ለኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ስደተኞች ተስፋን የፈነጠቀው አዲሱ አሜሪካ የመግቢያ ዕድል

የአሜሪካ ባንዲራ እና የነጻነት ሐውልት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሜሪካ ስትነሳ ዲቪ ይታወሰናል።

ከዛሬ ነገ ይቆማል ሲባል የነበረው ዲቪ ለአሥርታት ዘልቋል። ይህ የሎቶሪ መርሃ ግብር ደንቡን ለሚያሟሉ ሁሉ ክፍት ነበር።

አሁን የባይደን አስተዳደር አዲስ መርሃ ግብር ጀምሯል። ይህኛው ደግሞ ትኩረት ያደረገው ስደተኞች ላይ ነው።

ጦርነት እና መከራን ሽሽት በሁለተኛ አገር ተጠልለው ያሉ ዜጎችን በአሜሪካ አዲስ ሕይወት እንዲጀምሩ ያስችላል።

‘ዌልካም ኮር’ የሚል ስም ተሰጥቶታል።

የውጭ ጉዳይ ኃላፊው ብሊንክን ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ያስተዋወቁት ይህ ስደተኞችን የመቀበል አዲስ መርሃ ግብር አሜሪካዊ ዜጎች፣ አብያተ ክርስቲያናት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የሚያሳትፍ ነው።

ብሊንከን የዚህን መርሃ ግብር መጀመር ሲያበስሩ አሜሪካ በስደተኞች የተመሠረተች አገር መሆኗን በመዘከር ነበር።

“እኛ ስደተኞችን መቀበል ቱባ ባሕላችን ነው” ሲሉ ዜጎች በዚህ አዲስ መርሃ ግብር የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አድርገዋል።

የቢቢሲ አጋር የሆነው የአሜሪካው ሲቢኤስ ቴሌቪዥን እንደዘገበው ይህ መርሃ ግብር በከፊል የተቀዳው ከካናዳ ነው።

ለመሆኑ ይህ ስደተኞችን የመቀበል መርሃ ግብር እንዴት ነው የሚሠራው? ማንን ተጠቃሚ ያደርጋል?

ለስደተኞች የተከሸነ “ዲቪ”

ይህ የጆ ባይደን አስተዳደር ያስተዋወቀው አዲስ መርሃ ግብር ዘንድሮ በሙከራ ደረጃ ነው የሚተገበረው።

“ዌልካም ኮር” (Welcome Corps) ይባላል።

በአጭሩ ለማስቀመጥ ግለሰቦች ተቧድነው ስደተኛን ወደ አገረ አሜሪካ የሚያመጡበት የቅበላ ሥርዓት ነው።

ከዚህ ቀደም ስደተኞችን ወደ አሜሪካ የሚያስገቡ እና የሚቀበሉት ድርጅቶች በቁጥር ዘጠኝ ብቻ ነበሩ።

እነዚህም ቢሆኑ በትራምፕ ዘመን ሆን ተብሎ እንዲሽመደመዱ ተደርገው ነበር።

በዚህ የተነሳ ባለፉት ዓመታት ወደ አሜሪካ መሻገር የቻሉ ስደተኞች ቁጥር እጅግ በጣም ጥቂት ሆኖ ቆይቷል።

አሁን ለሙከራ የተዘረጋው ሥርዓት ግን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኛን ለአሜሪካ ምድር ማብቃት እንዲችል የተዘየደ ይመስላል።

አምስት አሜሪካዊያን ወይም የአሜሪካ ቋሚ መኖርያ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ይቧደናሉ።

ከዚያ ልክ እንደ ድርጅት አንድ ስደተኛን ስፖንሰር አድርገው ወደ አሜሪካ ማስገባት ያስችላሉ።

ስደተኛውን ለመቀበል የተቧደኑት ሰዎችም በጋራ የሚያዋጡት ገንዘብ ደግሞ 2 ሺህ 275 ዶላር ብቻ ነው።

ከዚህ ገንዘብ ጋር አምስቱ የተቧደኑ ሰዎች አዲሱን ስደተኛው ወደ አሜሪካ ሲመጣ ለ90 ቀናት እንዴት ተቀብለው አገር እንደሚያላምዱት የሚዘረዝር ምክረ ሐሳብ ያቀርባሉ።

ይህም ማለት ስደተኛው ምግብ፣ መጠለያ፣ ሕክምና፣ ትምህርቱን ወዘተ ለመጀመሪያዎቹ 90 ቀናት መሸፈን እንደሚችሉ መተማመኛ የሚሰጥ ይሆናል።

የአሜሪካ ዜግነትን ለመቀበል ቃለ መሃላ እየፈጸሙ ያሉ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ ዜግነትን ለመቀበል ቃለ መሃላ እየፈጸሙ ያሉ ሰዎች

በዚህ መርሃ ግብር የሚካተቱት እነማን ናቸው?

