“አልሸባብን ብንመክተውም ከዚህ በኋላ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል” ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፌ 

ፕሬዝዳንት ሙስጠፌ ከሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ጋር

የፎቶው ባለመብት, SRTV

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ሙስጠፌ ከሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ጋር

የሶማሊያው እስላማዊ ታጣቂ ቡድን አልሻባብ በሶማሌ ክልል ውስጥ የከፈተው ጥቃት የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች መክተው መመለሳቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ለቢቢሲ ተናገሩ።

አቶ ሙስጠፌ አልሻባብ በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመው ጥቃት አሁን ካለው ቀጠናዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ዝግጅቶች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ያሳየ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ ከቢቢሲ ጋር የስልክ ቃለ ምልልስ ባደረጉበት ዛሬ ማክሰኞ ሐምሌ 19/2014 ዓ.ም. ከሰዓት የአልሻባብ ታጣቂዎች ጥቃት ከፈጸሙባቸው የክልሉ አከባቢዎች አንዱ በሆነው ፌርፌር ወረዳ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

“የአልሸባብ የሸብር ዕቅድ ከሽፏል። ነገር ግን የቀጠናው የፖለቲካ ሁኔታዎች እና የአንዳንድ አገሮች ፍላጎት ስንመለከት ግን፤ ዝም ብለን መተኛት ሳይሆን ሌሎች ዝግጅቶች ያስፈልጋሉ” ሲሉ አቶ ሙስጠፌ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ መንግሥት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው እና መቀመጫውን ሶማሊያ ያደረገው አልሸባብ ካለፈው ሳምንት ረቡዕ ጀምሮ በተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቆ በመግባት በሶማሌ ክልል ውስጥ ጥቃቶችን ከፍቷል።

ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ሙስጠፌ፤ አልሸባብ ባለፉት ቀናት ጥቃት ከማድረሱ በፊት በክልሉ የተለያ የፀጥታ ስጋት እንዳልነበረ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ታጣቂ ቡድኑ ጥቃት ማድረሱ እንዲሁም ታጣቂ ቡድኑን ለመከላከል የተወሰደው እርምጃ ወደፊት የሶማሌ ክልልን ፀጥታን ለማረጋገጥ ዝግጁነት እንዲኖር ዕድል ይፈጥራል ሲሉ አስረድተዋል።

“. . . ከዚህ በኋላ እንዳንዘናጋ ዕድል ስለሚሰጥ የተሻለ ሁኔታ አለ ብዬ ነው የማምነው” ሲሉ አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከቀናት በፊት የእስላማዊ ቡድኑ ታጣቂዎች ለቁጥጥር አስቸጋሪ በሆነውና ረጅሙ የሶማሊያ እና የኢትዮጵያ ድንበር በኩል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ታጣቂዎቹን በማስገባት ጥቃት ሰንዝሯል።

የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ዘልቀው ከገቡ የአልሻባብ ታጣቃዎች ጋር ካለፈው ሳምንት ረቡዕ ጀምሮ በተለያዩ የድንበር አካባቢዎች ላይ መዋጋታቸውን የክልሉ መንግሥት ገልጿል።

ጥቃቱ የተፈፀመው ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር በምትዋሰንባቸው የድንበር ከተሞች ላይ ሲሆን በሁለቱም ወገኖች ዘንድ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት መድረሱን በወቅቱ ተዘግቦ ነበር።

ይህን በአልሸባብ የተከፈተውን ጥቃት ለመከላከል የአገር መከላከያ ሠራዊት ወደ ክልሉ መሰማራቱን የሶማሌ ክልል መንግሥት አስታውቋል።

አልሻባብ በሶማሊያ ውስጥ በስፋት የሚንቀሳቀስ ታጣቂ እስላማዊ ቡድን ሲሆን፣ ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው ይነገራል። ቡድኑ በሶማሊያ ውስጥ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ያጠፉ በርካታ የቦምብ እና የደፈጣ ጥቃቶችን ሲፈጽም ቆይቷል።

ቡድኑ ከሶማሊያ ባሻገር በኬንያ ውስጥ ተደጋጋሚ ከባድ የሽብር ጥቃቶችን የፈጸመ ሲሆን ጥቃቱ እስከ ኡጋንዳ ድረስ የዘለቀ ነው።

አልሻባብ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት እንደሚፈጽም በተደጋጋሚ ሲዝት የቆየ ቢሆንም ከሙከራ ያለፈ ጥቃት አድርሶ አያውቅም። አሁን ታጣቂዎቹ ድንበር ተሻግረው የከፈቱት ጥቃት ያልተጠበቀ ነው።

አልሻባብ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር አስርጎ ያስገባቸው ታጣቂዎቹ የከፈቱትን ጥቃት ተከትሎ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በወሰደው እርምጃ ወደ 200 የሚጠጉ የቡድኑ አባላት መገደላቸው ተገልጿል።

ቡድኑ ባለፈው ሐሙስ ለሮይተርስ እንደተናገረው በፈጸመው ጥቃት ከ80 በላይ የልዩ ፖሊስ አባላትን ገድያለሁ ማለቱ ይታወሳል።