የብራዚላዊው የእግር ኳስ ንጉሥ የፔሌ ታሪክ በብራዚላዊው ጋዜጠኛ ዐይን

ፔሌ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

*ብራዚላዊው የቢቢሲ ጋዜጠኛ ፈርናንዶ ዱዋርቴ ፔሌን ከአንድም ሁለት ጊዜ አግኝቶታል። እነሆ ትዝታውን እንዲህ ያካፍለናል።

ፔሌን ለመጨረሻ ጊዜ ያየሁት ለንደን ውስጥ ከአንድ የፈጣን ምግብ መሸጫ ሱቅ ደጃፍ ሳንድዊች ለመብላት ሲታገል ነው።

ጊዜው መጋቢት 2015 ነበር። የእግር ኳስ ንጉሡ ፔሌ ‘ሰብዌይ’ ከተሰኘው የአሜሪካ ሳንድዊች ቸርቻሪ ጋር በገባው ቃል መሠረት ለድርጅቱ ማስታወቂያ አየሠራ ነበር።

ከፔሌ ጋር ከዚህ ቀደም ተገናኝተን እናውቃለን። ሁሌም ሳገኘው ፈገግታው ይጋባብኛል። ከጋዜጠኞች መሃል መርጦ ሲጠራኝ ነብሴን ይሞቃታል።

ፔሌን አንድ ለአንድ ቃለ መጠይቅ ማድረግ በመቻሌ እንደኔ ዕደለኛ ሰው ያለ እንዳይመስለኝ አድርጎኛል።

ነገር ግን ከሁሉም ከሁሉም የማይረሳኝ ፔሌ በ74 ዓመቱ ጤናማ ሆኖ፤ ሰውነቱ ተመልሶ ያገኘሁት ቀን ነው።

“ንጉሥ፤ ሆስፒታል ስትገባ እኮ ብዙ ሰው ተጨነቀ” አልኩት።

“ትሬስ ኮራሶይስ [በፖርቹጊዝ ሦስት ልቦች ማለት ነው] ከተማ መወለዴን ዘነጋህ እንዴ? ሦስት ልብ ያለውን ሰው በቀላሉ መጣል የማይታሰብ ነው” አለኝ በፈገግታ ታጅቦ።

‘ልዕለ ኃያሉን ማግኘት’

ሆስፒታል ከመግባቱ አንድ ዓመት ቀድሞ ዙሪክ ውስጥ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል ፊፋ ባዘጋጀው አንድ ስብሰባ ላይ ታድሞ ነበር።

ፔሌ በዚህ ወቅት ሰውነቱ እንደ መገርጣት ብሎ ነበርና ብዙዎች በሐዘኔታ ከንፈራቸውን መጠጡ፤ እጅግ ደነገጡ።

ልክ እንደአብዛኞቹ ብራዚላዊያን ጋዜጠኞች፣ እኔም ፔሌ ብዙም የሚቆይ አልመሰለንም ነበረ።

ከዚያ በኋላ እንደሰማነው ፔሌ የኩላሊት ችግር አጋጥሞት ሲሰቃይ ቆይቷል። አልፎም በፈረንጆቹ 1970 አንደኛ ኩላሊቱን ማጣቱ ነገሮችን አወሳሰባቸው።

ለ21 ዓመታት እግር ኳስ የተጫወተው ፔሌ ከተጋጣሚዎቹ ይደርስበት የነበረው ጉሸማም ለኩላሊቱ በጎ ውለታ አልዋለም።

ሁሌም ካገኘሁት በኋላ ባሉት ሁለት፣ ሦስት ቀናት ምንድነው የሆነው ብዬ እገረማለሁ። ‘ልዕለ ኃያሉን’ ማግኘት ያለው ስሜት ይለያል።

ለአብዛኛዎቹ የእግር ኳስ ደጋፊዎች፤ በተለይ ደግሞ ብራዚላውያን ኤድሰን አራንቴስ ዶ ናሺሜንቶ ልክ በሆሊውድ ፊልም እንደምናያቸው በራሪ አክተሮች ‘ልዕለ ኃያል’ (ሱፐርሂሮ) ነው።

በቀላል ቋንቋ ለብራዚላውያን ፔሌ ማለት እግር ኳስ ሜዳ ላይ የታየ የምንም ጊዜ ታላቅ ተጫዋች ነው።

እንግሊዛዊው ሙዚቀኛ ጆን ሌነን በአንድ ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር። “የሮክ እና ሮል የሙዚቃ ዘውግ በቻክ ቤሪ ይጠራ።”

ቻክ ቤሪ፤ የሮክ እና ሮል የሙዚቃ ዘውግ አባት ነው ይባልለታል።

ልክ እንደዚያው እግር ኳስ ደግሞ ፔሌ ተብሎ ሊጠራ ይገባል።

ፔሌ

ፔሌ አሁንም በታሪክ ሦስት ጊዜ የዓለም ዋንጫን ያነሳ ብቸኛው እግር ኳሰኛ ነው። የመጀመሪያውን ዋንጫ ሲያነሳ ደግሞ ገና ዕድሜው 17 ነበር።

ከ12 ዓመታት በኋላ ሜክሲኮ ላይ ብራዚል ዋንጫ ስታነሳ ያ ብሔራዊ ቡድን የምንጊዜም ምርጡ ተብሎ ነበር።

በወቅቱ ፔሌ ያሳየውን ብቃት ተመልክቶ ጣልያናዊው ተከላካይ ታርቺስኮ በርጊንች እንዲህ አለ “እኔ ልክ እንደሌሎቻችን ቆዳ እና አጥንት ያለው መስሎኝ ነበር። ነገር ግን ተሳስቻለሁ።”