አሁን በሙከራ ላይ ያለው መርሃ ግብር ወደ ሦስተኛ አገር ለመሄድ በሁለተኛ አገር የሚገኙትን ይመለከታል።

ለጊዜው በተባበሩት መንግሥታ የስደተኞች ድርጀት ተመዝግበው ረዥሙን የማጣራት ሂደትን የጨረሱ እና አሜሪካ ለመግባት ተራ የሚጠባበቁ ስደተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።

ሙከራው ስኬታማ ከሆነ በኋላ ግን ዕድሉ በዚህ ብቻ አይወሰንም ተብሏል።

የትኞቹ ስደተኞች ቅድሚያ ያግኙ የሚለውን የአሜሪካ መንግሥት የሚወስን ቢሆንም፣ ወደፊት ግን ስፖንሰር አድራጊዎቹ አምስቱ ሰዎች ወደ አሜሪካ የሚያስመጡት ስደተኛ እነርሱ የሚመርጡበት አማራጭ ይኖራል ተብሏል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት እንደ መነሻ 10ሺህ አሜሪካውያንን ወይም ቋሚ የአሜሪካ ፈቃድ ያላቸውን ሰዎች በዚህ ስፖንሰር አድራጊነት እንዲመዘገቡ እያበረታታ ነው።

አስር ሺዎቹ ስፖንሰር አድርገው ወደ አሜሪካ የሚያመጧቸው ሰዎች 5ሺህ ያህል እንደሚሆኑ ይጠበቃል። ይህ አሐዝ በየዓመቱ በከፍተኛ ቁጥር ይመነደጋል።

ሂደቱን ስደተኛ በመቀበል ልምድ ያላቸው በአሜሪካ የሚገኙ ድርጅቶች ያስተባብሩታል።

ይህ መርሃ ግብር በየትኞቹ አገራት ስደተኞች ተሞክሮ ያውቃል?

ይህ ግለሰቦች ስደተኛን ስፖንሰር አድርገው አሜሪካ እንዲወስዱ የሚያስችለው አሰራር በከፊል ከዚህ ቀደም ለአፍጋኒስታን እና ለዩክሬናውያን አገልግሎት ላይ ውሎ ያውቃል።

በዚህ ሂደት በአንድ ዓመት ብቻ 100ሺህ ዩክሬናዊያን ከጦርነቱ በመሸሽ ወደ አሜሪካ መግባት ችለዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ በደቡባዊ ድንበሯ የሚደረገውን ሕገ ወጥ የሰዎች ፍልሰትን ለማስቆም በትራምፕ ጊዜ የኮንክሪት ግንብ እስከመገንባት ደርሳለች።

የባይደን አስተዳደር ሕጋዊውን መንገድ ካሳለጥን ወደ አሜሪካ በሕገ ወጥ መንገድ የሚገባው ሰው ቁጥር እንደሚቀንስ በጽኑ ያምናል።

ይህን ተከትሎም በተለይ የኩባ፣ የሄይቲ፣ የኒካርግዋ እና የቬንዝዌላ ዜጎች በሜክሲኮ በኩል በድንበር ከሚገቡ ሜክሲኮ ላይ ሆነው በመተግበሪያ ለጥገኝነት እንዲያመለክቱ አዲስ አሠራር ተከፍቶላቸዋል።

በአንድ ለአምስት አሠራር ወደ አሜሪካ የገቡት የዩክሬን እና የአፍጋን ዜጎች ጊዜያዊ የሥራ ፈቃድ ብቻ ነው የሚያገኙት።

ይሁንና አሁን በሚጀመረው የ‘ዌልካም ኮር’ መርሃ ግብር የሚገቡ ስደተኞች ቋሚ የሥራ ፈቃድ ከማግኘታቸውም ባሻገር የአሜሪካ ዜግነትን ለማግኘት በሂደት ማመልከት ይፈቀድላቸዋል።

