ዩናይትድ ኪንግደም እና ሌሎች ምዕራባውያን እንዴት እና ለምን ዜግነትን ሊነጥቁ ይችላሉ?

ከተወለዱበት አገር ዜግነትዎን ሊነጠቁ ይችላሉ እንዴት?
የምዕራባውያኑ አገር ዜግነት ገፈፉ፣ ወይም ነጠቁ ሲባልም ይሰማል።
በተለይም ዘራቸው ከአረቡ ዓለም ጋር የተያያዙ ሰዎችን ዜግነት።
አንዳንዶች ትውልዳቸው ዩናይትድ ኪንግደም ቢሆንም ዘራቸው ተመዞ ወደ ቤተሰቦቻቸው አገር እንዲመለሱ የሚደረግበት አስራር አለ።
የሻሚማ ቤገምን ጉዳይ እንመልከት።
የተወለደችው ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ሲሆን በታዳጊነቷ አገሯን ለቃ እስላማዊ መንግሥትን የተባለውን ቡድን (አይኤስ) ተቀላቀለች።
ዩኬም ዜግነቷን የነጠቀቻት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ዜግነቷን ለማስመለስ ከአገሪቱ መንግሥት ጋር እየተሟገተች ትገኛለች።
በአሁኑ ወቅት የ23 ዓመቷን የሻሚማ ጉዳይን ልዩ ችሎት እየተመለከተው ይገኛል።
ለመሆኑ ሻሚማ ቤገም ማን ናት?
ሻሚማ በአውሮፓውያኑ 2015 አይኤስን ለመደገፍ ወደ ሶሪያ ከተጓዙት ሦስት የምሥራቅ ለንደን ተማሪዎች መካከል አንዷ ናት።
ወላጆቿ እንግሊዛዊ ሲሆኑ ዘራቸው ከባንግላዴሽ ይመዘዛል።
ሻሚማ ወደ ሶሪያ ስትሄድ አስራ አምስት ዓመቷ ነበር።
በአውሮፓውያኑ 2019 የዩናይትድ ኪንግደምን ብሔራዊ ደኅነትን መሠረት ያደረገ ነው በተባለ ውሳኔ ዜግነቷ ተነጠቀ።
ዜግነት ምንድን ነው?
ዜግነት የአንዲት አገር ውስጥ አባል እና ባለቤት የመሆን ሕጋዊ ሁኔታ ነው።
አንድ ግለሰብ የዩኬ ዜግነት ካለው በአገሪቱ ውስጥ የመኖር እንደ ደኅንነት፣ ትምህርት እና የጤና አጠባበቅን የመሳሰሉ አገልግሎቶችን የማግኘት ሕጋዊ መብት አለው።
በፖለቲካው ዘርፍም መሪን የመምረጥም ሆነ የመመረጥ መብት አለዎት።
ዜግነት የማንነትም መገለጫ ነው።
አንድ ሰው ማንነቱን የሚገልጽበት እና የዚያች አገር ባለቤት እና አባል የመሆን ስሜትም የሚገለጽበት ነው።
አንዳንድ ዜግነት የሌላቸው ሰዎች በዩኬ ውስጥ በርካቶቹን ከዜጎች ጋር ተመሳሳይ የሆኑ መብቶችን አስጠብቀው በቋሚነት የመኖር መብት አላቸው።
በዚህም በአገሪቱ የመኖር መብት ሲሰጣቸው “የተደላደለ ሁኔታ” (ሴትልድ ስታተስ) ይባላል።
ዜግነት እንዴት ይነጠቃል?
መንግሥት በአንዳንድ ሁኔታዎች የአንድን ሰው የዩናይትድ ኪንግደም ዜግነት የመንጠቅ ሥልጣን አለው ይህንንም ለመፈጸም የተወሰኑ መስፈርቶች አሉ።
- “ለሕዝብ ጥቅም” ሲባል እና አገር አልባ የማይሆኑ ከሆነ
- ዜግነታቸውን በማጭበርበር ካገኙ
- ድርጊታቸው የዩኬን ጥቅም ሊጎዳ የሚችል ከሆነ እና በሌላ አገርም ዜግነት ሊጠይቁ የሚችሉ ከሆነ
እነዚህም እርምጃዎች እንደ አልቃይዳ ወይም እስላማዊ መንግሥት ቡድን ባሉ በዩኬ የተከለከሉ ድርጅቶች አባላት ወይም ዜግነታቸውን በማጭበርበር ባገኙ ሰዎች ላይ ከዚህ ቀደም ጥቅም ላይ ውሏል።
ሆኖም እነዚህ ዜጎች በሌላ አገር ዜግነት ለማግኘት ብቁ መሆናቸው መረጋገጥ አለበት።
ዩናይትድ ኪንግደም ዜግነት የነጠቀቻቸው ሰዎች አገር አልባ አለመሆናቸውን የማረጋገጥ የዓለም አቀፍ ሕግ ኃላፊነቶች አሉባት።
ነገር በቅርቡ የፀደቀው የብሔር እና የድንበር ሕግ የአገር ውስጥ ጽህፈት ቤት በተወሰኑ ሁኔታዎች ውስጥ ለግለሰሰቦቹ ሳይገለጽ ዜግነትን የመንጠቅ ሂደትን ቀላል አድርጎታል።
እንደነዚህ ዓይነቶቹ ሁኔታዎች ተግባራዊ የሚሆኑት የብሔራዊ ደኅንነት ስጋቶችን የሚጋርጡ ወይም ግለሰቦቹ በከባድ ወንጀል የተከሰሱ ከሆነ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Tauqir Sharif
ታውቂር ሸሪፍ የተባለ የረድዔት ድርጅት ሠራተኛ በብሔራዊ ደኅነት ምክንያት ዜግነቱን አጥቷል።
በአውሮፓውያኑ 2012 ከባለቤቱ ጋር ወደ ሶሪያ መሄዱን ተከትሎም ከአምስት ዓመታት በኋላ ዜግነቱን ተነጥቋል።
የአገር ውስጥ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሸሪፍ ከአልቃይዳ ጋር ከተሰለፈ ቡድን ጋር ግንኙነት እንዳለውም በመግለፅ ነው ዜግነቱን የነጠቀው።
ታውቂር በበኩሉ የቀረበበት ክስ ፍጹም ሐሰት ነው በማለት የዩኬን ሥርዓት “ፍትሃዊ ያልሆነ” እና “ዘረኛ” ሲልም ጠርቶታል።
የሻሚማ ቤገም ጉዳይ ምን ላይ ደረሰ?
