድ የነበረውና የተቋረጠው ንግግር እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

ከሳምንት በፊት ኢትዮጵያ የሕዳሴው ግድብ ሦስተኛው ዙር የውሃ ሙሌትን እንደምታከናውን እንደተገለጸላት በመጥቀስ ግብፅ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አቤቱታ አቅርባ ነበር።

ግብፅ ለመንግሥታቱ ድርጅት በጻፈችው ደብዳቤ ላይ ኢትዮጵያ ከስምምነት ላይ ሳይደርስ በተናጠል የግድቡን የውሃ ሙሌት ማከናወን የለባትም በሚል ተቃውሞዋን አስመዝግባለች።

ኢትዮጵያ ግን የግድቡ ግንባታም ሆነ የውሃው ሙሌት በታችኛው ተፋሰስ አገራት ላይ የሚያስከትለው የጎላ ጉዳት የለም በማለት ግንባታውን እና የውሃ ሙሌቱን ወደ ማጠናቀቅ እየተቃረበች ነው።