አሜሪካ ከ1980ዎቹ ጀምሮ በከፈተችው የስደተኞች መርሃ ግብር በግማሽ ክፍለ ዘመን የተቀበለቻቸው ሰዎች ብዛት ከ3 ሚሊዮን አይበልጥም።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2022 ለምሳሌ አሜሪካ 125ሺህ ስደተኞችን እቀበላለሁ ብትልም መቀበል የቻለውችው ግን 25 ሺዎችን ብቻ ነው።

ከባይደን አስተዳደር በፊት የትራምፕ አስተዳደር ይህን ቁጥር በግማሽ ቀንሶት ነበር።

የካናዳ የዜግንት መጠየቂያ ሰነድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኢትዮጵያውያን እና ለኤርትራውያን ስደተኞች ትልቅ ተስፋ ነው የተባለው ለምንድነው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይህ አምስት ሰዎች አንድ ስደተኛን ወደ አሜሪካ እንዲወስዱ የሚያደርገው አሰራር በዋናነት ከካናዳ እንደተቀዳ ተመልክቷል።

“ለመሆኑ የካናዳ አሠራርና ተሞክሮ ምን ይመስላል? ከአዲሱ የአሜሪካ መርሃ ግብር የሚያመሳስለውስ ምኑ ነው?” ስንል በቶሮንቶ ካናዳ የተመሰከረላቸው የኢሚግሬሽን ጠበቃ እና የሕግ አዋቂ የሆኑትን አቶ ተክለሚካኤል አበበ ሳሕለማሪያምን ጠይቀናል።

ካናዳ ከውጭ አገር በዓመት ከ15 ሺህ እስከ 20 ሺህ ስደተኞችን በተለያየ መንገድ እንደምትቀበል ያወሳሉ።

እነዚህን የምትቀበለው በዋናነት በሦስት መንገድ ነው።

አንደኛው “ስፖንሰርሺፕ አግሪመንት ሆልደርስ” በሚባሉ ድርጅቶች ናቸው።

እነዚህ በሁለት ይከፈላሉ።

እነዚህ ስደተኛን ስፖንሰር የማድረግ መብት የተሰጣቸው ድርጅቶች አብያተ ክርስቲያናት፣ ለትርፍ ያልተቋቋሙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የማኅበረሰብ አቀፍ ድርጅቶች፥ ከካናዳ መንግሥት ጋር ውል አስረው ስደተኛን ወደ ካናዳ የሚያስገቡ ናቸው።

ሁለተኛው የኮሚኒቲ ስፖንሰሮች ይባላሉ።

እነዚህ ደግሞ ከመንግሥት ጋር ውል ሳያስሩ የሚሠሩ የንግድ ድርጅቶች ወይም አብያተ ክርስቲያናት ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህም ስደተኛን ከውጭ ያስገባሉ።

ሦስተኛው ወደ ካናዳ የመግቢያ መንገድ ደግሞ “ግሩፕ ኦፍ ፋይቭ” የሚባለው ነው።

ይህ አሠራር አምስት የካናዳ ዜጎች ወይም ቋሚ የመኖሪያ ፍቃድ ያላቸው የካናዳ ነዋሪዎች በጋራ ሆነው ስደተኛን የሚቀበሉት አሠራር ነው።

በካናዳ ላለፉት ረዥም ዓመታት የተተገበረው ይህ አሠራር ነው አሁን በአሜሪካ የተቀዳው።

“ከምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ ካየን ይህን መንገድ በተለይ ኤርትራውያን ውጤታማ በሆነ መንገድ ተጠቅመውበታል” ይላሉ ጠበቃው አቶ ተክለሚካኤል።

አሠራሩን “በደንብ ያልተጠቀምንበት ነገር ግን ልንጠቀምበት የሚገባ ነው” ይሉታል።

እርግጥ ነው በሚገባው መጠን ይህን አሠራር አልተጠቀምንበትም ቢባልም ከቫንኩቨር፣ ካልጋሪ፣ አልበርታ፣ ኤድመንተን ቶሮንቶን ጨምሮ ብዙ ሐበሾች የአገር ልጅን ስፖንሰር አድርገው ወደ ካናዳ የወሰዱበት አሠራር ነው።

የካናዳው አሠራር ምን ይመስላል?

አሜሪካ ስለ ዝርዝር ሂደቱ ገና ይፋ አላደረገችም። ነገር ግን አሠራሩ ከካናዳ የተቀዳ ከመሆኑ አንጻር የካናዳን ሂደት ሊከተል ይችላል የሚል ግምት ያሳድራል።

የካናዳን አሠራር መረዳት ስለ አሜሪካው አሠራር የሚጠቁም የሚሆነውም ለዚሁ ነው።

በካናዳ ሂደቱን በተመለከተ አቶ ተክለሚካኤል ግልጽና ቀላል ነው ይላሉ።

መጀመሪያ አምስት ሰዎች ይቧደናሉ። አምስቱ ሰዎች ወይ ዜጋ ወይም ቋሚ የመኖርያ ፍቃድ ያላቸው መሆን አለባቸው።

ከዚያ ከፖሊስ የወንጀል መዝገብ ውስጥ እጃቸው እንደሌለ ሰርተፍኬት ይወስዳሉ። ይህ የሚደረገው የሚያመጡት ስደተኛ በእነዚህ ሰዎች እንዳይበዘበዝ ለመከላከል ነው።

ከዚያ ወደ 16ሺህ የካናዳ ዶላር ገንዘብ በባንክ ያስቀምጣሉ።

ባንክ ማስመጥ ባይችሉ እንኳ አቅም እንዳላቸው የሚያሳይ “ኖቲስ ኦፍ አሰስመንት” የሚባል የታክስ ወረቀት ያቀርባሉ።

ዋናው ሐሳብ ስደተኛው ከመጣ በኋላ ለ12 ወራት ያህል ችግር እንዳይገጥመው ማድረግ ነው።

“ምግብ፣ መጠለያውን፣ የትምህርቱን ጉዳይ፣ ሥራ ማፈላለግ፣ ሆስፒታል መውሰድ ቢያስፈልግ፣ መንጃ ፈቃድ ማውጣት፣ ቋንቋ ማስተማር የመንግሥት አገልግሎቶችን ቢፈልግ በአጠቃላይ ኑሮውን እንዲያደላድል አምስቱ ሰዎች ስደተኛውን በኃላፊነት የሚወስዱበት አሠራር ነው።”

የአሜሪካ ዜግነት ሰነድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ወደ ካናዳ የሚገቡትን ስደተኞቹን የሚመርጡት እነማን ናቸው?

“እኔ በአሜሪካ እዚያ የሚኖረው አሠራር ምን ሊሆን እንደሚችል ባላውቅም...” ብለው ይነሳሉ አቶ ተክለሚካኤል፤ በካናዳው አሠራር አምስቱ ሰዎች ተሰብስበው ማምጣት የሚችሉትን ሰው እነሱው ናቸው የሚመርጡት።

ሆኖም ወደ ካናዳ የሚወሰደው ግለሰብ ለስደት ያበቃው ምክንያት መጻፍ ይኖርበታል። ታሪኩ ለስደት የሚያበቃ ምክንያት እንዳለውም ሊረጋገጥ ይገባል። በርካታ ፎርሞችም ይሞላሉ።

የጾታ ጥቃት፣ የዘር ጥቃት፣ ፖለቲካ እና ሌሎች በርካታ ምክንያቶች ለስደት ሊዳርጉ ይችላሉ። ያ ምክንያት ተጽፎ ኦቶዋ ለሚገኘው የኢሚግሬሽን ቢሮ (ROC-O) ይላካል።

ያ ቢሮ ጉዳዩን ገምግሞ አሳማኝ ሆኖ ሲያገኘው ስደተኛው ለሚገኝበት (ናይሮቢ፣ ካምፓላ፣ ካይሮ ወዘተ) የቪዛ ቢሮ ይላካል።

አቶ ተክለሚካኤል በካናዳ የስደተኛ አቀባበል ውስጥ አብያተ ክርስቲያናት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መንግሥት የሚመርጣቸውን ስደተኞች የሚቀበሉበት እና ስፖንሰር የሚያደርጉበት አሠራርም እንዳለ አስረድተውናል።

አንዳንድ ስደተኞች ለምን 10 እና 20 ዓመት ይቆያሉ?

በርካታ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ከአገራቸው ተሰደው በጎረቤት አገራት የስደተኛ ወረቀት ይዘው ለረዥም ጊዜ ወደ ሦስተኛ አገር ለመሻገር ሳይሳካላቸው ይቀራሉ።

አንዳንዶች ግን በዓመት እና በሁለት ዓመት ይሰምርላቸዋል? ይሄ የሚሆነው ለምንድነው?

አቶ ተክለሚካኤል ይህን ሲያስረዱ እርሳቸው ራሱ ከሁለት አሥርታት በፊት ስደተኛ እንደነበሩ በማውሳት ነው።

“አራት ዓመት ኬንያ ተሰድጄ ተቀምጫለሁ። ከእኔ ጋር የተሰደዱ አንዳንዶቹ 8 ዓመት፤ አንዳንዶቹ እስከ ዛሬም በዚያ የቆዩ ሊኖር ይችላሉ።”

ይህ ለምን ሆነ ከተባለ ምክንያቱ በርካታ ሊሆን ይችላል።

በዓለም ላይ ካሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞች ውስጥ ወደ ሦስተኛ አገር የሚገባው (Resettlement) ቁጥር አንድ እጅ እንኳ አይሞላም። ይህ ማለት 99 ከመቶው ባለበት ነው የሚቆየው።

አንድ እጅ ከሚሆነው ጥቂት የቀናው ስደተኛ መካከል ደግሞ በመንግሥት የሚወሰድ አለ። በድርጅትም የሚወሰድ አለ።

“እኔ ለምሳሌ ዩናይትድ የሚባል ቸርች በ2005 (እአአ) 75ኛ ዓመቱን ያከብር ነበር። ያን በማስመልከት 25 ስደተኞችን ወደ ካናዳ እናምጣ ሲሉ ከእነዚያ ዕድለኞች መካከል ሆንኩኝ።”

አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ስደተኛው ከአገር የወጣበት ምክንያት አንገብጋቢነት ይወስነዋል። የስደተኛው ማንነት እና የሚያቀርባቸው ማስረጃዎች እንዲሁም ሌሎች በርካታ ሁኔታዎች ስደተኛው ወደ ሦስተኛ አገር የሚገባበትን ፍጥነቱን ይወስኑታል።

ታሪካቸው ውስጥ በጦርነት እና በወንጀል ተሳትፎ የነበራቸው ወይም ደግሞ የካናዳ መንግሥት በዓመት ከሚፈቅደው የጤና ወጪ ከፍ ያለ ገንዘብ ሊያስወጣ የሚችል የጤና እክል ያለባቸው ሰዎች ካናዳ የመግባት ዕድል የላቸውም (Inadmissible) ይሆናሉ።

አቶ ተክለሚካኤል የአሜሪካው ፕሮግራም ተግባራዊ ሲሆን ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ይገምታሉ።

ምክንያቱን ሲያስረዱ አሜሪካ ከ300 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ እንደሚኖር፣ የሐበሾች ቁጥር ተጋኖ ሲነገር ወደ አንድ ሚሊዮን እንደሚጠጋ ካወሱ በኋላ በርካታ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ቢሯቸው ካናዳ እንደሚደውሉላቸው የነሳሉ።

“በካናዳ ፕሮግራም ለመጠቀም እኔ ጋ የሚደውለው ሰው ይኸው ፕሮግራም እዚያ ሲመጣለት እርግጠኛ ነኝ በርካታ ሰው ዕድሉን ለመጠቀም ይረባረባል” ይላሉ አቶ ተክለሚካኤል።

ከዚህ በላይ ያስደናቃቸው ደግሞ የሚጠየቀው ገንዘብ ዝቅተኛ መሆኑ ነው።

በካናዳ 12ሺህ የአሜሪካ ዶላር ሲጠየቅ በአሜሪካ ከ2500 ዶላር በታች ነው።

በካናዳ አምስቱ የቡድን አባላት ስደተኛውን የመንከባከብ ግዴታ የተጣለባቸው ለ12 ወራት ሲሆን በአሜሪካው አሰራር ግን ለ90 ቀናት ብቻ ነው።

“የእኔንን ግምት ከጠየቅከኝ የአሜሪካ መንግሥት በዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ በሚሆኑ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨናነቅ እጠብቃለሁ። አዲስ ፕሮግራም ስለሆነ ዜጎች ተሳፏቸውን ዝቅ አድርገው የገመቱት ይመስለኛል” ይላሉ አቶ ተክለሚካኤል።

“በተለይ ኤርትራውያን በዚህ ረገድ በጣም የሚደነቁ ናቸው፤ ተቀናጅተው ነው የሚሠሩት። ብዙ ሺህ ወገኖቻቸውን ከስደት ያወጣሉ ብዬ ነው የምጠብቀው።”

አዲስ የካናዳ ዜጋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ለምን ስፖንሰሮቹ አምስት እንዲሆኑ ተፈለገ?

ይህ የሆነበት መሠረታዊ እሳቤ ሰዎች የራሳቸው ሕይወት መኖር ስላለባቸው እና ስደተኛውን በጋራ መቀበል ኃላፊነትን መጋራት ስለሚሆን የተሻለ ነው ተብሎ ስለታመነ ነው።

ለምሳሌ አንድ ስደተኛ ሌላ አገር ሄዶ በቀላሉ ተግባብቶ እና ተዋህዶ እንዲኖር የአንድ ሰው ሥራ እንዲሆን አይፈልገም።

“እኔ እህቴ መጣች እንበልና፤ ዛሬ ትምህርት ቤት ብወስዳት እኔ ሥራ ስሄድ ሐኪም ቤት ማን ይወስዳታል? መንጃ ፍቃድ ማን ያስተምራታል? ገበያ ማን ያሳያታል? አምስት እንዲሆን የተፈለገው ለዚህ ነው። እሳቤው የተሳለጠ የኮሚኒቲ ተግባቦትን መፍጠር ስለሆነ ነው።”

አሜሪካ እና ካናዳ ለምን ስደተኛን መቀበል ፈለጉ?

ቻይናን ጨምሮ ጃፓን እንዲሁም የስካንዲኒቪያን በርካታ አገራት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወሊድ ምጣኔ መቀነሱ እንዳሳሰባቸው ገልጠዋል።

የሠራተኛ ኃይል እየተመናመነ መምጣቱ በወደፊቱ ምጣኔ ሃብታቸው ላይ ጠበሳ እንዳይኖረው ይሰጋሉ።

አሁን አሜሪካ የጀመረችው አዲስ መርሐ ግብር ከሰብአዊነቱ ጀርባ ኢኮኖሚያዊ ሰበብ አለው?

አቶ ተክለሚካኤል በዚህ ሐሳብ ብዙም አይስማሙም።

አገራት ዜጎቻቸው በዕድሜ እየገፉባቸው፣ የወሊድ ምጣኔ እየቀነሰባቸው መሄዱ እሙን ቢሆንም፤ እንዲህ ዓይነቶቹ መርሃ ግብሮችን ግን በዋናነት ያን ክፍተት ለመሙላት የሚያደርጉት ነው ብለው ለማመን ይቸገራሉ።

“በካናዳ ስደተኛ እንዲያውም ሸክም የሚሆንበት ዕድል ብዙ ነው። ኤርትራውያን እና ኢትዮጵያውያን ጠንካራ ሠራተኞች ስለሆኑ ቶሎ ወደ ሥራ ይገባሉ እንጂ ሁሉም ግን እንደዚያ ናቸው ማለት አይደለም።”

“በቀጣዮቹ ዓመታት ካናዳ አንድ ሚሊዮን ተኩል ሰዎችን እናስገባለን ብላለች። ከዚህ ውስጥ ለስደተኛው የተያዘው 15 ከመቶ ብቻ ነው። ኢኮኖሚያዊ ለሆነው ጉዳይ 85 በመቶውን የሚያስገቡት ሰዎች ይሸፍናሉ። የስደተኞቹ ግን ሰብአዊነት ነው ብዬ ነው የማስበው በግሌ። ደግሞ ብዙ ገንዘብ ያስወጣቸዋል እኮ” ይላሉ አቶ ተክለሚካኤል።