ካናዳ ለምን 1.5 ሚሊዮን ስደተኞች ለመቀበል ፈቀደች?

ካናዳውያን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ካናዳ ሠራተኛ ኃይሏ ላይ የተፈጠረውን ምጣኔ ሃብታዊ ክፍተት ለመሙላት ከሌሎች አገራት ሰዎችን ለማስገባት እየሰራች ነው። ስደተኞች ትቀበላለች ሲባል ግን ሁሉንም ማለት አይደለም።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የፌደራል መንግሥቱ እአአ በ2025 ላይ 500,000 ስደተኞችን ለመውሰድ ግዙፍ ዕቅድ አውጥቷል። በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥም ወደ 1.5 ሚሊዮን የሚጠጉ አዳዲስ ስደተኞች ወደ አገሪቱ ይገባሉ።

በቅርብ የተደረገ የሕዝብ አስተያየት መለኪያ እንደሚያሳየው ደግሞ ብዙ መጤዎችን መቀበል የፈጠረው ጭንቀትም አለ።

የካናዳ ትልቅ ዕቅድ

ለብዙ ዓመታት ካናዳ ቋሚ ነዋሪዎችን (በአገሪቱ ላልተወሰነ ጊዜ የመቆየት መብት ያላቸው፣ ነገር ግን ዜጎች ያልሆኑ ማለት ነው) ለመሳብ ሞክራለች። ዓላማው የሕዝብ ብዛት እና ኢኮኖሚን ለማሳደግ ነው።

ባለፈው ዓመት አገሪቱ 405,000 ቋሚ ነዋሪዎችን ወስዳለች። ይህ በታሪኳ ከፍተኛው ቁጥር ነው ተብሏል።

ልክ እንደሌሎች ምዕራባውያን አገራት ሁሉ ካናዳ ዝቅተኛ የወሊድ መጠን እና እርጅና የተጫነው ሕዝብ አላት። ይህም አገሪቱ ማደግ ከፈለገች ስደተኞችን መቀበል አለባት ማለት ነው።

ስደተኞች ቀድሞውንም ለአገሪቱ የሠራተኛ ኃይል ዕድገት ሙሉውን በሚባል ደረጃ ይሸፍናል። በ2032 የአገሪቱን የሕዝብ ቁጥር ዕድገትንም ይሸፍናል ተብሎ ይጠበቃል ሲል የመንግሥት መረጃ አመልክቷል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የካናዳ መንግሥት ከሦስት ዓመት በኋላ 500,000 አዲስ ስደተኞችን ለመውሰድ ተስፋ እንዳለው አስታውቋል። ይህ ቁጥር ካለፈው የፈረንጆች ዓመት በ25 በመቶ ገደማ ክፍ ያለ ነው።

የዓለም ልዩ ቦታ

ዛሬ ከአራት ካናዳውያን አንዱ በስደተኛነት ወደ አገሪቱ የገባ ነው። ይህም ቡድን ሰባት አገራት መካከል ከፍተኛው ነው። የቅይጦች አገር በምትባለው አሜሪካ እንኳን 14 በመቶው ብቻ ነው ስደተኛ።

ዩናይትድ ኪንግደምም (ዩኬ) 14 በመቶ ገደማ መጤ ሕዝብ አላት።

በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የፍልሰት ዳይሬክተር የሆኑት ማዴሊን ሱምፕሽን እንሚሉት፣ እነዚህ ቁጥሮች ዩኬ በስደተኞች አሃዝ ወደ ኋላ ቀርታለች ማለት አይደለም፤ ነገር ግን ካናዳ “የእጅግ ወጣ ያለች” ነች።

የካናዳን በእጥፍ የሚበልጥ ሕዝብ ያላት ዩናይትድ ኪንግደም ቀድሞውንም ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት አላት። ከ38 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ካናዳ በዓለም ላይ ግዙፍ መሬት ካላቸው አገራት አንዷ ስትሆን ለማደግም ቦታ አላት።

“በአጠቃላይ ዩናይትድ ኪንግደም ካናዳ ባደረገችው መንገድ የሕዝብ ብዛቷን የመጨመር ዓላማ አልነበራትም” ብለዋል።

በማክማስተር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንቲስት የሆኑት ጄፍሪ ካሜሮን በበኩላቸው እንደ ካናዳ ያሉ አገራት ዝቅተኛ የወሊድ መጠን እና እርጅና የተጫነው ሕዝብ ቢኖራቸውም፣ የማንኛውም የስደተኛ ሥርዓት ስኬት የተመሠረተው በሕዝብ ድጋፍ ላይ ነው ብሏል።

