እየተበላሸ ያለው የኢትዮጵያ እና የምዕራባውያን ግንኙነት

ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ መቀለ ትግራይ ውስጥ ሰዓት እላፊ ጥሷል ተብሎ በተገደለ ወጣት የተሰማውን ሐዘን የሚገልጽ ወጣት

የፎቶው ባለመብት, AFP

    • ፀሐፊ, ፋሩክ ቾቲያ
    • የሥራ ድርሻ, ቢቢሲ ኒውስ

የኢትዮጵያ መንግሥት ከአሜሪካና ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ያለው ግንኙነት በተቀዛቀዘበት በአሁኑ ወቅት ከትግራይ አማጺያን የተከፈተበትን ጥቃት ለማሸነፍ ሌሎች ወዳጆችን እየፈለገ ነው።

አሜሪና የአውሮፓ ሕብረት፣ በመንግሥትና በህወሓት መካከል እየተካሄደ ያለውና አገሪቱን ሊበታትናት ይችላል ብለው አንዳንዶች የሚሰጉት ጦርነት እንዲቆም ጫና ለመፍጠር በሁለቱም ላይ ማዕቀብ እንደሚጥሉ አስጠንቅቀዋል።

ይህም መንግሥት ትኩረቱን ወደሌሎች እንዲያዞር እንዳደረገው ኖርዌይ ውስጥ በሚገኘው የኦስሎ ኒው ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በግጭቶች ጥናት ላይ የሚያስተምሩት ሸትል ትሮንቮል ይናገራሉ።

"የኢትዮጵያ መንግሥት የጦር መሳሪያ ከኢራን፣ ከቱርክ እና ከቻይና፣ የገንዘብ ብድር ከሳዑዲ አረቢያ እና ከዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ እንዲሁም ፖለቲካዊ ድጋፍ ደግሞ ከሩሲያና ከቻይና በማግኘት ከምዕራባዊያን ውጪ የሚፈልገውን ማድረግ እንደሚችል ይሰማዋል" በማለት ሩሲያና ቻይ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በጦነቱ ላይ የቀረበን የውሳኔ ሃሳብን መቃወማቸውን እንደምሳሌ ያነሳሉ።

ጨምረውም ምንም እንኳን ይፋዊ ማረጋገጫ ባይኖርም የኢትዮጵያ ሠራዊት በአማጺያኑ ላይ የበላይነትን ለመያዝ ኢራንና ቱርክ ሰራሽ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ማግኘቱን ታማኝ ሪፖርቶች እንዳሉ ትሮንቮል ተናግረዋል።

ቁልፍ የደኅንንት አጋር

መቀመጫቸውን ካናዳ ያደረጉት የኢትዮጵያ ጉዳዮች ተንታኝ አን ፊትዝ-ጄራልድ አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ "የቅጣት እርምጃ" ለመውሰድ መዘጋጀታቸው እንዳሳሰባቸው ይናገራሉ።

"ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከሕጋዊው የኢትዮጵያ መንግሥት እና በጦርነቱ ከተጎዱት ከትግራይ፣ ከአማራ እንዲሁም ከአፋር ክልሎች ጋር ነው መቆም ያለበት። በህወሓት በተፈጸሙ ጭፍጨፋዎች ላይ በማተኮር መሳሪያውን እንዲያስቀምጥ ጥሪ ማቅረብ አለባቸው" ይላሉ ፕሪፌሰር ፊትዝ-ጄራልድ።

አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን በመጡበት ጊዜ "የቅርብ ስልታዊ አጋር" አድርገው ነበር የተመለከቷቸው።

በወሳኙ የመርከቦች መተላለፊያ ቀይ ባሕር፣ የአስላማዊ እንቅስቃሴ ማዕከል እና ወደ አውሮፓ የሚጓዙ ስደተኞች ዋነኛ ምንጭ በሆነው አካባቢ የምትገኘው ኢትዮጵያን ደግሞ "ቁልፍ የደኅንነት አጋር" አድርገው ይመለከቱ እንደነበር ፕሮፌሰር ትሮንቮል ይናገራሉ።

"ጦርነቱ ሲጀምር ግንኙነታቸው በመበላሸቱ አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት በመንግሥት የሚፈጸሙ ጭፍጨፋዎችን እና ትግራይ ውስጥ ያለውን የረሃብ ሁኔታ አጥብቀው መተቸት ጀመሩ" ይላሉ ትሮንቮል።

የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣናት በትግራይ ክልል ላይ መንግሥት በጣለው ይፋዊ ያልሆነ ዕገዳ ሳቢያ የእርዳታ አቅርቦት በመስተጓጎሉ 400 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች በረሃብ መሰል ሁኔታዎች እንደሚገኙ ይናገራሉ።

ተቀማጭነታቸው አሜሪካ የሆኑት የአፍሪካ ቀንድ ተንታኙ ፋይሳል ሮብሌ እንደሚሉት የኢትዮጵያ መንግሥት አቋሙን የማያለዝብ ከሆነ፣ ምዕራባውያን በሱዳን በኩል የእርዳታ መተላለፊያ ሊያዘጋጁ ወይም በትግራይ ክልል ላይ ከበረራ ነጻ ሆነ ቀጠና በማወጅ ምግብና መድኃኒት በአውሮፕላን ለማቅረብ ሊያስቡ ይችላሉ ይላሉ።

ምዕራባውያን በመንግሥት ላይ የሚያሳድሩትን "የእርዳታ ኢምፔሪያሊዝም" የሚሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት የዓለም አቀፍ ግንኑነት ምሁሩ ውሂበእግዜር ፈረደ (ዶ/ር) "ያልተገራ" የዲፕሎማሲ ጫና በመቃወም ያስጠነቅቃሉ።

ጨምረውም የፌደራል መንግሥቱ በትግራይ ክልል ውስጥ ያልተገደበ እንቅስቃሴ እንዲያደረግና ለሕዝቡ እርዳታ እንዲያቀረብ ለማስቻል ግፊቱ በህወሓት ላይ መሆን አለበት ይላሉ።

"የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሙሉ ትኩረት በትግራይ ላይ ብቻ መሆን የለበትም" የሚሉት ውሂበእግዜር የህወሓት ጥቃት ሰብአዊ ቀውስ ባስከተለባቸው አጎራባቾቹ የአማራና የአፋር ክልሎች ላይ ጭምር መሆን አለበት ብለዋል።

አማራ ክልል ጭና ውስጥ ከተፈጸመ ጭፍጨፋ በኋላ የአርዳታ ዱቄት የተሰጣት ሴት ጥቅምት 2014

የፎቶው ባለመብት, AFP

የዲፕሎማሲ ግንኙት

ባለፈው ዓመት ነሐሴ ላይ የአውሮፓ ሕብረት የፖሊሲ ጉዳዮች ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል በተባበሩት መንግሥታት የሚደረገው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ምርመራ ከተጠናቀቀ በኋላ በግጭቱ ተሳታፊ ቡድኖች ላይ ማዕቀብ እንደሚጥል፤ ነገር ግን ሕብረቱ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው የልማት ድጋፍ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

"የጦር ወንጀሎችን እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን እንደ ጦር መሳሪያ በሚጠቀሙ የታጠቁ ቡድኖች አማካይነት ትግራይ ውስጥ ስልታዊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽሟል" ብለዋል።

ፕሬፌሰር ትሮንቮል የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የጆ ባይደን አስተዳደር በሚከተሉት እርምጃዎች በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ግፊቱን እያጠናከረ ነው ይላሉ፡

• ትግራይ ውስጥ የዘር ማጥፋት መፈጸም አለመፈጸሙን "ሕጋዊ ምርመራ" እንዲደረግ በማዘዝ

• የዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለኢትዮጵያ ከሚሰጡት ብድር የተወሰነውን እንዲይዙ በመጠየቅ እና

• ምርታቸውን ከቀረጥ ነጻ ወደ አሜሪካ ከሚልኩ የአፍሪካ አገራት ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያን ለማስወጣት መታሰቡ ከባድ ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ ጉዳትን በመንግሥት ላይ ያስከትላል።

"ጦርነት ሲኖርና እንዲቆም ግፊት ሲደረግ ተደማጭነትን ለማግኘት ኢትዮጵያ በአሜሪና በአውሮፓ ያላትን ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ታጠናክር ነበር አሁን እየሆ ያለው ግን የዚህ ተቃራኒ ነው" ይላሉ ፕሮፌሰር ትሮንቮል።

