ስለ እግር ኳሱ ንጉሥ ፔሌ የማናውቃቸው 10 ምስጢሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
መላው ዓለም በእግር ኳስ ንጉሥነቱ የሚስማማበት ኤዲሰን አራንቴስ ዶ ናሲሜንቶስ በአጭሩ ፔሌ፣ ሦስት የዓለም ዋንጫዎች በማንሳት በታሪክ ብቸኛው ከመሆኑ በተጨማሪ በርካታ ግቦችንም በማስቆጠር የክብረ ወሰን ባለቤት ነው።
ባለፈው ሳምንት በ82 ዓመቱ ያረፈው ፔሌ የእግር ኳስ ነገር ሲነሳ ስሙ በቀዳሚነት የሚጠቀስ እና ታሪኩ ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት በመላው ዓለም ሲነገር ቆይቷል።
በዚህም የፔሌ አብዛኛው ታሪክ እና ገጠመኙ በስፋት ተነግሯል ቢባልም ስለኳሱ ንጉሥ ብዙም ያለተባለለቸውን አስር ጉዳዮች እነሆ።
ለፔሌ ሲባል ዳኛ ከሜዳ መባረሩን ያውቃሉ?
በ1968 (እአአ) የብራዚል ቡድን ለኦሊምፒክ ውድድር ዝግጅት የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ከኮሎምቢያ አቻው ጋር ቦጎታ ውስጥ ገጥሞ ነበር።
በወቅቱ ቀይ ካርድ ሥራ ላይ ውሎ ስላልነበረ የጨዋታው ዳኛ ጉሌርሞ ቬላስጌዝ ፔሌ በኮሎምቢያ ተጫዋች ላይ ጥፋት በመፈጸሙ ከሜዳ እንዲወጣ አዘዙ በዚህ ጊዜ በስታዲየሙ ውስጥ ቀውጢ ተፈጠረ።
ብራዚላውያኑ ተጫዋቾች የቡድናቸው ወሳኝ ተጫዋች ከሜዳ እንዲወጣ መታዘዙ አስቆጣቸው፣ የእግር ኳሱን ኮከብ ለመመልከት ስታዲየም የታደሙት ኮሎምቢያውያንም የፔሌን ከሜዳ መባረር በመቃወማቸው ግርግር ተፈጠረ።
ዳኛውም በተፈጠረው ውዝግብ መሃል ጉሸማ ደርሶባቸው ፊሽካቸውን ለአንደኛው የመስመር ዳኛ አስረክበው ከሜዳ ሲወጡ፣ ፔሌ ወደ ጨዋታው እንዲመለስ ተደርጎ ግጥሚያው ቀጥሏል።

የፎቶው ባለመብት, Courtesy of Santos FC
የፔሌን ጨዋታ ለማየት ተኩስ አቁም ተደርጎ ነበር?
በአውሮፓውያኑ 1960ዎቹ ፔሌ የሚጫወትበት የሳንቶስ ቡድን በዓለም ላይ ካሉ ዝነኛ ክለቦች መካከል አንዱ በመሆኑ፣ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስገኙ የወዳጅነት ጨዋታዎችን በዓለም ዙሪያ እየተጓዘ ያደርግ ነበር።
ከእነዚህ ጨዋታዎች መካከል ሳንቶስ በ1969 በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ወደ ነበረችው አፍሪካዊት አገር ናይጄሪያ በመሄድ በቤኒን ከተማ ካለ ቡድን ጋር ተጋጥመው 2 ለ 1 አሸንፏል።
በወቅቱ ቢያፍራ የተባለችውን ግዛት ከናይጄሪያ ለመገንጠል የተጀመረ ጦርነት ይካሄድ ነበር። ፔሌ የሚገኝበት የሳንቶስ ቡድን የደኅንነት ስጋት ስለነበረው ለጨዋታ ከማምራቱ በፊት ተዋጊዎቹ ወገኖች ተኩስ ለማቆም ተስማምተው ነበር።
በእርስ በርስ ጦርነቱ የሚሳተፉት ወገኖች ጨዋታው በሚካሄድበት ወቅት ጦርነቱን እንደሚያቆሙ እና አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ጥቃት እንደማይሰነዝሩ አረጋግጠዋል።
ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ዝነኛው ፔሌ በቡድኑ ውስጥ መካተቱ ነው ተብሎ ይታመናል።
ታዋቂዎቹ ‘ዘ ቢትልስ’ ፔሌን እንዳያዩ ተከልክለዋል?
ፔሌ ፕሮፌሽናል ተጫዋች ሆኖ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አሜሪካ በ1975 (እአአ) በመሄድ ኒው ዮርክ ኮስሞስ የተባለን ቡድን ተቀላቅሎ ነበር።
ከቡድኑ አባላት ጋር ለመግባባት እንዲያግዘው ኒው ዮርክ ከደረሰ በኋላ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት መማር በጀመረበት ጊዜ፣ በዘመኑ በሙዚቃው ዘርፍ በመላው ዓለም ተወዳጅ የነበሩት የ‘ዘ ቢትልስ’ የሙዚቃ ቡድን አባል ከሆነው ከጆን ሌነን ጋር ተገናኝተዋል።
በ1966 (እአአ) እንግሊዝ ውስጥ የዓለም ዋንጫ በተካሄደበት ጊዜ ታዋቂዎቹ ሙዚቀኞች ፔሌን እና የብራዚል ብሔራዊ ቡድን ተጫወቾችን ለማየት ሞክረው ነበር።
ነገር ግን ሌነን ለፔሌ እንደነገረው የዘ ቢትልስ ሙዚቀኞች ሙከራ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። ይህም የሆነው በወግ አጥባቂ የብራዚል እግር ኳስ ማኅበር ባለሥልጣናት እምቢተኝነት መሆኑን ፔሌ ጽፏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፔሌ ለምን ለአውሮፓ ቡድን መጫወት አልቻለም?
የፔሌ ተቺዎች ፔሌ እግር ኳስን በአውሮፓ ክለቦች ውስጥ ተጫውቶ አለማወቁ ያለተቀናቃኝ የእግር ኳስ ንጉሥ እየተባለ ለመዝለቅ ሕይወቱን ቀላል አድርጎለታል ይላሉ።
ለዚህ ግን ችግሩ የፔሌ አልነበረም። እንደሚነገረው ከሌሎች ብራዚላውያን ተጫዋቾች በተለየ ፔሌ ዝነኛ በነበረባቸው ዓመታት ወደ ውጪ አገር ሄዶ እንዳይጫወት ታግዶ ነበር።
በወቅቱ በተጫዋቾች ዕጣ ፈንታ ላይ ክለቦች ወሳኝ ስለነበሩ፣ ክለቡ ሳንቶስ ከሪያል ማድሪድ እና ከኤሲ ሚላን ፔሌን ለመውሰድ የቀረበለትን ጥያቄ ሳይቀበለው ቀርቷል።
ፔሌ ብራዚል ውስጥ ብቻ እንዲጫወት ግፊቱ ከመንግሥት በኩልም መጥቶ ነበር። በ1961 (እአአ) የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጃኒዮ ኳድሮስ፣ ፔሌ “ወደ ውጪ ሊላክ የማይችል ብሔራዊ ሀብት ነው” ብለው አወጀው ነበር።
ነገር ግን ከዓመታት በኋላ ፔሌ የአሜሪካውን ኒው ዮርክ ኮስሞስ ቡድንን በመቀላቀል በውጪ አገር ቡድን ውስጥ ተሰልፎ የመጫወት ዕድል አገኘ።
ፔሌ ለምን አምበል ሳይሆን የእግር ኳስ ዘመኑ አበቃ?
ምንም ያህል የእግር ኳስ ጥበበኛ ቢሆን፣ ዝናው በዓለም ቢናኝ ፔሌ በእግር ኳስ ዘመኑ በአምበልነት በጨዋታ ላይ የተሳተፈው አንድ ጊዜ ብቻ ነው።
ለዚህም ምክንያቱ ለአገሩ ብሔራዊ ቡድንም ሆነ ለቡድኑ አምበል እንዲሆን ሲጠየቅ እምቢኝ በማለቱ ነበር።
ፔሌ ለአንድ ጊዜም ቢሆን የአምበልነቱን መለያ ክንዱ ላይ ያሰረው የእግር ኳስ ዘመኑ ካበቃ በኋላ በ50ኛ ዓመት ዕድሜው ለብሔራዊ ቡድኑ በተሰለፈበት ጊዜ ነው።
ይህ የሆነው ከብሔራዊ ቡድኑ ተሳትፎ ጫማውን ከሰቀለ ከ19 ዓመታት በኋላ በ1990 (እአአ) ለፔሌ 50ኛ ዓመት በተዘጋጀው ጨዋታ ላይ ነው።
ጨዋታው ጣሊያን ሚላን ውስጥ የተካሄደ ሲሆን በብራዚል ብሔራዊ ቡድን እና ከመላው ዓለም የተወጣጡ ታዋቂ ተጫዋቾች መካከል ሲሆን፣ ፔሌ በመጀመሪያው 45 ደቂቃ ተሰልፎ ተጫውቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፔሌ ለምን ከሜዳ “ተጠልፎ” ተወሰደ?
