ሕዳሴ የግድብ 3ኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, FANA
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ተጠናቆ በግድቡ አናት ላይ ውሃ መፍሰስ መጀመሩ ተገለጸ።
የ3ኛው ዙር የግደቡ የውሃ ሙሌት መጠናቀቁን ተከትሎ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ እና ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት በስፍራው ተገኝተዋል።
ባለፉት ሁለት የክረምት ወቅቶች የመጀመሪያው እና ሁለተኛው የግድቡ የውሃ ሙሌት መካሄዱ ይታወሳል።
የ3ኛው ዙር የግደቡ የውሃ ሙሌት መጠናቀቁ የተገለጸው ትናንት ነሐሴ 5/2014 ዓ.ም. የሁለተኛው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ተርባይን ሥራ መጀመሩ ከተገለጸ በኋላ ነው።
ትናንት ኃይል ማመንጨት የጀመረው የግድቡ 2ኛው ተርባይን ዩኒት ዘጠኝ የተባለው ሲሆን 270 ሜጋ ዋት የአሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም አለው ተብሏል።
የካቲት 2014 ዓ.ም. ወደ ሥራ የገባው ዩኒት 10 ተርባይን በተመሳሳይ 270 ሜጋ ዋት ሃይል የማመንጨት አቅም እንዳለው ተገልጿል። በዚህም መሠረት ሁለቱ ኃይሎች በድምሩ 540 ሜጋ ዋት የአሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳላቸው ተመልክቷል።
የግድቡ ግንባታ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ የግድቡ የሲቪል ሥራዎች ግንባታ 95 በመቶው መጠናቀቁን የገለጹ ሲሆን፤ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች ግንባታና እና ተከላ ወደ 61 በመቶ ከፍ ማለቱንና የውሃ ማስተላለፊያ የብረታ ብረት ሥራዎችን ደግሞ 73 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።
ዋና ሥራ አስኪያጁ የግድቡ ሁለተኛው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ተርባይን ኃይል የማመንጨት ሥራን ለማስጀመር በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር የግድቡ አጠቃላይ የግንባታ ሥራ 83.3 በመቶ ደርሷል ብለዋል።
ግንባታው ሲጠናቀቅ በአፍሪካ ግዙፉ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ እንደሚሆን የሚጠበቀው የሕዳሴ ግድብ ከፍታው 145 ሜትር ሲሆን፤ ርዝመቱ ደግሞ 1 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ነው።
ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ፈሶበት ከአምስት ሺህ በላይ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል የተባለው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአካባቢው አገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።
የግንባታው መሠረተ ድንጋይ መጋቢት 24/2003 ዓ.ም የተጣለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ በስተምዕራብ ከሱዳን ጋር በምትዋሰንበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በጉባ ወረዳ እየተገነባ ይገኛል።












