ሩሲያ ከዓለም አቀፉ የጠፈር ማዕከል ልትወጣ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሩሲያ በአውሮፓውያኑ 2023 ራሷን ከዓለም አቀፉ የጠፈር ማዕከል በማግለል የራሷን የጠፈር ማዕከል እንደምትገነባ አስታወቀች።
ሩሲያ እና አሜሪካ ከሌሎች አጋሮች ጋር በመሆን እአአ ከ1998 ጀምሮ የዓለም አቀፉን የጠፈር ማዕከል በማቋቋም በጋር ሲጠቀሙበት እና ሲጠግኑ ቆይተዋል።
ይሁን እንጂ ሩሲያ ዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመች በኋላ በሁለቱ ኃያላን አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ሻክሯል።
ሩሲያ ከዚህ ቀደም ምዕራባውያን አገራት ማዕቀብ በመጣላቸው ራሷን ከጠፈር ማዕከሉ እንደምታገል አስታውቃ ነበር።
ናሳ በበኩሉ ሩሲያ ራሷን ከጠፈር ጣቢያው እንደምታገል በይፋ አልተነገረኝም ብሏል።
እአአ ከ1998 ጀምሮ ለበርካታ ሳይንሳዊ ምርምሮች ድጋፍ ሲያደርግ የቆየው ማዕከሉ እስከ 2024 ድረስ በአገራቱ ትብብር በሥራ ላይ እንዲቆይ ስምምነት ያለ ሲሆን፤ አሜሪካ ይህ ውል ለተጨማሪ 6 ዓመታት እንዲራዘም ፍላጎት ነበራት።
የሩሲያ የጠፈር ማዕከል ኃላፊ ዩሪይ ቦሪሶቭ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር በነበራቸው ውይይት ላይ ሩሲያ ከአጋሮቿ ጋር የነበራትን ውል ካጠናቀቀች በኋላ የራሷን ከጠፈር ማዕከሉ ታገላለች ሲሉ ተናግረዋል።
ቦሪሶቭ እስከ አውሮፓውያኑ 2024 ድረስ የተቋማቸው ቀዳሚው ተግባር የሩሲያን የጠፈር ማዕከል መገንባት እንደሆነ ከተናገሩ በኋላ፤ ፑቲን “መልካም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ሩሲያ ከዓለም አቀፉ የጠፈር ማዕከል ራሷን ማግለሏ የማዕከሉ የወደፊት ዕጣን እንዴት ሊቀይር እንደሚችል እስካሁን ግልጽ አይደለም።

የፎቶው ባለመብት, ROSKOSMOS
አሜሪካዊው የቀድሞ የዓለም አቀፉ የጠፈር ማዕከል አዛዥ ዶ/ር ሊኦሪ ቻኢኦ ግን ሩሲያ የጠፈር ማዕከሉን በትክክል ጥላ ለመውጣት ከውሳኔ መድረሷ አጠራጣሪ ነው ይላሉ።
“ሩሲያውያኑ ተጽእኖ ፈጣሪነታቸውን ለማሳየት ካልሆነ በቀር ሌላ የጠፈር ማዕከል መገንባት የሚያስችል ገንዘብ የላቸውም። የጠፈር ማዕከል ለመገንባት ረዥም ዓመታትም ይወስዳል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እስካሁን ድረስ የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ዋሽንግተን ዲሲ እና ሞስኮ በዓለም አቀፉ የጠፈር ማዕከል ላይ ያላቸው ትብብር ላይ ይህ ነው የሚባል ተጽዕኖ አላሳደረም ነበር።
ይሁን እንጂ የዩክሬን ጦርነት በሌሎች ዘርፎች ላይ የአሜሪካ እና ሩሲያ ግንኙነትን ከመቼውም ጊዜ በላይ አሻክሮታል።
የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት እንዲሁም የአሁኗ ሩሲያ በጠፈር ምርምር የረዥም ጊዜ ልምድ አላቸው። እአአ 1961 ወደ ጠፈር ሰው መላካቸው ትልቅ ብሔራዊ ኩራት ነው።