የሳንቶስ ቡድን ተጫዋቾች በ1972 (እአአ) ለግጥሚያ ወደ ካሪቢያኗ አገር ትሪንዳድ ኤንድ ቶቤጎ ለግጥሚያ በሄዱበት ጊዜ በአገሪቱ ሰላም ስላልነበረ በቶሎ ግጥሚያቸውን አደርገው ወደ አገራቸው ለመመለስ ጓጉተው ነበር።
ነገር ግን በጨዋታው ላይ በ43ኛው ደቂቃ ፔሌ ግብ ሲያስቆጥር ያልጠበቁት ነገር ተከሰተ። በስታዲየሙ የነበሩት ተመልካቾች በደስታ ሜዳውን ጥሰው ገቡ።
ከዚያም ግብ ያስቆጠረውን ፔሌን በትከሻቸው ላይ ተሸክመው ከስታዲየም ውጪ ይዘውት በመውጣት በጎዳናዎች ላይ እየጨፈሩ ደስታቸውን ይገልጹ ነበር።
በወቅቱ ከቡድኑ አባላት ተለይቶ በደጋፊዎቹ ወደ ጎዳና የተወሰደውን ፔሌን ከትከሻቸው ላይ አውርዶ ከቡድኑ ጋር ለመቀላቀል ከፍ ያለ ጥረትን ፈልጎ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በፊልም ላይ የራምቦን ቦታ ፔሌ ለምን ተካ?
በ1980 (እአአ) ‘ኢስኬፕ ቱ ቪክትሪ’ የተባለው ፊልም ሲቀረጽ ሲልቭስተር ስታሎን (ራምቦ) በፊልሙ ዓለም ዝነኛ ተዋናይ ነበር።
‘ኢስኬፕ ቱ ቪክትሪ’ የተሰኘው ልቦለዳዊ ፊልም በናዚ ቡድን እና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት እስረኛ በነበሩ ተጫዋቾች መካከል የሚደረግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ታሪክን የሚያሳይ ነው።
በዚህ ፊልም ላይ ታዋቂዎቹ እግር ኳስ ተጫዋቾች ፔሌ፣ ቦቢ ሙር እና ኦሲ አርዲልስ የተሳተፉበት ሲሆን፣ ሲልቭስተር ስታሎን ደግሞ በረኛ ሆኖ ተሰልፏል።
በፊልሙ ላይ ፔሌ በመቀስ ምት ኳስ ሲመታ የሚታይበት አንድ ክፍል አለ፤ ይህ ክፍል ሲቀረጽ በመጀመሪያው ሙከራ ፔሌ በድንቅ ሁኔታ የሚፈለገውን የመቀስ ምት ሲመታ ተቀርጿል።
ፔሌ እንደተናገረው ይህን የፊልም ክፍል ጀመሪያ ላይ ሲልቭስተር ስታሎን እንዲተውነው ነበር የታቀደው። ነገር ግን እሱ ያንን ማድረግ ባለመቻሉ ፔሌ ያቺን የመቀስ ምት ግብ ሲያስቆጥር እንዲቀረጽ ተደረገ።
ፔሌ በረኛ ሆኖ በተጫወተበት ጊዜ ግብ አልተቆጠረበትም?
ፔሌ የሚታወቀው በአጥቂነት ቦታ ባለው ድንቅ ችሎታ እና ሚና በመሆኑ የተዋጣለት ግብ ጠባቂ ስለመሆኑ ብዙም አይነገርም።
ለዚህም ቡድኑ አንድ ተጫዋች ብቻ የመቀየር ግዴታ ሲኖርበት ፔሌ የበረኛውን ቦታ በመረከብ ወሳኝ ተጫዋች ወደ ሜዳ እንዲገባ ያደርጋል።
በተጨማሪም ለቡድኑ ሳንቶስ በተጫወተባቸው ዓመታት አራት ጊዜ በረኛ ሆኖ የተሰለፈ ሲሆን፣ አንደኛው ቡድኑ ለብራዚል ሻምፒዮና ለግምሽ ፍጻሜ በደረሰበት ወቅት ነበር። ፔሌ በግብ ጠባቂነት በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ላይ አንድም ግብ ተቆጥሮበት አያውቅም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በፔሌ ስም የሚታወቁ በርካታ ታዋቂ ተጫዋቾችስ. . . ?
ከዝነኛው ፔሌ በኋላ በርካታ በእርሱ ስም የሚጠሩ ሰዎች በመላው ዓለም ተፈጥረዋል። እነዚህም በእግር ኳስ ሜዳ እና በሌለው መስክ የሚታወቁ ናቸው።
በተለይ ድንቅ የእግር ኳስ ችሎታ ላላቸው ታዳጊዎች ፔሌ የሚለውን ቅጽል ስም መስጠት የተለመደ ነው። በርካቶችም በዚህ ስም በእግር ኳሱ መድረክ ችሎታቸውን አሳይተዋል።
ከእነዚህም መካከል በአፍሪካ ዝነኛ እግር ኳስ ተጫዋች የነበረው ጋናዊው አቤዲ አዬው፣ በአፍሪካ እና በአውሮፓ ክለቦች ውስጥ ሲጫወት በስፋት የሚታወቀው አቤዲ ፔሌ በሚለው ስሙ ነው።
የኬፕ ቬርዲው ተከላካይ እና በ2006 (እአአ) ለእንግሊዙ ሳውዝ ሃምፕተን የተጫወተው ፔድሮ ሞንቴሮ፣ በልጅነቱ በወጣለት ፔሌ በተሰኘው ቅጽል ስሙ ይታወቅ ነበር።
የእግር ኳሱ ንጉሥ የስም ተጽእኖ ፔሌ በሚለው ስሙ ላይ ብቻ የተወሰነ አልነበረም፣ ኤዲሰን አራንቴስ ዶ ናሲሜንቶስ ከሚለው ስሙ ላይ የመጀመሪያውን በመውሰድ በርካቶች ለልጆቻቸው ሰጥተዋል።
ፔሌ ዝነኛ ከሆነ በኋላ በብራዚል ውስጥ ኤዲሰን የሚለው ስምም በበርካቶች ዘንድ ተመራጭ መሆኑን የአገሪቱ ስታትስቲክስ ተቋም ገልጿል።
በ1950ዎቹ በአገሪቱ ውስጥ ኤዲሰን በሚለው ስም የሚጠሩ 43,511 ሰዎች ነበሩ። ከ20 ዓመታት በኋላ ፔሌ ከ1,000 ጎሎች ሲያስቆጥር እና በሦስት የዓለም ዋንጫዎች አሸናፊ ሲሆን የስሙ ተፈላጊነት ጨምሮ ኤዲሰን የሚባሉት ሰዎች ቁጥር ወደ 111,000 ደረሰ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፔሌ የብራዚል ፕሬዝዳንት የመሆን ፍላጎት ነበረው?
በ1990 (እአአ) ፔሌ ከአራት ዓመት በኋላ በሚካሄደው የብራዚል ፕሬዝዳንትንት ምርጫ ላይ እንደሚወዳደር ለዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን አሳውቆ ነበር።
ነገር ግን እንዳለው ለመሪነት ዕጩ ሆኖ ባይቀርብም ወደ ፖለቲካው ዓለም በመግባት መሳተፍ ጀመረ። ከ1995 አስከ 1998 የብራዚል ስፖርት ሚኒስትር ሆኖ አገልግሏል።
በዚያ ወቅትም እሱን በውጭ አገራት ቡድኖች ውስጥ ተሰልፎ እንዳይጫወት ያደረገው የቡድኖች ጫና እንዲቀንስና ተጫዋቾች በወደፊት ዕጣቸው ላይ ለመወሰን የሚያስችል ሕግ እንዲወጣ ጥረት አድርጓል።