“ለአብዛኞቹ አገራት ገዳቢው ጉዳይ የሕዝብ አስተያየት ነው” ብለዋል።

በአሜሪካ ደቡብ አቅጣጫ ድንበር አቋርጠው ወደ አገሪቱ የሚገቡት ስደተኞች ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። ካለው ሥራ ይልቅ የስደተኞች ከፍተኛ መሆን ስጋቱ ፈጥሯል።

ዜግነት ለመቀበል ቃለ መሐላ የሚፈጽሙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ብሪታኒያ ከአውሮፓ ኅብረት ከመውጣቷ በፊት ከምሥራቅ አውሮፓ ወደ ዩኬ የሄዱ የአውሮፓ ኅብረት ስደተኞች መጥፎ ስሜት ፈጥረዋል።

እንደ ሳምፕሽን ገለጻ ከሆነ ባለፉት በርካታ ዓመታት ግን ሕዝቡ ስለ ስደተኞች ያለው አውንታዊ አስተያየት ጨምሯል። ከምክንያቶቹ አንዱ አገሪቱ ከበፊቱ የበለጠ በሚመጡ ስደተኞች ላይ ያላት ቁጥጥር እንዳደገ ስለሚያምኑ ነው። “ ”

ካናዳ በበኩሏ ለስደተኞች ከፍተኛ ድጋፍ አላት።

“እኔ እንደማስበው አንዱ ምክንያት ወደ ካናዳ የሚደረገው ስደት በመንግሥት በሚገባ ቁጥጥር የሚደረግበት እና የካናዳን ጥቅም በሚያስጠብቅ መንገድ የሚተዳደር ነው የሚል ሕዝባዊ እምነት በመኖሩ ነው” ብለዋል ካሜሮን።

ይህ ማለት ግን ስለስደተኞች ምንም አይነት ስጋት የለም ማለት አይደለም።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዩናይትድ ስቴትስ ድንበር ላይ የስደተኞች ፍልሰት መጨመር መጠነኛ ውዝግብ አስነስቷል። በ2018 የካናዳ ሕዝባዊ ፓርቲ የተባለው ቀኝ ዘመም ፓርቲ ብቅ ማለቱ በ2019 የፌደራል ምርጫ ርዕሱን ግንባር ቀደም አድርጎታል።

የተለያዩ የካናዳ ክፍሎችም ለስደተኞች የተለያየ አመለካከት አላቸው።

መንግሥት በዓመት እስከ 500,000 የሚደርሱ አዳዲስ ስደተኞችን የማስገባት አላማውን ይፋ ባደረገበት ወቅት የራሷን የኢሚግሬሽን ገደብ የምታወጣው የኪውቤክ ግዛት በዓመት ከ50,000 በላይ ስደተኞችን እንደማትወስድ አሳውቃለች።

ያ ማለት የአገሪቱን ሕዝብ 23 በመቶ ድርሻ ያላት ኪውቤክ ከአገሪቱ ስደተኞች 10 በመቶ ብቻ ትወስዳለች ማለት ነው።

የኪውቤክ ጠቅላይ ሚንስትር ፍራንሷ ሌጋልት ብዙ ስደተኞች ከገቡ የክልሉን የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪነት ያዳክማሉ የሚለው እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል።

“50,000 እየተቀበልንም ፈረንሳይኛን ከውድቀት ለመታደግም አስቸጋሪ ነው” ብለዋል።

ካናዳ ለማደግ ብዙ ዕድል ሊኖራት ቢችልም፣ አንዳንድ ቦታዎች ከአሁኑ ችግሩ እየተሰማቸው ነው። እንደ ቶሮንቶ እና ቫንኩቨር ያሉ ዋና ዋና ከተሞች (የአገሪቱ 10 በመቶ ሕዝብ ይኖርባቸዋል) የተመጣጣኝ የመኖሪያ ቤት ቀውስ አለባቸው።

