በቀጥታ ስርጭት ላይ የነበረው ቅንጡው ሰባኪ 1 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ጌጣጌጦቹን ተዘረፈ

ፓስተሩ በሚያደርጋቸው ውድ እና ብልጭልጭ ጌጣጌጦች ይታወቃል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በብልጭልጭ አኗኗሩ የሚታወቀው የኒው ዮርክ ከተማ ሰባኪ በቀጥታ ስርጭት ስብከቱን በማስተላለፍ ላይ እያለ ከአንድ ሚሊየን ዶላር በላይ የሚያወጡ ጌጣጌጦቹን ተዘረፈ።

የ44 ዓመቱ ቢሾፕ ላሞር ዋይትሄድ ወንጀለኞች “የትም አያመልጡም” ሲል ተናግሯል።

ፖሊስ ክስተቱን በማጣራት ላይ የሚገኝ ሲሆን እስካሁን የተጠረጠረ ወይም በቁጥጥር ሥር የዋለ ሰው እንደሌለ ገልጿል።

ሮልስ-ሮይስ ቅንጡ መኪና የሚያሽከረክረው ሰባኪ፤ ሮሌክስ ሰዓት፣ አልማዝ እና ኢመራልድ ተዘርፏል።

ሰባኪው በቀጥታ ስርጭቱ ላይ "ስንትዎቻችሁ ሌላ ሰው ሲሞት ስላያችሁ እምነታችሁን አጥታችኋል?" በማለት እየጠየቁ ሳለ ነበር በርካታ ጭምብል ያጠለቁ እና የታጠቁ ዘራፊዎች ብሩክሊን ወደሚገኘው ቤተክርስትያን የገቡት።

በአገልግሎቱ ወቅት ምን ያህል ሰዎች እንደነበሩ እስካሁን ግልጽ አይደለም።

"ሽጉጣቸውን ይዘው ወደ መቅደስ ሲገቡ ስመለከት ሁሉም ሰው መሬት ላይ እንዲተኛ ጠየቅኩ፣ ሰዎችም እንደዛው አደረጉ’’ ሲል ሰባኪው በኢንስታግራም ገጹ ላይ ተናግሯል።

"ቤተክርስቲያኑ ውስጥ ተኩስ ለመክፈት ይምጡ ወይም ለዝርፊያ ብቻ የመጡ መሆናቸውን አላወቅኩም ነበር" ሲሉም አክለዋል።

እንደ ቢሾፕ ዋይትሄድ ገለጻ ጭንብል ያጠለቁት ሌቦች በመርሴዲስ መኪና ተጭነው አምልጠዋል።

በኢንስታግራ ገጻቸው "የቤተ ክርስቲያንን በር ረግጣችሁ በአገልግሎት መሀል ሽጉጥ ይዛችሁ በመግባታችሁ ፈጣሪ በእናንተ ላይ የሚያደርግባችሁ እኔ ማድረግ ከምችለው በላይ ነው" ሲል ለዘራፊዎቹ ተናግሯል።

የኒው ዮርክ ከተማ ከንቲባ ኤሪክ አዳምስ በሰጡት መግለጫ የኒው ዮርክ ፖሊስ ወንጀሉን እየመረመረ ይገኛል ብለዋል።

"የእምነት መሪዎቻችን ይቅርና ማንም ሰው በዚህ ከተማ ውስጥ የታጠቁ ሰዎች በሚያደርጉት ዘረፋ ሰለባ መሆን የለበትም’’ ሲሉ ከንቲባው ተናግረዋል።

ኋይትሄድ በበኩሉ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ የሚጠቅም መረጃ ለሚሰጥ ሰው የ50,000 ዶላር ሽልማት አዘጋጅቷል።