የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ስለ ሰላም ድርድሩ ለመነገጋገር ወደ ኢትዮጵያ ሊያቀኑ ነው

የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር

የፎቶው ባለመብት, Goobjog News

የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር የርስ በርስ ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት ሊደረግ የታሰበው የሰላም ድርድር ላይ ለመወያያት ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ መሆኑን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስታወቀ።

ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ከዛሬ ሐምሌ 17- ሐምሌ 25 2014 ዓ.ም ኢትዮጵያን ጨምሮ በግብፅ፣ በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ጉብኝታቸውን ያደርጋሉ።

ማይክ ሐመር በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው በኢትዮጵያ መንግሥት እና በትግራይ ባለስልጣናት መካከል ሊደረግ የታሰበውን የሰላም ድርድር ወደፊት ለማራመድ የሚደረገውን ጥረት የመገምገም እድል እንደሚኖራቸው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በትናንትናው ዕለት ሐምሌ 16፣ 2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ማይክ ሐመር በኢትዮጵያ ቆይታቸው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ያለበትን ሁኔታ መገምገም እንዲሁም በጦርነቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ አካላት ተጠያቂ ማድረግን በተመለከተም እንደሚመክሩ መግለጫው አመላክቷል።

በኢትዮጵያ የተከሰተውን የርስ በርስ ጦርነት መከሰቱን ተከትሎ በአሜሪካ ሶስተኛ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ በመሆን በግንቦት ወር መጨረሻ የተሾሙት ማይክ ሐመር ይህ ጉብኝታቸው ለሁለተኛ ጊዜ የሚደረግ ነው።

ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ በነበረው በባለፈው ጉብኝታቸው ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር መነጋገራቸው ይታወሳል።

“አሜሪካ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሁሉም ህዝቦች ዘላቂ ሰላም፣ ደህንነት እና ብልፅግና ለማምጣት ያስችል ዘንድ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ሂደትን መደገፍ እና ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ለማራመድ ቁርጠኛ ነች” ይላል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ

ከሰሞኑ የትግራይ አመራሮች ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት ለሚደረገው ድርድር የሰላም ቡድን መቋቋሙን ማስታወቃቸው ይታወሳል።

 በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራው ሰባት አባላት ያሉት የመንግሥት ተደራዳሪ ኮሚቴ ስራ መጀመሩን መግለጹ ይታወሳል።

ሁለቱ አካላት ለሰላም ድርድሩ ያላቸውን ፍላጎት ቢገልጹም ውይይቱ መቼ ይጀመር፣ የትስ ቦታ ነው በሚለው ላይ የተባለ ነገር የለም።

ከትግራይ ክልል በኩል በአማራ ክልል ዘንድ የይገባኛል ጥያቄ ያለበትና በአሁኑ ወቅት በአማራ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ያለው ምዕራብ ትግራይ እንዲሁም ከአመት በላይ የተቋረጡ የመሰረተ ልማቶች ጥያቄ ለድርድር እንደማይቀርቡ የተናገሩ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት በነዚህ ጉዳዮች ላይ ምንም ያለው ነገር የለም።

ልዩ መልዕክተኛው ከርስ በርስ ጦርነቱ በተጨማሪ ስለ ታላቁ ህዳሴ ግድብም ይነጋገራሉ ተብሏል።

ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ወደ ግብፅ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የሚያቀኑ ይሆናል።

ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በሚወዛገቡበት ጉዳይ ላይ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ ለማምጣት የአሜሪካ ድጋፍ እንደሚያደርጉ መግለጫው የጠቀሰ ሲሆን ይህም የሁሉንም አካላት ፍላጎት በሚያረካ መልኩ ነው ተብሏል።

 በአዲስ አበባ ቆይታቸውም አምባሳደር ሐመር የሶስትዮሹን ድርድር ሲመራ ከነበረው የአፍሪካ ህብረትም ጋር እንደሚመክሩ ተገልጿል።

አምባሳደር ማይክ ሐመር ከሳምንት በፊት ሐምሌ 12፣ 2014 በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ከሆኑት ዶ/ር ስለሺ በቀለም ጋር ህዳሴ ግድብን ጨምሮ መወያየታቸው ተገልጿል።

የ X ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

የ X ይዘት መጨረሻ

የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ስለሺ በቀለ ሐምሌ 12፣ 2014 ዓ.ምከልዩ መልዕክተኛው ጋር መነጋገራቸውን ባሰፈሩበት የትዊተር ገጻቸው ሰላሙን አስመልክቶ በኢትዮጵያ መንግሥት እየተወሰደ ስላለው እርምጃ፣ ብሄራዊ ምክክር፣ በጦርነትና በድርቅ በተጠቁ አካባቢዎች ስላለው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ማስረዳታቸውን ማስረዳታቸውን ገልጸዋል።

ለአምስት ወራት ያህል በልዩ መልዕክተኝነት ቦታው ላይ የቆዩት አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድን የተኩት አዲሱ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር በዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ቺሊ ውስጥ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው የሰሩ ሲሆን፣ በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት እና በዋይት ሐውስ ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግለዋል።