በአፍሪካ የስፖርት ውድድሮች ላይ ዋነኛ አወዛጋቢ ጉዳይ የሆነው የዕድሜ ማጭበርበር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለዓመታት በአፍሪካ ስፖርት ላይ ጥቁር ጥላውን እንዳጠላ ነው። በቅርቡ በተካሄደው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ የችግሩ ስፋት ታይቷል።
የስፖርተኞች የዕድሜ ጉዳይ።
ካሜሩን ባዘጋጀችው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ተሳታፊ ከነበሩት አገራት መካከል አንዷ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ነበረች። ነገር ግን ከጨዋታው ጅማሬ በፊት ከውድድሩ እንድትሰረዝ ተደርጓል።
ምክንያቱ ደግሞ ለውድድሩ ከተላኩት ተጫዋቾች መካከል 25ቱ ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በላይ መሆናቸውን የኤምአርአይ ምርመራ በማሳየቱ ነው።
ከኮንጎ በተጨማሪ ቻድ እንዲሁ ተጫዋቾቿን ካሜሩን ከላከች በኋላ ከውድድሩ ተሰርዛለች።
የካሜሮን እግር ኳስ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ኤቶ የኤምአርአይ ምርመራ እንዲደረግ ካዘዘ በኋላ፣ ቻድ ለውድድሩ ካቀረበቻቸው ተጫዋቾች መካከል 30ዎቹ የዕድሜ ገደቡን አልፈዋል።
በመላው ዓለም የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖችን የሚያማክሩት የስፖርት ሳይንስ ባለሙያው በአፍሪካ ስፖርተኞች ላይ የሚታየው የዕድሜ ማጭበርበር መቆም እንዳለበት ቢስማሙም፤ ኤምአርአይ ግን የተጫዋቾችን ትክክለኛው ዕድሜ ለማወቅ ትክክለኛው አማራጭ ላይሆን ይችላል ይላሉ።
በሶለንት ዩኒቨርሲቲ ሳውዝሃምፕተን የስፖርት ሳይንስ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር አደም ሆውኪ የኤምአርአይ ምርመራ የተጫዋቾችን ትክክለኛ ዕድሜ ማሳየት የሚችል አይደለም ይላሉ።
“በኤምአርአይ የሚደረግ ልኬት የአንድን ሰው ዕድሜ በትክክል ላያሳይ ይችላል” ይላሉ።
ቀድሞ በተቀመጠ የጊዜ ገደብ ውስጥ በተከታታይ የኤምአርአይ ምርመራ ተደርጎ የእነዚህ ምርመራ ውጤቶች ካልተተነተኑ በቀር ስፖርተኛው ዕድሜው ስንት እንደሆነ ለማወቅ ያዳግታል ሲሉ ያስረዳሉ።
የተጫዋቾችን ዕድሜን ለመለካት ኤምአየርአይን መጠቀም በተመለከተ ስጋታቸውን የገለጹት ዶ/ር ሆውኪ ብቻ አይደሉም።
እአአ 2013 ላይ አሜሪካዊው አማካይ አቡቺ ኦቢንዋ የልደት ሰርተፊኬቱን ከተወለደባት አሜሪካ ቢያቀርብም የተደረገለትን የኤምአየርአይ የዕድሜ ምርመራ ማለፍ አልቻለም።
ይህ ተጫዋች ያቀረበው ሰነድ ተዓማኒ ከሆነ ምንጭ የተገኘ መሆኑን በመጥቀስ ምርመራው የተለየ ውጤት ማሳየቱ መነጋገሪ ሆኖ ነበር።
የኤምአየርአይ ምርመራ የሚሰራው እንዴት ነው?
የዓለም እግር ኳስ የበላይ አስተዳዳሪ የሆነው ፊፋ እአአ በ2009 በናይጄሪያ አዘጋጅነት በተካሄደው ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ላይ ኤምአርአይ የተጫዋቾች ዕድሜ ለምርመራ ጥቅም ላይ እንዲውል ወስኖ ነበር።
ማግኔቲክ ሬሶናንስ ኢሜጂንግ (ኤምአርአይ) ማግኔቲክ ፊልድ እና የሬዲዮ ሞገዶችን በመጠቀም ቆዳን ዘልቆ በመግባት የዘርፉ ባለሙያዎች አጥንት እና የውስጥ አካላትን ማየት እንዲችሉ ያስችላል።
ዕድሜ ለመለካት በሚደረገው የኤምአርአይ ምርመራ ከመዳፍ እስከ ክርን ባለው በተጫዋቹን የእጅ ክፍል ላይ ምርመራ በማድረግ የዕድሜ ግምት ይሰጣል።
ከመደበኛ ሥራቸው በተጨማሪ በርካታ የኦሊምፒክ ኮሚቴዎችን እና የስፖርት አካላትን የሚያማክሩት ዶ/ር ሆውኪ፤ ኤምአርአይ ዕድሜን ለመለካት ጥቅም ላይ እንዲውል መደረጉ ሌላ ‘ዕድል’ ይዞ ሊመጣ ይችላል ይላሉ።
እንደ ዶ/ር ሆውኪ ከሆነ ኤምአየርአይ ዕድሜ ለመመርመር ብቻ ሳይሆን ለስፖርተኞች የተለያዩ ምርመራዎችን በማድረግ አካላዊ ጤናቸውን ማረጋገጥ እንዲቻል ዕድል ይፈጥራል ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
“እንደ ኤምአርአይ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በወጣት ስፖርተኞች ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የልብ ችግሮችን እና የመሳሰሉትን ቀድሞ ለመለየት ይጠቅማል።”
ይህም “ዋዳ [የዓለም ፀረ አበረታች ኤጀንሲ] ከሚያደርገው መደበኛ ምርመር የተለየ ላይሆን ይችላል” ይላሉ።
“እያወራን ያለነው ስለ ሰው ልጆች ነው። . . . በወደፊት በፕሮፌሽናል ሕይወታቸው ላይ ሊያጋጥማችው ስለሚችለው ነገር ብቻ ሳይሆን፣ በጤናቸው ላይ ሊያጋጥማቸው ስለሚችለው ጉዳት ቀድመን መለየት ይኖርብናል” ይላሉ ዶክተሩ።
እአአ 2003 ላይ አማካዩ ማርክ-ቪቪያን ፎኤ ለአገሩ ካሜሮን እየተጫወተ ሳለ እራሱን ስቶ ሜዳ ውስጥ ከወደቀ በኋላ ሕይወቱ ማለፉ አይዘነጋም።
በቅርቡም ሌላኛው የካሜሮን ተጫዋች የነበረው ሞደስቴ ምባሚ ገና በ40 ዓመቱ በልብ ድካም ሕይወቱ አልፏል።
የዴንማርኩ እና የማንችስተር ዩናይትዱ ክርስቲያን ኤሪክሰን በ2020 የአውሮፓ ዋንጫ ላይ በልብ ሕመም ሜዳ ላይ ተዝለፍልፎ ወድቆ ለጥቂት ሕይወቱ ተርፏል።
ታዲያ የዶ/ር ሆውኪ መከራከሪያ የተጫዋቾችን ዕድሜ ብቻ ለማወቅ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለውን የኤምአርአይ ምርመራ እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን ብንጠቀም እና የተጫዋቾችን የጤና ሁኔታ መመርመር ቢቻል ከላይ የተጠቀሱትን አይነት መጥፎ አጋጣሚዎች የማስቀረት ዕድሉ ሊኖር ይችላል የሚል ነው።