ለዚህም በአባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ በምትገነባው ግድብ ምክንያት እየተወዛገበቻት ያለችውን ግብፅን ጨምሮ መንግሥት 30 የሚደርሱ የዲፕሎማቲክ ሚሽኖችን ለመዝጋትና ደረጃቸውን ዝቅ ለማድረግ መወሰኗን በማሳያነት ይጠቅሳሉ።

"ኢትዮጵያ ረጅም እድሜ ያለውና ጠንካራ የዲፕሎማቲክ አባላት ካላቸው የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ነበረች፤ ነገር ግን ይህ አሁን ባለው መንግሥት ስር እየተቀየረ ነው" ይላሉ ትሮንቮል።

በዩናይትድ ኪንግደም ነዋሪ የሆኑት የአፍሪካ ቀንድ ተንታኙ አብዱራህማን ሰይድ ግን የመንግሥት እርምጃ ወጪን ለመቀነስ ፊቱን ወደ "ዲጂታል ዲፕሎማሲ" ማዞሩን የሚያመላክትና የአገሪቱን የዲፕሎማሲ ሚሽኖች ከህወሓት ደጋፊዎች "ለማጽዳት" ነው ይላሉ።

"ምዕራባውያን አገራት ኢትዮጵያን አልተረዷትም። መንግሥት ላይ ማዕቀብ እንደሚጥሉ በማስፈራራት ህወሓትን እያደፋፈሩ ነው" በማለት አብዱራህማን ይናገራሉ።

"የፌደራል መንግሥቱ በሉዓላዊ ግዛቱ ላይ ያለውን ሥልጣን ካከበረው ከአፍሪካ ሕብረት ትምህርት መውሰድ ያስፈልጋቸዋል" በማለት ይመክራሉ።

በአውሮፓ ሕብረት እና በአሜሪካ በኩል እየተደረገ ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግፊት መንግሥታና ህወሓት በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር የተኩስ አቁም ስምምነት አድርገው የሰላም ድርድር እንዲየደርጉ ያለመ ነው ይላሉ ፕሮፌሰር ትሮንቮል።

የኖቤል የሰላም ተሸላሚው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንደእርሳቸውም የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት የቀድሞዋ የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ የተካተቱበት የሕብረቱ የመልዕክተኞች ቡድን ተኩስ አቁም እንዲደረግ ያደረገውን ጥረት ሳይቀበሉት በመቅረታቸው፤ አሁን ደግሞ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆን ልዩ መልዕክተኛው አድርጎ ሰይሟል።

ህወሓት የትኛውንም አይነት የሰላም ድርድር ጥረት እንደተቀበለ የሚገልጹት ትሮንቮል "በኦባሳንጆ ላይ ግን በተለያዩ ምክንያቶች ጥርጣሬ አለው" ይላሉ።

"ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኦባሳንጆን የልዩ መልዕክተኝነት ሹመት የተቀበሉት ቢሆንም፣ አስካሁን ለሰላማዊ ሂደት እራሳቸውን ዝግጁ አላደረጉም" በማለት ትሮንቮል ያክላሉ።

በአውሮፓ ሕብረትና በአሜሪካ መንግሥታት ውስጥ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የነበሩት አሌክስ ሮንዶስ እና ማርክ ሜዲሽ 'ፖለቲኮ' በተባለው መጽሔት ላይ በጋራ ባወጡት ጽሁፍ ላይ ሰላም ለማምጣት የሚደረገው ጥረት ካልተፋጠነ ኢትዮጵያ የዩጎዝላቪያ ዕጣ ሊገጥማት እንደሚችልና ውጤቱም ከፋ እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል።

ሁለቱ ግለሰቦች "ይህንን ቀውስ ለመፍታት ከ25 ዓመታት በፊት ደም አፋሳሹን የቦሲኒያን ጦርነት ለማስቆም ከተደረገው ዲፕሎማሲና ሽምግልና ያልተናነሰ ጥረትን ይፈልጋል" ሲሉ ጽፈዋል።

የአፍሪካ ቀንድ ተንታኙ አብዱራህማን ሰይድ ግን ትኛውም አይነት የሰላም ሂደት ባለው የመሳካት ዕድል ላይ ጥርጣሬ አላቸው።

ምክንያቱም "የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁልጊዜም የአሸናፊና የተሸናፊ ፖለቲካ ነው። አንደኛው ወገን ሌላኛውን አሸንፎ መውጣት አለበት" ይላሉ።