ከ2026 የዓለም ዋንጫ ምን ይጠበቃል? የቡድኖች ብዛት፣ ስታዲሞች እና የውድድር ቅርጽ

የሜክሲኮው አዝቴካ ስታዲየም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሜክሲኮው አዝቴካ ስታዲየም

የተጠናቀቀው የዓለም ዋንጫ ኳታር በትንሽ ስፍራ ተካሄደ ውድድር በመሆን በታሪክ ይታወሳል። የ2026ቱ ደግሞ ከዚህ ይለያል።

በኳታር ሁሉም ግጥሚያዎች የተካሄዱት በአንድ ሰዓት ርቀት ውስጥ በሚገኙ ስታዲየሞች ውስጥ ነበር። ቀጣዩ የዓለም ዋንጫ ግን በሦስት አገራት ማለትም በካናዳ፣ በአሜሪካ እና በሜክሲኮ ይካሄዳል።

መጪው የዓለም ዋንጫ 16 ተጨማሪ ቡድኖች የሚሳተፉበት ውድድርም ይሆናል። በዚህም ተጨማሪ ግጥሚያዎች ይከናወናሉ ማለት ነው።

ውድድሩ ከሰኔ 2026 አጋማሽ ጀምሮ በአምስት ሳምንታት ውስጥ ተከናውኖ ይጠናቀቃል።

ውድድሩ በ11 የአሜሪካ፣ በሦስት የሜክሲኮ እና በሁለት የካናዳ ከተሞች ይሰናዳል። ይህም ተጨዋቾች እና ደጋፊዎቻቸው ላይ በሚፈጥረው ጉዞ መጠን ላይ ጥያቄዎችን ያስነሳል።

ቡድኖችን፣ ደጋፊዎችን፣ ጋዜጠኞችን እና የፊፋ ባለሥልጣናትን በሦስቱ አገራት ውስጥ ለማጓጓዝ በርካታ በረራዎች ያስፈልጋሉ።

በ2026 በርካታ ቡድኖች ለምን ይሳተፋሉ?

ፊፋ ቀጣዩን የወንዶች የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ቡድኖችን ቁጥር ከ32 ወደ 48 እያሳደገ ነው።

ይህም በስፖንሰርሺፕ፣ በቁሳቁስ ሽያጭ፣ በትኬት ሽያጭ እና በመገናኛ ብዙኃን ስርጭት ገቢ ተጨማሪ ገንዘብ ይመነጫል። ፊፋ እስከ ኅዳር 2026 ባለው ጊዜ 11 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት አቅዷል።

በሰሜን አሜሪካ የእግር ኳስ ተወዳጅነት እየጨመረ በመምጣቱ በሚቀጥለው የዓለም ዋንጫ ብዙ ተመልካቾች እንደሚገኙ ይጠበቃል።

በሚቀጥለው ውድድር ላይ እስከ 5.5 ሚሊዮን የሚደርሱ ደጋፊዎቸ እንደሚታደሙ ፊፋ ገምቷል። በእያንዳንዱ ጨዋታ በአማካይ 68,000 ተመልካች የታደሙበትን የ1994 ዓለም ዋንጫ 3.6 ሚሊዮን ደጋፊዎች ክብረ ወሰንም ያሻሽላል።

ፊፋ አብዛኛውን ትርፍ የዓለም እግር ኳስ ለማሳደግ እንደሚውል ገልጿል። የሴቶችን እግር ኳስ ማስፋትን ጨምሮ በርካታ ፕሮጀክቶችም ይካሄዳሉ።

በቀጣዩ የዓለም ዋንጫ በርካታ አዳዲስ ተሳታፊ አገራት ከአፍሪካ እና ከእስያ አህጉራት ይካተታሉ።

በ2022ቱ ውድድር ኳታርን ጨምሮ ከሁለቱ ኮንፌዴሬሽኖች የተውጣጡ 11 ቡድኖች ተሳታፊ ነበሩ።

በ2026 ከሁለቱ ኮንፌዴሬሽኖች የተወጣጡ ቢያንስ 17 ቡድኖች ይኖራሉ። ይህ ቁጥር ወደ 19 ሊያድግ ይችላል።

ካናዳ፣ ሜክሲኮ እና አሜሪካን ጨምሮ ቢያንስ ስድስት የኮንካ ካፍ ቡድኖች ለዓለም ዋንጫ የሚያልፉ ሲሆን፣ ፌዴሬሽኑም በጥሎ ማለፍ ጨዋታ ሁለት ቡድኖች ይኖረዋል።

ሮዝ ባውል ስታዲየም
የምስሉ መግለጫ, የ1994 (እአአ) የዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ በአሜሪካ ካሊፎርኒያ፣ ፓሳዲና ውስጥ በሚገኘው በዚህ ሮዝ ባውል ስታዲየም ነበር የተካhደው

የ2026 ጨዋታዎች የት ይከናወናሉ?

