ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 83.3 በመቶ መድረሱ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, PM Office/Twitter
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሥራ ወደ 83.3 በመቶ መድረሱን የግድቡ ግንባታ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ተናገሩ።
ሥራ አስኪያጁ ይህንን ያሉት የግድቡ ሁለተኛው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ተርባይን ኃይል የማመንጨት ሥራን ለማስጀመር በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ላይ ነው።
ግንባታው ከተጀመረ አስር ዓመታትን ያስቆጠረው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ አብዛኛው የግንባታ ሥራው ወደመጠናቀቁ የተቃረበ ሲሆን ባለፈው የካቲት ወር የመጀመሪያውን የኃይል ማመንጨት ሥራውን መጀመሩ ይታወሳል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ሁለት ዙር የውሃ ሙሌት አካሂዶ ሦስተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት በዚህ ወር ያካሂዳል ተብሎ ሲጠበቅ ነው ሁለተኛው የኤሌክትሪክ ማመንጫ ተርባይን ሥራ መጀመሩ የተገለጸው።
በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ እና ሌሎች ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ግድቡ በሚገኝበት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ተገኝተዋል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የግድቡ ግንባታ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ እንደተናገሩት የግድቡ የሲቪል ሥራዎች ግንባታ 95 በመቶው መጠናቀቁን ተናግረዋል።
እንዲሁም ጠግድቡ ኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች ግንባታና እና ተከላ ወደ 61 በመቶ ከፍ ማለቱንና የውሃ ማስተላለፊያ የብረታ ብረት ሥራዎችን ደግሞ 73 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።
በዚህ ዓመትም ከሲቪል ሥራው በተጨማሪ በሜካኒካል ዘርፉ ተይዘው ከነበሩት ዕቅዶች መካከል በሁለት ተርባይኖች እና ጄኔሬተሮች ኃይል ማመንጨት ሥራው መከናወኑን አመለክተው፣ ዩኒት 9 አሁን ደግሞ ዩኒት 10 የተባሉት ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት ጀምረዋል።
ሥራ አስኪያጁ ጨምረውም ቀደም ባሉት ዓመታት ግድቡን እስከ 141 ሜትር ከፍ በማድረግ ሁለት የውሃ ሙሌቶች መከናወናቸውንና በተያዘው ዕቅድ መሠረትም ሦስተኛው ሙሌት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሥራ 83.3 በመቶ መድረሱን ያመለከቱት ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ፤ ቀሪዎቹን ሥራዎች በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ተኩል ውስጥ ለማጠናቀቅ ዕቅድ እንዳለ ተልጸዋል።
ዛሬ ኃይል የጀመረው የግድቡ 2ኛው ተርባይን ሲሆን ዩኒት ዘጠኝ የተባለው ሲሆን 270 ሜጋ ዋት የአሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም አለው ተብሏል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው የሁለተኛውን ተርባይን ሥራ ያስጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ በግድቡ የውሃ ሙሌትና አጠቃላይ ሥራ ላይ ተቃውሞ እያሰሙ ካሉት ከግብፅ እና ከሱዳን ጋር ኢትዮጵያ ድርድር ለመቀጠል ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ኢትዮጵያ የታችኛው የአባይ ተፋሰስ አገራትን የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላት በመጥቀስ “ከድርድር ውጪ ያሉ አማራጮች የግድቡን ግንባታ አያስቆሙትም” በማለት በአገራቱ መካከል ሲካሄድ የነበረውና የተቋረጠው ንግግር እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
ከሳምንት በፊት ኢትዮጵያ የሕዳሴው ግድብ ሦስተኛው ዙር የውሃ ሙሌትን እንደምታከናውን እንደተገለጸላት በመጥቀስ ግብፅ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አቤቱታ ማቅረቧ ይታወሳል።
ግብፅ ለመንግሥታቱ ድርጅት በጻፈችው ደብዳቤ ላይ ኢትዮጵያ ከስምምነት ላይ ሳይደርስ በተናጠል የግድቡን የውሃ ሙሌት ማከናወን የለባትም በሚል ተቃውሞዋን አስመዝግባ ነበር።
ኢትዮጵያ ግን የግድቡ ግንባታም ሆነ የውሃው ሙሌት በታችኛው ተፋሰስ አገራት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት የለም በማለት ግንበታውን እና የውሃ ሙሌቱን ወደ ማጠናቀቅ ተቃርባለች።
ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ፈሶበት ከአምስት ሺህ በላይ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል የተባለው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአካባቢው አገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።
የሕዳሴው ግድብ
የግንባታው መሠረተ ድንጋይ መጋቢት 24/2003 ዓ.ም የተጣለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ በስተምዕራብ ከሱዳን ጋር በምትዋሰንበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በጉባ ወረዳ ይገኛል።
ግድቡን ለመገንባት 80 ቢሊየን ብር (ከ4 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ) የሚያስወጣ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ ግንባታው በዋናነት በጣሊያኑ ሳሊኒ ኢምፕሬጂሎ በተባለው ሥራ ተቋራጮ የሚከናወን ነው።
ግንባታው ሲጠናቀቅ በአፍሪካ ግዙፉ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ የሚሆነው የሕዳሴ፣ ከፍታ 145 ሜትር ሲሆን፤ ርዝመቱ 1 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ነው።
ግድቡ ሙሉ ለሙሉ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ የሚይዘው የውሃ መጠን 74 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ሲሆን፤ ግድቡ የሚሸፍነው የቦታ ስፋት ደግሞ 1 ሺህ 680 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ይሆናል።
ለዚህም በተከታታይ ዓመታት የሚካሄድ የውሃ ሙሌት የሚኖር ሲሆን በ2012 ዓ.ም እና 2013 ዓ.ም ሁለት ክረምቶች ለተከታታይ ጊዜ የውሃ ሙሌት ተካሂዶ በዚህ ዓመትም ሙሌቱ ይካሄዳል።
የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የሆነው ይህ ግድብ 13 ተርባይኖች የሚኖሩት ሲሆን አንዱ ተርባይን 375 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳለው ተገልጿል።
በተያዘለት ዕቅድ መሠረትም የካቲት 13/2014 ዓ.ም. በአንድ ተርባይን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን፣ ሁሉም ተርባይኖች ሥራ ሲጀምሩ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ አጠቃላይ የማመንጨት አቅሙ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት ይደርሳል።












