ጀርመን ውስጥ መፈንቅለ መንግሥት ለመፈጸም አሲረዋል የተባሉ 25 ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

የጀርመን ፖሊስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፖሊስ በመላዋ ጀርመን ባካሄደው ዘመቻ መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ እያሴሩ ነበሩ የተባሉ 25 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነገረ።

የጀርመን መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከሆነ ቀኝ ዘመም ፖለቲከኞች እና የቀድሞ የጦር አባላት ሪችስታግ የተባለውን የአገሪቱን ምክር ቤት ሕንጻ በኃይል በመያዝ የመንግሥትን ሥልጣን ለመቆጣጠር አሲረው ነበር ተብሏል።

የዚህ ያልተጠበቀ ሴራን በማቀናበር ሄንሪች 8ኛ የተባለው የ71 ዓመት ግለሰብ ዋነኛ ተዋናይ መሆኑም በስፋት ተዘግቧል።

እንደ የጀርመን ዐቃቤ ሕግ ከሆነ ይህ ግለሰብ መፈንቅለ መንግሥት ሲያሴሩ ከነበሩ ሁለት ዋነኛ ግለሰቦች መካከል አንዱ መሆኑን ገልጿል።

23ቱ ሰዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት ጀርመን ካሏት 16 ግዛቶች በ11ዱ ውስጥ ነው። ሁለት ተጨማሪ ሰዎች ደግሞ በኦስትሪያ እና ጣሊያን ከሴራው ጋር በተገናኘ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል የጽንፈኛው ሪችስበርገር ንቅናቄ አባላት ይገኙበታል። የዚህ ንቅናቄ አባላት ኃይል በተቀላቀለባቸው ጥቃቶች እና ከዘረኝነት ጋር በተያያዘ ድርጊቶች በጀርምን ፖሊስ ጥብቅ ክትትል ሲደረግባቸው የቆዩ ናቸው።

የመፈንቅለ መንግሥቱ ዋነኛ አቀናባሪ ነው የተባለው የ71 ዓመቱ ሄንሪች

የፎቶው ባለመብት, DPA PICTURE ALLIANCE

የምስሉ መግለጫ, የመፈንቅለ መንግሥቱ ዋነኛ አቀናባሪ ነው የተባለው የ71 ዓመቱ

በግምት 50 የሚሆኑ ሰዎች የዚህ ንቅናቄ አካል የነበሩ ሲሆን፤ አሁን ላይ ያለችውን የጀርመን አስተዳደርን አይቀበሉም።

ዓላማቸውም ያለውን የጀርመን ሪፐብሊክ ሥርዓትን በማስወገድ እአአ 1871 ላይ የነበረውን የጀርመን አስተዳደርን መመለስን ይፈልጋሉ።

“ለዚህ ቡድን እስካሁን መጠሪያ የለንም” ሲሉ የፌደራል መንግሥቱ ዐቃቤ ሕግ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

የጀርመን የፍትሕ ሚኒስትር ማርኮ በሽማን ግዙፍ ፀረ-ሽብር ዘመቻ በመላው አገሪቱ እየተካሄደ እንደሆነ እና “ሕገ-መንግሥታዊ አካላት ላይ ጥቃት” ታቅዶ እንደነበረ በትዊተር ገጻቸው ገልጸዋል።

የአገሪቱ ዐቃቤ ሕግ እንደሚለው ከሆነ ቡድኑ ከእአአ 2021 ጀምሮ ባለፉት 12 ወራት መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ ሲያሴር ቆይቷል።

በጀርመን ጦር ውስጥ ልዩ የኮማንዶ አባላት የነበሩ ግለሰቦችም የመፈንቅለ መንግሥቱ ቁልፍ አካል መሆናቸው ተመላክቷል።

መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ ሲያሴሩ የነበሩት ግለሰቦች ዕቅዳቸውን ከተገበሩ በኋላ፣ ጀርመንን እንዴት ማስተዳደር እንዳለባቸው ዝርዝር ዕቅድ አውጥተው ጨርሰው እንደነበረ ተገልጿል።

የቡድኑ አባላት ዓላማቸውን እውን ማድረግ የሚችሉት “ሰዎችን መግደልን ጨምሮ፣ ኃይል በተቀላቀለበት መንገድ ብቻ ነው” ብሏል የአገሪቱ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ።