በአልኮል መጠጥ መመረዝ 12 ኡጋንዳውያን ለሞት ተዳረጉ

በአንድ ጎጆ ኢንዱስትሪ ውስጥ የተመረተ የአልኮል መጠጥ የጠጡ አስራ ሁለት ሰዎች ኡጋንዳ ውስጥ ሕይወታቸው ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ።
በሰሜን ምዕራብ ኡጋንዳ ውስጥ በምትገኘው ማዲ-ኦኮሎ ወረዳ ውስጥ የሰዎቹ ሞት የተከሰተው ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ቅዳሜ እና እሁድ መሆኑን ተገልጿል።
በአነስተኛ አምራች አማካይነት የተጠመቀ አረቄን ጠጥተው ለሞት ተዳርገዋል ተብሎ የተጠረጠሩትን የአስራ ሁለቱን ሰዎች የሞት ምክንያት በትክክል ለማወቅ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል።
ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪም በአናናስ ጣዕም የተዘጋጀ ነው የተባለውን የአልኮል መጠጥ ሲሸጥ ነበር የተባለ አንድ ነጋዴን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በመመረዝ ምክንያት ሆስፒታል ገብተዋል።
ለሰዎቹ ሞትና ሆስፒታል መግባት ምክንያት የሆነው መጠጥ በውስጡ ምን እንደያዘ የታወቀ ነገር የለም፤ ነገር ግን በጠርሙሱ ሽፋን ላይ “የተጣራ ውሃ፣ አልኮል እና የአናናስ ጣዕም” እንደተጨመረበት የሚገልጽ ጽሑፍ ሰፍሮበታል።
የአካባቢው ፖሊስ ቃል አቀባይ እንዳሉት ከአረቄው ላይ ናሙናዎች እንደተሰበሰቡ እና በመንግሥት ቤተ ሙከራ ውስጥ ምርመራ እንደሚደረግበት ገልጸዋል።
ሞትና ጉዳትን ካስከተለው ከዚህ መጠጥ ጋር በተያያዘ አራት ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፣ መጠጡ የተመረተበት የጎጆ ኢንዱስትሪ ተዘግቶ ምርመራ እየተካሄደበት ነው።
ከተለያዩ ነገሮች ጋር ተቀላቅሎ ከሚሰሩ የእልኮል መጠጦች ምክንያት በኡጋንዳ ውስጥ የሰው ሕይወት መጥፋት በተደጋጋሚ ያጋጥማል።
ከሁሉ የከፋው ከ12 ዓመት በፊት በደቡብ ምዕራብ ኡጋንዳ ውስጥ ሜታኖል ከተባለ ኬሚካል ጋር ተቀላቅሎ በተዘጋጀ መጠጥ ቢያንስ 80 ሰዎች ሞተው እንደነበር ባለሥልጣናት ገልጸዋል።
ተመሳሳይ ሁኔታ ከኡጋንዳ ባሻገር፣ በኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ በደቡብ አፍሪካና በሌሎች በርካታ የአፍሪካ አገራት በተደጋጋሚ በአልኮል መመረዝ የሰው ሕይወት ያልፋል።