የዩኬ ፍርድ ቤት በአውሮፓውያኑ 2020 የሻሚማ ቤገም ዜግነት መነጠቅ ሕጋዊ ነው ሲል ወስኗል።
ፍርድ ቤቱም ለዚህ የሰጠው ምክንያት “በዘሯ የባንግላዴሽ ዜጋ ነች” ስለዚህ የብሪታንያ ዜግነቷን መንጠቅ አገር አልባ አያደርጋትም ሲል ተከራከረ።
ባንግላዴሽ በበኩሏ ጉዳዩ ይህ እንዳልሆነ እና ወደ አገርም እንድትገባ እንደማይፈቀድላት አስታወቀች።
ሆኖም የዩኬ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሻሚማ ቤገም በውሳኔው ላይ ይግባኝ ለመጠየቅ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም መመለስ እንደማትችል ወስኗል።
በሰሜናዊ ሶሪያ ታጣቂዎች በሚቆጣጠሩት ካምፕ ውስጥ የሚገኙት የሻሚማ ጠበቆች በአሁኑ ወቅት ዜግነት የመነጠቋን ጉዳይ ለልዩ የኢሚግሬሽን ይግባኝ ኮሚሽን (SIAC) አቅርበው እየተሟገቱ ይገኛሉ።
ጠበቆቿ ውሳኔው ሕገ ወጥ ነው በማለት እየተከራከሩ ሲሆን፣ ለዚህም አባሪ አድርገው ያቀረቡት ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ሰለባ አለመሆኗን ያላገነዘበ ነው ብለዋል።
እስካሁን ስንቶች ዜግነታቸውን ተነጥቀዋል?
በዩናይትድ ኪንግደም ምን ያህል ሰዎች ዜግነታቸው እንደተነጠቀ የሚያሳይ አጠቃላይ አሃዝ በቀላሉ አይገኝም።
ነገር ግን ግን የአገር ውስጥ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ከአውሮፓውያኑ 2010 እስከ 2018 ባሉት ዓመታት በአማካይ “ለሕዝብ ጥቅም” ሲባል በየዓመቱ 19 ሰዎች ዜግነታቸውን ተነጥቀዋል።
በተጨማሪም በየዓመቱ በአማካይ 17 ሰዎች በማጭበርበር ምክንያት ዜግነታቸውን እንደተነጠቁ ይፋ አድርጓል።
'ፍሪ ሙቭመንት' የተሰኘው የኢሚግሬሽን ሕግ ድረ-ገጽ ባደረገው ጥናት ከ460 በላይ ሰዎች ከአውሮፓውያኑ 2006 እስከ 2020 ባለው ጊዜ ውስጥ ዜግነታቸው መነጠቁን አስፍሯል።
ከእነዚህም ውስጥ 175ቱ በብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ምክንያት እና 289 በማጭበርበር እንደሆነም ተጠቅሷል።
በሌሎች አገሮችስ ዜግነት እንዴት ይነጠቃል?
በአሜሪካ ለተወለዱ ዜጎች ዜግነት በውልደት የሚገኝ መብት መሆኑ በሕገ መንግሥቱ ስለተረጋገጠ ሊሻር አይችልም።
ነገር ግን በስደት ወደ አሜሪካ ገብተው ዜግነታቸውን ያገኙ ግለሰቦች ዜግነታቸውን ሊነጠቁ ይችላሉ።
በአሜሪካ ዜግነትን ከሚያስነጥቁ ጉዳዮች መካከል በሕግ የታገደ ቡድን አባል መሆን ወይም ዜግነታቸውን በማጭበርበር ማግኘት ይጠቀሳሉ።
በአውስትራሊያ ደግሞ ግለሰቦች ጥምር ዜግነት ካላቸው በብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ምክንያት ዜግነታቸው ሊነጠቅ ይችላል።
ግሪክ፣ ፈረንሳይ እና ሩሜኒያን ጨምሮ በ14 የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት፣ ዜግነት ከአገር ክህደት ጋርና ታማኝነት ካለማሳየት ጋር በተያያዘ እና በሌሎች ብሔራዊ ደኅንነት ስጋቶች ምክንያት ሊነጠቅ ይችላል።
በኔዘርላንድስ ግለሰቦቹን ሳያሳውቁ ዜግነት የሚነጠቅበት አስራር አለ።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዩናይትድ ኪንግደም ከባህሬን በስተቀር ከየትኛውም አገር በላይ የብዙ ሰዎችን ዜግነት በመግፈፍ የሚወዳደራት እንደሌለ 'ኢንስቲስትዩት ኦን ስቴትለስነስ ኤንድ ኢንክሉዥን' የተሰኘው ተቋም ያወጣው ሪፖርት አመልክቷል።












