የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ የአልጀርስ ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ ወሰነ

የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ለሃያ ዓመታት ኢትዮጵያና ኤርትራን በጦርነት ውስጥ ተፋጠው እንዲቆዩ ላደረጋቸው የድንበር ፍጥጫ መፍትሄ ይሰጣል የተባለውን የአልጀርስ ስምምነትን እንደሚቀበል አሳውቋል።
ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ከዚህ በተጨማሪም ወሳኝ የሚባሉ ኢኮኖሚያዊና ውሳኔዎችን አሳልፏል።
በዚህም መሰረት ለሦስት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በመንግሥት ብቸኛ ቁጥጥር ስር የነበሩ እና በግንባታ ላይ ያሉ ማምረቻ እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ወደ ግል ባለቤትነት እንዲዘዋወሩ ወስኗል።
በዚህም መሰረትም የኢኮኖሚ ዕድገቱ ዜጎችን አካታች ሆኖ እንዲቀጥል የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች በትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ የአክስዮን ድርሻ እንዲኖራቸውም ወስኗል።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም እውቀትና የውጭ ምንዛሪ ካፒታል ያላቸው የውጭ ባለሃብቶች ተገቢውን አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ ለማስቻል
• በመንግሥት ይዞታ ሥር ያሉ በማምረት ወይም አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙትም ሆነ በግንባታ ላይ የሚገኙ የባቡር፣ የስኳር ልማት፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የሆቴልና የተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በአክሲዮን ሽያጭ ወደ ግል ዘርፍ እንዲተላለፉ
• እንዲሁም የኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች እና የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት ትልቁን የአክስዮን ድርሻ መንግሥት ይዞ ቀሪው አክሲዮን ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ባለሃብቶች እንዲተላለፍ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮ-ኤርትራ ወቅታዊ ሁኔታን በጥልቀት በመገምገም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ተፈጥሮ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃና በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር ጥሪ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የአልጀርሱን ስምምነት እና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ የወሰነና ለተግባራዊነቱ ያለማመንታት በቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑንም ገልጿል።
የኤርትራ መንግሥትም ተመሳሳይ አቋም በመውሰድ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ የሰላም ጥሪውን ተቀብሎ ከዚህ በፊት የነበረውን አብሮነትና ሰላም ወደነበረበት ለመመለስና በቀጣይም ዘላቂነቱን ለመጠበቅ ለተግባራዊነቱ ያለማመንታት በቁርጠኝነት እንዲሰራ ጥሪ አቅርቧል።