ውድድሮች የሚካሄዱባቸው 16ቱ ሜዳዎች በሰኔ ወር ይፋ ሆነዋል። ሁሉም ስታዲየሞች ተገንብተው ተዘጋጅተዋል። አብዛኛዎቹ ትልቅ አቅም ያላቸው ስታዲየሞች ያሉት በአሜሪካ ሲሆን፣ የኤን ኤፍ ኤል ቡድኖች የሚጠቀሙባቸው ናቸው።

አንዳንድ ስታዲየሞች ከ2026 በፊት ማሻሻያ ይደረግባቸዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ ሰው ሠራሽ ሣር በፊፋ የማይፈቀድ በመሆኑ ተፈጥሯዊ ሳር ማንጠፍ ይጠበቅባቸዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ በ2026ቱ ውድድር 80 ግጥሚያዎች ይኖራሉ። ይህም ግን ሊቀየር ይችላል። ዩናይትድ ስቴትስ ከሩብ ፍፃሜው ጀምሮ ያሉትን ጨዋታዎች ጨምሮ 60 ግጥሚያዎችን ታስተናግዳለች። ጎረቤት ካናዳ እና ሜክሲኮ እያንዳንዳቸው 10 ግጥሚያዎችን ያስተናግዳሉ።

ዩናይትድ ስቴትስ እና ሜክሲኮ ከዚህ ቀደም የዓለም ዋንጫን አስተናግደዋል። አብዛኛዎቹ ስታዲየሞች የ2026ዱን አያስተናግዱም። አሜሪካ በ1994 የተጠቀመቻቸውን ስታዲየሞች በድጋሚ አታስተናግድባቸውም።

ሜክሲኮ ግን በ1970 እና 1986 ጨዋታዎችን ያስተናገደውን በሜክሲኮ ሲቲ የሚገኘውን ታዋቂው ኢስታዲዮ አዝቴካ ለሦስተኛ ጊዜ ትጠቀማለች።

የ2026 ስታዲየሞች

ዩናይትድ ስቴትስ/አሜሪካ

  • ኒው ዮርክ/ኒው ጀርሲ (ሜትላይፍ ስታዲየም)
  • ሎስ አንጀለስ (ሶፊ ስታዲየም)
  • ዳላስ (ኤቲኤንድቲ ስታዲየም)
  • የሳን ፍራንሲስኮ የባሕር ወሽመጥ አካባቢ (የሌዊ ስታዲየም)
  • ማያሚ (ሃርድ ሮክ ስታዲየም)
  • አትላንታ (መርሴዲስ-ቤንዝ ስታዲየም)
  • ሲያትል (ሉመን ፊልድ)
  • ሂዩስተን (ኤንአርጂ ስታዲየም)
  • ፊላዴልፊያ (ሊንከን ፋይናንሺያል ፊልድ)
  • ካንሳስ ከተማ፣ ሚዙሪ (አሮውሄድ ስታዲየም)
  • ቦስተን/ፎክስቦሮ (ጂሌት ስታዲየም)

ካናዳ

  • ቶሮንቶ (ቢኤምኦ መስክ)
  • ቫንኩቨር (ቢሲ ፕሌስ ስታዲየም)

ሜክስኮ

  • ጓዳላያራ (ኢስታዲዮ አክሮን)
  • ሜክሲኮ ሲቲ (አዝቴካ ስታዲየም)
  • ሞንቴሬይ (ቢቢቪኤ ባንኮመር ስታዲየም)

ለቀጣዩ የዓለም ዋንጫ የመልክዓ ምድራዊ ስርጭቱ ምን እንደሚመስል እስካሁን ይፋ ባይሆንም ቡድኖች የምድብ ጨዋታቸውን በዞኖች የሚያደርጉ ይሆናል።

ሦስት ዋና ዋና ቦታዎች አሉ። ይህም ለውድድሩ የሚያስፈልገውን ጉዞ ለመቀነስ ይረዳል።

ምዕራባዊ ክልል፡

  • ቫንኩቨር
  • ሲያትል
  • ሳን ፍራንሲስኮ ቤይ
  • ሎስ አንጀለስ
  • ጓዳላያራ

ማዕከላዊ ክልል፡

  • ካንሳስ
  • ዳላስ
  • አትላንታ
  • ሂዩስተን
  • ሞንቴሪይ
  • ሜክሲኮ ሲቲ

ምሥራቃዊ ክልል፡

  • ቶሮንቶ
  • ቦስተን
  • ፊላዴልፊያ
  • ማያሚ
  • ኒው ዮርክ/ኒው ጀርሲ

የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ እንዴት ይዋቀራል?

