ዶናልድ ትራምፕ ከፍተኛ ዝና እያገኙ ያሉትን የፍሎሪዳ ገዥ አብጠለጠሉ

ለትራምፕ ፈተና ይሆናሉ የተባሉት ሮን ዴሳንቴስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ለትራምፕ ፈተና ይሆናሉ የተባሉት ሮን ዴሳንቴስ

የአጋማሽ ምርጫ ውጤትን ተከትሎ ዶናልድ ትራምፕ እንደ አዲስ አነጋጋሪ ሆነው ብቅ ብለዋል።

ትራምፕ ያቀረቧቸው በርካታ የሪፐብሊካን እጩዎች ያልተጠበቀ ሽንፈት ካጋጠማቸው በኋላ አንዳንድ የሪፐብሊካን አባላት በዶናልድ ትራምፕ ላይ ጥያቄ እያነሱ ነው።

ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው 'እኔ የመለመልኳቸው እጩዎች ድል ካደረጉ መወደስ ያለብኝ እኔ ነኝ፤ ከተሸነፉ ግን መወገዝ ያለባቸው እነርሱ ራሳቸው ናቸው' ብለዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በፍሎሪዳ ለአገረ ገዥነት የተወዳደሩት ሪፐብሊካኑ ሮን ዲሳንቴስ ታይቶ በማይታወቅ ብልጫ ማሸነፋቸው ዶናልድ ትራምፕን ሊያስደስት ሲገባ ብስጭት ውስጥ ጥሏቸዋል።

‘ብልሁ ትራምፕ’ እያሉ ሚዲያዎች የሚጠሯቸው ሪፐብሊካኑ ሮን ዲሳንቴስ የአሜሪካዊያንን ልዩ ትኩረት ማግኘታቸው ነው ዶናልድ ትራምፕን ያበሳጨው።

ትራምፕ ስለ ዲሳንቴስን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት ‘ሰውዬው ያን ያህልም ነው’ ብለዋል።

ዲሳንቴስ ዕድሜያቸው ገና 44 ዓመት ሲሆን በ2024 ለአሜሪካ ፕሬዝዳንትነት ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ይህ ሰውዬው እያገኙ ያሉት አድናቆት ሳያውካቸው አልቀረም።

‘እሱን እኮ ሰው ያደረኩት እኔ ነኝ፤ ገንዘብም ችሎታም አልነበረውም፤ በሚያሳዝን ሁኔታ ላይ ነበር፤ ይሁንታን ሰጠሁት፤ ወዲያውኑ ዝናው ናኘ’ ብለዋል ትራምፕ ዲሳንቴስን በተመለከተ ሲናገሩ።

ጨምረውም፤ ‘ዴሳንቴስ በሕዝብ አስተያየት ዝቅተኛ ነጥብ ነው የነበረው፤ ገንዘብን አልነበረውም፤ ልክ እኔ ይሁንታ ስሰጠው ተነሳ’ ብለዋል።

ትራምፕ በቀጣይ ከሁለት ዓመት በኋላ ለፕሬዝዳንትነት እንደሚወዳደሩ ፍንጭ የሰጡ ሲሆን ''ዴ ሳንቴስ 'እኔም እወዳደራለሁ' ብሎ ካሰበ ‘ብን ብሎ ድራሹ እንዲጠፋ’ አደርጋለሁ ብለዋል።

ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ ለፕሬዝዳንትነት እንደሚወዳደሩ በይፋ ያውጃሉ ተብሎ እየተጠበቀ ሲሆን እርሳቸውን የሚቀናቀን እጩ ከፓርቲያቸው እንዲመጣ ግን አይሹም።

ዴሳንቴስ ባላንጣ ሆነው የታዮዋቸውም ለዚሁ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሪፐብሊካኖች ማክሰኞ በተደረገው የአጋማሽ ምርጫ ሁለቱን ምክር ቤቶች በሰፊ ልዩነት 'በቀይ ማዕበል' ያጥለቀልቁታል ተብሎ ተጠብቆ የነበረ ሲሆን ይህ ሳይሆን በመቅረቱ በርካታ የሪፐብሊካን አባላት ትራምፕ ላይ ደስተኛ አልሆኑም።

እስከሁን ባለው የአጋማሽ ምርጫ ውጤት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤትን በተመለከተ ከመቶ መቀመጫዎች ሪፐብሊካኖች 49 ሲያሸንፉ፣ ዲሞክራቶች 48 አሸንፈዋል።

ከዚህ በኋላ የሚጠበቁት የጆርጂያ፣ አላስካ፣ ነቫዳና አሪዞና ውጤቶች ናቸው።

ሪፐብሊካኖች ሴኔትን ለመቆጣጠር 51 መቀመጫን መያዝ ይኖርባቸዋል።

በጆርጂያ ግዛት እጩዎች ከ50 በመቶ በላይ ድምጽ ማግኘት ስላልቻሉ ሊለይላቸው አልቻለም፤ ከአራት ሳምንታት በኋላ ድጋሚ ምርጫ ይደረጋል።

የታችኛው ምክር ቤት ግን በሪፐብሊካን መያዙ ከወዲሁ እርግጥ እየሆነ መጥቷል።

ለጊዜው ቆጠራ ባያልቅም 210 ወንበሮች በሪፐብሊካን፣ 200 ወንበሮች ደግሞ በዲሞክራቶች ተይዘዋል።

ይህን ምክር ቤት ለመቆጣጠር ደግሞ አንድ ፓርቲ 218 መቀመጫዎችን ማሸነፍ አለበት።

የታችኛው ምክር ቤት በሪፐብሊካን መያዝ ጆ ባይደን በርካታ አሳካቸዋለሁ ያሏቸውን ውጥኖች መና ሊያስቀርባቸው ይችላል።

ጆ ባይደን በቀጣይ ለሁለተኛ ጊዜ ለፕሬዝዳንትነት እንደሚወዳደሩ ተጠይቀው ‘ማየት ነው እንግዲህ’ የሚል አውንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል።

በርካታ ዲሞክራቶች በ2024 የአሜሪካ ምርጫ ከዴሳንቴስ ይልቅ ዶናልድ ትራምፕ እጩ ቢሆኑ ይመርጣሉ።

ይህም የሆነው ዶናልድ ትራምፕ ዝቅ ያለ ድጋፍ ያላቸው ሰው መሆናቸው፣ ያልተዘጉ ክሶች ስላሉባቸው መሸነፋቸው አይቀርም በሚል ነው።

ሮን ዴሳንቴስ ግን ከፍተኛ ስም እየገነቡ መምጣታቸው ልክ ለትራምፕ የጎን ውጋት እንደሆኑባቸው ሁሉ ለዲሞክራቶችም ራስ ምታት ሆነዋል።

 ሮን ዴሳንቴስ በፍሎሪዳ ለገዥነት ሲወዳደሩ ተቀናቃኛቸውን በ40 ዓመታት ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ልዩነት ነው ማሸነፍ የቻሉት።