በ1,537 ካናዳውያን ላይ በተካሄደ የሕዝብ አስተያየት፣ ከአራቱ አስተያየት ሰጪዎች ሦስቱ ዕቅዱ በቤቶች እና ማኅበራዊ አገልግሎት ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል በሚል ያሳስባቸዋል። 49 በመቶዎቹ ዕቅዱ በጣም ከፍተኛ ናቸው ሲሉ 31 በመቶዎቹ ደግሞ ትክክለኛ ቁጥር ነው ብለዋል።

የካናዳ አቀራረብ

ከምዕራቡ ዓለም ካናዳ ልዩ የሆነችበት ሌላው መንገድ በኢኮኖሚያዊ ስደተኝነት ላይ ያላት ትኩረት ነው። ከካናዳ ቋሚ ነዋሪዎች መካከል ግማሽ ያህሉን የተቀበለችው ባላቸው ክህሎት እንጂ ቤተሰብ በማዋሃድ አይደለም።

መንግሥት ይህን አሃዝ እአአ በ2025 ወደ 60 በመቶ ለማድረስ ተስፋ ያደርጋል።

ለዚህ አንደኛው ምክንያት የካናዳ ሥርዓት እንደተቀረጸበት መንገድ ነው ሲሉ ካሜሮን ተናግረዋል። ካናዳ እአአ በ1960ዎቹ በአገር ደረጃ ከሚመደበው የኮታ ሥርዓት ወጥታ ወደ ነጥብ ተኮር ሥርዓት በመቀየር ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚጠቅሙ ከፍተኛ ችሎታ ላላቸው ስደተኞች ቅድሚያ ሰጥታለች።

“በአሁኑ ጊዜም ሥርዓቱን በተመሳሳይ መርሆዎች ይመራሉ” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ምንም እንኳን አውስትራሊያ እና ኒውዚላንድ ተመሳሳይ ሥርዓቶች ቢኖራቸውም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካየነው ይህ ልዩ ነው።

በዩናይትድ ኪንግደም ከአራት ቋሚ ነዋሪዎች መካከል ከአንድ በላይ ሚሆኑትን በኢኮኖሚው ውስጥ በማካተት ተቀባይነት ያገኙ ናቸው።

በአሜሪካ ውስጥ 20 በመቶ ያህሉ ግሪን ካርዶች በኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ይሰጣሉ። ሁለቱም አገራት ወደ ግዛታቸው የሚገቡትን የኢኮኖሚ ስደተኞች መጠን ለመጨመር ተስፋ አድርገዋል። በሁለቱም አገራት ትልቁ ልዩነት አብዛኞቹ የኢኮኖሚ ስደተኞች በአሠሪዎቻቸው ስፖንሰር መደረጋቸው ነው።

በካናዳ የሥራ ዕድል ፍልሰተኞች ካላቸው ጠቅላላ ነጥብ ጋር ቢገናኝም ሁሌም ግን አስፈላጊ አይደለም።

ዩናይትድ ኪንግደምም በቅርቡ ወደ ነጥብ ተኮር ሥርዓት ፊቷን አዙራለች። እንደ ሳምፕሽን ከሆነ ይህም ከበፊቱ ሥርዓት ጋር ተመሳሳይ ሲሆን የሥራ ዕድል ላገኙትም ቅድሚያ ይሰጣል።

ካናዳ ዕቅዷን ማሳካት ትችላለች?

ካናዳ ከሌሎች ትልልቅ አገራት የበለጠ የኢኮኖሚ ስደተኞችን የምትቀበል ብቻ ሳትሆን፣ በ2021 ብቻ 20,428 ስደተኞችን በመቀበል ግንባር ቀደም ነች።

ታሪክ ሁሌም ከጎኗ ባይሆንም አገሪቱ ለወደፊት ትልቅ ግቦችን አስቀምጣለች። ካናዳ እአአ በ2021 ወደ 59,000 የሚጠጉ ስደተኞችን መልሶ ለማቋቋም አላማ ነበራት። ይህም አገሪቱ ከወሰደቻችው በሦስት እጥፍ የሚበልጥ ነው።

የኢሚግሬሽን ሚኒስትር ሼን ፍሬዘር ከሲቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ዕቅዱ ያልተሳካው በዋናነት በካናዳ እና በዓለም ዙሪያ ከኮቪድ ጋር በተያያዘ የድንበር መዘጋት በመፈጠሩ ምክንያት ነው ብለዋል ።

ካናዳ እአአ በ2023 ብቻ 76,000 ስደተኞችን በግዛቷ ውስጥ መልሳ ለማቋቋም አቅዳለች።