የመጨረሻው ውሳኔ በፊፋ ምክር ቤት በቀጣዩ የአውሮፓውያን ዓመት ይደረሳል።

የመጀመሪያው አማራጭ 16 ምድቦች እንዲኖሩ ነው። እያንዳንዱ ምድብ ሦስት ቡድኖችን ይይዛል።

የሦስት ቡድኖች ሁለት የምድብ ጨዋታዎችን ያደርጋሉ። የደረጃ ሰንጠረዡን የሚመሩት ሁለት ቡድኖች 32 ቡድኖች ወዳሉበት ዙር ያልፋሉ።

የዚህ መዋቅር መጥፎው ጎን በመጨረሻው ግጥሚያ የሚጫወቱት ሁለቱ ቡድኖች ተያይዘው ለማለፍ የሚያስችል ውጤት ማስመዝገብ መቻላቸው ሊሆን ይችላል።

በ1982 ተመሳሳይ ነገር ተፈጽሟል። ምዕራብ ጀርመን እና ኦስትሪያ ተያይዘው ለማለፍ እና አልጄሪያ እንዳታልፍ ለማድረግ 'የጊዮን ውርደት' የተባለውን ሸፍጥ አድርገዋል ተብለው ይወቀሳሉ።

በ2022 የአራት አገራት የምድብ ድልድል ስኬትን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለ2026 መዋቅሩ እንደገና እንደሚታይ የፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ተናግረዋል።

“ከዚህ የዓለም ዋንጫ የአራት ቡድኖች ስኬት በኋላ ሦስት ቡድኖች ያሉበት 16 ምድቦች ወይም አራት አገራት ያሉበት 12 ምድቦች ይሁን የሚለውን እንደገና ልንመለከት ወይም እንደገና መወያየት አለብን” ብለዋል።

ከዚህ አንጻር ሌላም አማራጭ አለ፤ ይህም የምድብ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት እንዲጠናቀቁ አለማድረግ ነው። ቡድኖቹ በ90 ደቂቃው አቻ ከሆኑ ተጨማሪ ሰዓት ሳያስፈልግ በቀጥታ ወደ መለያ ምት ማምራት ነው።

ሜትላይፍ ስታዲየም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አሜሪካ ኒው ጀርሲ ውስጥ የሚገኘው ይህ ሜትላይፍ ስታዲየም የዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታን ሊያስተናግድ ይችላል

የ2026 ፍፃሜ ጨዋታ የት ይደረጋል?

በርካታ ቡድኖች የሚሳተፉበትና በሦስት አገራት ውስጥ በሚስተናገደው ቀጣዩ የዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ግጥሚያ በየትኛው አገር እንደሚካሄድ ገና ውሳኔ ላይ አልተደረሰም።

ይህንን እና በሌሎች ውድድሩን በተመለከቱ ባሉ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ፊፋ በሚቀጥለው ዓመት ውሳኔው በሚቀጥለው የፈረንጆች ዓመት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

የፍጻሜውን ውድድር ለማዘጋጀት ግንባር ቀደም ተፎካካሪው በምሥራቅ ራዘርፎርድ ኒው ጀርሲ የሚገኘው የሜትላይፍ ስታዲየም ነው።

ይህ ስታዲየም 82,500 ተመልካቶችን የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን፣ በኤንኤፍኤል የሚወዳደሩት የኒውዮርክ ጃይንትስ እና የኒውዮርክ ጄትስ ቡድኖች ሜዳ ነው።

በሜክሲኮ የሚገኘው አዝቴካ ስታዲየም ለመክፈቻው ጨዋታ አስተናጋጅ ሆኖ ቀርቧል።

ሁለቱም ስታዲሞች የ2026ን የፍጻሜ ጨዋታ ለማዘጋጀት ተፎካካሪዎች ናቸው። የፊፋው ፕሬዝዳንት ኢንፋንቲኖ ለመወሰን ጊዜ እንደሚወስዱ ተናግረዋል።

“አሁንም የሚቀጥሉ ውይይቶች አሉ። በእርግጠኝነት ለመክፈቻ እና ለፍፃሜ የሚሆኑ ምርጥ ከተሞችን እንመርጣለን” ብለዋል ኢንፋንቲኖ።

“የዚህ ዓለም ዋንጫ እያንዳንዱ ግጥሚያ የፍጻሜ ያህል ይሆናል” ብለዋል።

የ2030 የዓለም ዋንጫስ?

13 ቡድኖች ብቻ የተፎካከሩበት የመጀመሪያው የፊፋ የዓለም ዋንጫ በኡራጓይ ከተስተናገደ ከ100 ዓመታት በኋላ የሚመጣ ልዩ የመቶ ዓመት ውድድር ይሆናል።

ኡራጓይ ውድድሩን ማስተናገድ አለብኝ ስትል ለተወሰነ ጊዜ ጠይቃለች። ምናልባትም ከአርጀንቲና ጋር ተጣምራ በጋራ ለማዘጋጀት ትጠይቅ ይሆናል።

ስፔን እና ፖርቱጋል በአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር በኩል ለማስተናገድ እድሉን እንደሚያገኙ ተስፋ ያደርጋሉ።

እንግሊዝ ከስኮትላንድ፣ ከዌልስ፣ ከሰሜን አየርላንድ እና ከአየርላንድ ሪፐብሊክ ጋር ዩሮ 2028 ለማሰናዳት ስትል የዓለም ዋንጫ ፍላጎቷን አቋርጣለች።

ሳዑዲ አረቢያ ሌላ ተፎካከሪ ልትሆን ትችላለች። ይህ ግን በመካከለኛው ምሥራቅ በሚኖረው ከፍተኛ የበጋ ሙቀት ምክንያት ሌላ የውድድር መፋለስ ሊያስከትል ይችላል።