ብራዚል ጣልያንን ረትታ ዋንጫውን ስታነሳ ፔሌ አንድ ጎል አስቆጥሮ ሁለት ግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል።

አነጋጋሪው ብሔራዊ ዓርማ

የፔሌ የብሔራዊ ቡድን ተሳትፎ ያበቃው በ1973 ነበር። ነገር ግን እስካሁን ስለሱ ኃያልነት የሚያወሩ አንደበቶች አልሰነፉም።

ብራዚልን በዓለም የእግር ኳስ መድረክ እጅግ የምትፈራ አገር ያደረገው ጥቁሩ ፔሌ ብሔራዊ ጌጥ ይባል ጀመረ።

የፔሌ አገር በቀደመ ታሪኳ ባርነት የሰፈነባት እና የቆዳ ቀለም ለይታ የምታዳላ ነበረች።

እንደ ፔሌ ታዋቂ የሆነ ብራዚላዊ ያለ አይመስለኝም።

በተጓዝኩበት ሁሉ የእሱን ስም እሰማለሁ። ከኒው ዮርክ እስከ አፍሪካ - ከየት እንደመጣሁ ስነግራቸው የፔሌን ስም ያነሱልኛል።

እርግጥ ነው ፔሌ ከትችት የነፃ አልነበረም። በተለይ ደግሞ በብራዚል የነበረውን ወታደራዊ አገዛዝ መቃወም ነበረበት ብለው የሚወቅሱት አሉ።

በፈረንጆቹ 2021 ኔትፍሊክስ ላይ በተለቀቀ ዘጋቢ ፊልም ፔሌ “እግር ኳሰኞች ለውጥ ማምጣት አይችሉም” ነበር ሲል በወቅቱ ስለነበረው ነገር ተናግሯል።

“እኔ አላውቅም ነበር ብል መዋሸት ይሆንብኛል። ነገር ግን እየሆነ ስለነበረው ነገር እርግጠኛ አልነበርንም።”

ፔሌ በ1974 ለብራዚል ብሔራዊ ቡድን ያልተጫወተው በወቅቱ የነበረውን ወታደራዊ አገዛዝ በመቃወም ነው የሚሉ ወሬዎች ተሰምተዋል።

አልፎም በብራዚል ስላለው ዘረኝነት እግር ኳስ ተጫዋች እያለም ሆነ ጫማ ከሰቀለ በኋላ ብዙ አልሠራም የሚል ትችት ይቀርብበታል።

ፔሌ በ17 ዓመቱ በዓለም ዋንጫ ተሰልፎ ቡድኑ የዋንጫ አሻናፊ ሲሆን በደስታ ሲያለቅስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፔሌ በ17 ዓመቱ በዓለም ዋንጫ ተሰልፎ ቡድኑ የዋንጫ አሻናፊ ሲሆን በደስታ ሲያለቅስ

ጥቁር ነጥቦች

የፔሌ ግላዊ ሕይወትም ከውዝግብ የፀዳ አይደለም። ልጁ ኤድሰን ዕፅ በማዘዋወር ተጠርጥሮ መታሰሩ፤ ከትዳር ውጪ የተወደለችው ሳንድራን መካዱ. . .

ፔሌ፤ በኔትፍሊክስ ዘጋቢ ፊልም ላይ ከበርካታ ሴቶች ጋር ግንኙነት እንደነበረው ጠቅሶ “ምን ያህል ልጆች እንዳሉኝ አላውቅም” ሲል ተናዟል።

ፔሌ ጫማውን የሰቀለው በፈረንጆቹ 1977 ነበር።

ንጉሱ እግር ኳሰኛ ወደ ማሰልጠን ያመራል ተብሎ ቢጠበቅም ብዙም አልገፋበትም። ባይሆንም በአስተያየት ሰጪነት አገልግሏል።

በተከታታይ ድራማዎች እና ፊልሞች ላይም ተሳትፏል። የብራዚል ስፖርት ሚኒስትር ሆኖ ከ1995-98 አገልግሏል።

ስንፈተ-ወሲብን የሚከላከል መድኃኒት ጨምሮ ሌሎች በርካታ ማስታወቂያዎች ሰርቷል።

ፔሌ የእግር ኳስ ውጤቶችን ሲገምት ‘ዓይን የለመውም’። ብዙውን ጊዜ ግን አይሳካለትም።

“የእግር ኳስ ሕይወቴ የፈለግኩትን እንዳወራ መብት ሰጥቶኛል” ሲል በ2006 ተናግሯል።

ሊዮኔል ሜሲ ተዓምሩን ማሳየት ከጀመረ ወዲህ ፔሌ የምንጊዜውም ምርጡ እግር ኳሰኛ የሚለውን ስሙን የሚያጣ ይመስላል። እሱ ግን አይስማማም።

“እኔ በጭንቅላቴ እና በሁለቱም እግሮቼ ማስቆጠር እችላለሁ። ሜሲ ግን ከግራ እግሩ ውጪ መጫወት አይችልም። ደግሞ ገና አንድ ሺህ ጎል ማስቆጠር ይጠበቅበታል” ሲል ነግሮኝ ያውቃል።

አንድ ጊዜ አግኝቼው አርጀንቲናዊው አጥቂ ያንተን ያክል ክብር ለማግኘት ገና ሁለት የዓለም ዋንጫ ይቀረዋል ብዬ ብነግረው ደስ ይለኝ ነበር።

ይህን ሲሰማ ፈገግ እንደሚል አልጠራጠርም። ፈገግታው ይናፍቀኛል።

ፔሌ እና ዱዋርቴ

የፎቶው ባለመብት, Fernando Duarte

የምስሉ መግለጫ, ፔሌ እና ዱዋርቴ