የግብፅ እና የሶማሊያ መሪዎች ውይይት በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ

የፎቶው ባለመብት, Egypt presidency
የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል ሲሲ ለጉብኝት ወደ ካይሮ ከተጓዙት አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ጋር በኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸው ተዘገበ።
ሁለቱ መሪዎች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት ካደረጉ በኋላ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የግብፁ ፕሬዝዳንት እንደተናገሩት ከሶማሊያው አቻቸው ጋር በዓለም አቀፍ ወንዞች ላይ በሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ዙሪያ “አደገኛ የተናጠል ፖሊሲዎች” ባሏቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ገልጸዋል።
የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል-ሲሲ ከሶማሊያው አቻቸው ሐሰን ሼኽ ሞሐመድ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙርያ ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ በሰጡት መግለጫ፣ ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድቡን በተመለከተ “የተናጠል እርምጃ መውሰዷ አሉታዊ ውጤት ይኖረዋል” ማለታቸውን አናዶሉ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እያካሄደችው ካለው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ግብፅ እና ሱዳን የግድቡ ውሃ ሙሌት በአገራቱ መካከል ሕጋዊ እና አሳሪ ስምምነት ሳይደረግበት እንዳይካሄድ አጥብቀው ሲጠይቁ መቆየታቸው ይታወሳል።
ነገር ግን ኢትዮጵያ የሁለቱን አገራት ጥያቄን ሳትቀበለው ባለፉት ሁለት ዓመታት በሁለት ዙር ግድቡን በውሃ የመሙላት ተግባርን በስኬት ማከናወኗን አሳውቃ በቀጣይ ነሐሴ ወር ደግሞ ሦስተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ለመካሄድ ተዘጋጅታለች።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት እና የግብፁ አቻቸው በቀጥታ በቴሌቪዥን በተላለፈ የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሁለቱ መሪዎች የግድቡን የውሃ ሙሌት እና ቀጣይ ሥራን በተመለከተ አሳሪ ሕጋዊ ስምምነት መድረስ አስፈላጊ በመሆኑ ላይ መስማማታቸውን አልሲሲ ተናግረዋል።
“በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ባሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይተናል፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ወንዞች ላይ ከሚካሄዱ ፕሮጅክቶች አንጻር በተናጠል የሚካሄዱ ፖሊሲዎች የሚያስከትሉት አደጋ ላይ ተወያይተናል። እንዲሁም ለትብብር እና ለምክክር ተገዢ መሆን መርኅ ላይም ሃሳብ ተለዋውጠናል” ሲሉ አልሲሲሰ ተናግረዋል።
አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ በበኩላቸው በሕዳሴ ግድብ ሙሌትና ሥራ ዙሪያ ሕጋዊ እና አሳሪ ስምምነት ስለመድረስ አስፈላጊነት ላይ ከአል ሲሲ ጋር መስማማታቸውን እንደተናገሩ አል አህራም ጋዜጣ ዘግቧል።
ግብፅ ለዘመናት ያለገደብ ስትጠቀምበት የነበረውን የውሃ መጠን ግንባታው እየተጠናቀቀ ያለው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ይቀንስብኛል በሚል፣ የግድቡን ውሃ አያያዝና አለቃቅ በተመለከተ ኢትዮጵያ አስገዳጅ ስምምነት እንድትፈርም ትፈልጋለች።
ከዚህ ቀደም ሁለት ዙር የውሃ ሙሌት አከናውና ሦስተኛውን ለማካሄድ የተዘጋጀችው ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ግብፅ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ጥረት እያደረገች ነው። በዚህም ከአካባቢው አገራት በሻገር ኃያል አገራት እንዲደግፏት ጉዳዩን ወደ ፀጥታው ምክር ቤት ጭምር ወስዳዋለች።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ አብዱል ፋታህ አል ሲሲ በሳዑዲ አረቢያ ጉብኝት ያደረጉትን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን በማግኘት በታላቁ ሕዳሴ ግድብና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ይታወሳል።
ፕሬዝዳንት አል ሲሲ አገራቸው የግድቡን የውሃ ሙሌትና ቀጣይ ሥራን በተመለከተ የግብፅን የውሃ ዋስትና በሚያስከብር ሁኔታ “አሳሪ ሕጋዊ ስምምነት እንዲደረስ” ያላትን ጽኑ አቋም ለባይደን መግለጻቸውን ጽህፈት ቤታቸው አመልክቷል።
ፕሬዝዳንት ባይደንም አሜሪካ የግብፅን የውሃ ዋስትና እንደምትደግፍ እንዲሁም ለአካባቢው ሰላምና ብልጽግና አስተዋጽኦ የሚያደርግ፣ የሁሉንም ወገኖች ጥቅም የሚያስከብር ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ ላይ እንዲደረስ እንደሚፈልጉ መናገራቸውን ተገልጿል።
በዚህ ሳምንትም የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ማይክ ሐመር በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ በግብፅ እና በኢትዮጵያ ጉብኝት የሚያደርጉ ሲሆን፣ ከሚወያዩባቸው ጉዳዮች መካከልም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ አንዱ እንደሚሆን ተነግሯል።
ከኢትዮጵያ ጋር ረጅም ድንበር የምትጋራውና ለአስርታት በአለመረጋጋት ውስጥ የምትገኘው የሶማሊያ መንግሥት የኢትዮጵያ ሠራዊት አባል በሆነበት በአፍሪካ ኅብረት የሠላም አስከባሪ ኃይል የሚደገፍ ነው።
የኢትዮጵያ የቅርብ ወዳጅ በነበሩት በቀድሞው የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ የሥልጣን ዘመን ከግብፅ ጋር የነበረው ግንኙነት ቀዝቃዛ የነበረ ሲሆን፣ የሰሞኑ የካይሮ ጉብኝትም ይህንን ግንኙነት ለማደስ እንደሆነ ይታመናል።
ከዚህ ቀደም የነበሩት የሶማሊያ መሪዎች ኢትዮጵያና ግብፅ ከሚወዛገቡበት የሕዳሴው ግድብ አንጻር እንደ አሁኑ በይፋ አቋማቸውን ሳይገልጹ ቆይተዋል። ይልቁንም ከኢትዮጵያ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ስላላቸው በግድቡ ጉዳይ ላይ ከመናገር ተቆጥበው ቆይተዋል።
ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ሲጠበቁ የነበሩት አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ወደ አዲስ አበባ ሳይሄዱ ቀርተዋል።
ከዚያ ይልቅ ወደ ግብፅ አምርተው ከፕሬዝዳንት አል ሲሲ ጋር የሁለትዮሽና አካባቢ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ተገልጿል።
በዚህ ውይይት ላይ በሁለቱ ፕሬዝዳንቶች ስለታላቁ ሕዳሴ ግድብ በተሰነዘረው ሃሳብ ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም።












