ሶማሊያ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ለግብፅ አልወገንኩም አለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ኢትዮጵያ እየገነባችው ባለው በታላቁ የሕዳሴ ግግድብ ዙሪያ ለግብፅ የሚወግን አስተያየት አለመሰንዘራቸው የአገሪቱ መንግሥት አስታወቀ።
የሶማሊያ መንግሥት ይህን ያለው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ከግብፁ አቻቸው አብዱለ ፋታህ አል ሲሲ ጋር ካይሮ ውስጥ በተደረገ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ኢትዮጵያ እየገነባች ባለችው ግድብ ዙሪያ ተነጋግረዋል መባሉን ተከትሎ ነው።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ አብዲካሪን አሊ ካር፤ “የግብፅ እና የሶማሊያ ፕሬዝዳንቶች የግድቡ ግንባታ እና አሞላል በተመለከተ ምንም አይነት ይፋዊ አቋም አላንጸባረቁም” ብለዋል።
አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ባለፈው ሳምንት ምብቂያ ላይ ወደ ግብፅ ካመሩ በኋላ፣ ከፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል ሲሲ ጋር በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸው በስፋት ተዘግቦ ነበር።
ሁለቱ መሪዎች ከውይይታቸው በኋላ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ አብዱል ፋታህ አል ሲሲ ከሶማሊያው አቻቸው ጋር በዓለም አቀፍ ወንዞች ላይ በሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ዙሪያ “አደገኛ የተናጠል ፖሊሲዎች” ባሏቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ተናግረዋል።
የግብፁ ፕሬዝዳንት በዚሁ መግለጫቸው ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ “የተናጠል እርምጃ መውሰዷ አሉታዊ ውጤት ይኖረዋል” ማለታቸውንም አናዶሉ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የግብፅ ዕለታዊ ጋዜጣ አል አህራም በበኩሉ በዚሁ የጋራ መግለጫ ላይ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ በሕዳሴ ግድብ ሙሌትና ሥራ ዙሪያ ሕጋዊ እና አሳሪ ስምምነት ስለመድረስ አስፈላጊነት ከአል ሲሲ ጋር መስማማታቸውን ተናግረዋል ብሎ ዘግቧል።
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ አብዲካሪን አሊ ካር ግን በጉዳዩ ላይ የሶማሊያ አቋም በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ዓለም አቀፍ ሕጎችን መደገፍ ነው ብለዋል።
ቃል አቀባዩ ካር ሁለቱ መሪዎች በካይሮ በሰጡት የጋራ መግለጫ ላይ፤ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት “በግድቡ ዙሪያ የአገሪቱን አቋም የሚያንጸባርቅ ንግግር አላደረጉም” ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እያካሄደችው ካለው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ግብፅ እና ሱዳን በአገራቱ መካከል ሕጋዊ እና አሳሪ ስምምነት ሳይደረግበት የግድቡ ውሃ ሙሌት እንዳይካሄድ አጥብቀው ሲጠይቁ መቆየታቸው ይታወሳል።
ነገር ግን ኢትዮጵያ የሁለቱን አገራት ጥያቄን ሳትቀበለው ባለፉት ሁለት ዓመታት በሁለት ዙር ግድቡን በውሃ የመሙላት ተግባርን በስኬት ማከናወኗን አሳውቃ፣ በቀጣይ ነሐሴ ወር ደግሞ ሦስተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ለመካሄድ ተዘጋጅታለች።
በዚህ ዓመትም ግድቡ ካሉት 13 የኃይል ማመንጫ ተርባይኖች መካከል አንዱን ወደ ሥራ በማስገባት የሙከራ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ጀምራለች።
ግብፅ ለዘመናት ያለገደብ ስትጠቀምበት የነበረውን የውሃ መጠን ግንባታው እየተጠናቀቀ ያለው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ይቀንስብኛል በሚል፣ የግድቡን ውሃ አያያዝና አለቃቅ በተመለከተ ኢትዮጵያ አስገዳጅ ስምምነት እንድትፈርም ትፈልጋለች።
ግብፅ ይህን ፍላጎቷን ለማሳካት በኢትዮጵያ ላይ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ጫና እያሳደረች ትገኛለች።
በዚህም ከአካባቢው አገራት በሻገር ኃያል አገራት እንዲደግፏት ጉዳዩን ወደ ፀጥታው ምክር ቤት ጭምር ወስዳዋለች።
ከኢትዮጵያ ጋር ረጅም ድንበር የምትጋራውና ለአስርታት ባለመረጋጋት ውስጥ የምትገኘው የሶማሊያ መንግሥት የኢትዮጵያ ሠራዊት አባል በሆነበት በአፍሪካ ኅብረት የሠላም አስከባሪ ኃይል የሚደገፍ ነው።
የኢትዮጵያ የቅርብ ወዳጅ በነበሩት በቀድሞው የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ የሥልጣን ዘመን ከግብፅ ጋር የነበረው ግንኙነት ቀዝቃዛ የነበረ ሲሆን፣ የሰሞኑ የካይሮ ጉብኝትም ይህንን ግንኙነት ለማደስ እንደሆነ ይታመናል።
የሶማሊያ መሪዎች ኢትዮጵያ እና ግብፅ በሚወዛገቡበት የሕዳሴው ግድብ ጉዳይ በይፋ አቋማቸውን ከመግለጽ ተቆጥበው ቆይተዋል።












