በመቀለ ከተማ ከአንድ ዓመት በኋላ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተመለሰ

የፎቶው ባለመብት, DT
የትግራይ ክልል መዲና መቀለ ከአንድ ዓመት በኋላ የኤሌከትሪክ አገልግሎት አገኘች።
የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደገለጹት ከትናንት ማክሰኞች ኅዳር 26/2015 ዓ.ም. ጀምሮ በከተማዋ የኤሌክትሪክ አግልግሎት ተመልሷል።
የእርስ በእርስ ጦርነቱን ተከትሎ መዲናዋን ጨምሮ አብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች መብራት፣ ስልክ፣ ኢንተርኔት እና ባንክን የመሳሰሉ መሠረታዊ አገልግሎቶች ተቋርጦባቸው ቆይቷል።
ይሁን እንጂ የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት ጦርነቱን በማስቆም የሰላም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ በክልሉ የመሠረተ ልማቶች መልሶ ግንባታ እንቅስቃሴዎች እንደተጀመሩ ተገልጿል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ደም አፋሳሽ ጦርነት ያካሄዱት ሁለቱ ተዋጊ ኃይሎች በደረሱት ስምምነት መሠረት ህወሓት ትጥቅ ሊፈታ የተስማማ ሲሆን የፌደራሉ መንግሥት ደግሞ መሠረተ ልማቶችን የመመለስ እና ሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ የበኩሉን ለመወጣት ኃላፊነት ወስዷል።
ከኤሌክትሪክ አገልግሎት በተጨማሪ፣ የኢትዮ-ቴሌኮም የስልክ አገልግሎት በሽረ እንዳሥላሴ እና በአከባቢው የሙከራ ሥራ ጀምሯል።
“በከተማዋ ሁሉም ቦታ ከትናንት (ማክሰኞ) ጀምሮ በሁሉም ቦታ መብራት አለ” ሲል አንድ የከተማዋ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግሯል።
የኢትዮ-ቴሌኮም ቺፍ ኮምንኬሽን ኦፊሰር የሆኑት አቶ መሳይ ውብሸት ከሳምንት በፊት ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ በሽረ እንዳሥላሴ እና አካባቢው የሙከራ ሥራ እየተካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የመቀለ ኤሌክትሪክ መስመር ከብሔራዊ መቆጣጠሪያ ማዕከል ግሪድ ጋር መገናኘቱን ትናንት አስታውቆ ነበር።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበኩሉ፤ የባለሙያዎች ቡድን ለጥገና ሥራ የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ይዞ ወደ ክልሉ በቅርቡ ተሰማርቶ፣ የጥገና ሥራውን በአጭር ግዜ በማጠናቀቅ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲመለስ እንደሚሠራ አስታውቋል።
ከነገ ጀምሮ ለጥገና ሥራው የሚያስፈልጉ ግብአቶችን በማሟላት፣ ሠራተኞቹ ከሰሞኑ ወደ ክልሉ እንደሚሰማሩና በአጭር ጊዜ የጥገና ሥራውን በማጠናቀቅ የተቋረጠውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ኅብረተሰቡ መልሶ እንደሚያገኝ አክሏል።
በቅርቡ በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ዘላቂ ግጭት የማቆም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የንግድ በረራዎችን መልሶ ለመጀመር ሙሉ ዝግጀቱን እንዳጠናቀቀ የአየር መንገዱ የንግድ ዘርፍ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ለማ ያደቻ ከሳምንት በፊት ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ለሁለት ዓመታት የተካሄደው የሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በእርስ ጦርነት በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ካስከተለው ሰብአዊ ጥፋት ባሻገር ከፍተኛ የንብረት ውድመት አስከትሏል።












