መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ መበደር የሚችለው የገንዘብ መጠን በአዲስ ረቂቅ ሕግ ሊገደብ ነው

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ

የፎቶው ባለመብት, National Bank of Ethiopia

የምስሉ መግለጫ, የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ

ላለፉት 16 ዓመታት ያለገደብ ከብሔራዊ ባንክ ገንዘብ ሲበደር የነበረው የፌደራል መንግሥት፤ ከአገር ውስጥ ገቢ ከ15 በመቶ የበለጠ ገንዘብ በብድር ማግኘት እንዳይችል የሚገድብ ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ።

ለምክር ቤቱ የቀረበው የብሔራዊ ባንክ ረቂቅ አዋጅ፤ መንግሥት የተበደረውን ገንዘብ በአንድ ዓመት ውስጥ ካልመለሰ ከተቋሙ ሌላ ብድር መውሰድ እንደማይችልም ያስቀመጠ ነው።

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው አዲሱ ረቂቅ አዋጅ፤ መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ ያለገደብ ብድር እንዲወስድ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደውን በ2000 ዓ.ም. የወጣውን አዋጅ የሚቀይር ነው።

የአገሪቱን ማዕከላዊ ባንክ ለመምራት ከ1955 ዓ.ም. ጀምሮ አራት አዋጆች የጸደቁ ሲሆን፣ አሁን በሥራ ላይ ካለው አዋጅ በስተቀር ቀሪዎቹ አራት አዋጆች ለመንግሥት በሚሰጥ የቀጥታ ብድር ላይ ገደብ ያስቀመጡ እና ገንዘቡ የሚመለስበት ጊዜ የወሰኑ ነበር።

በሥራ ላይ ያለው አዋጅ በአንጻሩ፤ “ባንኩ ለመንግሥት እና ለፋይናንስ ተቋማት ብቻ ብድር እንደሚሰጥ ከመግለጽ ውጭ ለመንግሥት በሚሰጠው ቀጥታ ብድር ላይ ግን ምንም ገደብ ሳይጥል በለሆሳስ ያለፈ የመጀመሪያው አዋጅ” እንደሆነ ከአዲሱ ረቂቅ ጋር የቀረበው ማብራሪያ ያስረዳል።

በዚህ አዋጅ ላይ በብሔራዊ ባንክ እና በፌዴራል መንግሥት መካከል የሚኖረው የብድር ሥርዓት በአግባቡ አለመደንገጉ “የነባሩ አዋጅ አንዱ መሠረታዊ ችግር” እንደሆነ በማብራሪያው ላይ ተጠቅሷል።

የፌደራል መንግሥት የሚያጋጥመውን በጀት ጉድለት ለመሸፈን ያለገደብ ብድር እንዲወስድ መደረጉ በገበያ ውስጥ ያለውን የገንዘብ መጠን በመጨመር በአገሪቱ ውስጥ በተከታታይ ዓመታት ለተፈጠረው የዋጋ ግሽበት መንስኤ እንደሆነ የኢኮኖሚ እና ፋይናንስ ባለሙያዎች ሲገልጹ ቆይተዋል።

ይህንን ሀሳብ የሚጋሩት የፋይናንስ ተንታኙ ዶ/ር አብዱልመናን መሐመድ፤ “መንግሥት የበጀት ጉድለት በገጠመው ቁጥር እንደፈለገ [ብድር] ሲወስድ” የነበረ መሆኑ ይህ አሠራር “ከቁጥጥር የወጣ የዋጋ ግሽበት” ማስከተሉን ይናገራሉ።

ሁለት መቶ የብር ኖቶችን የምትቆጥር ሴት እጆች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዶ/ር አብዱልመናን፤ ባለፉት 16 ዓመት ከተከሰተው “ማቆሚያ የሌለው የዋጋ ግሽበት ዋና ምክንያት” መንግሥት ያለገደብ ከብሔራዊ ባንክ ብድር እንዲወስድ መደረጉ እና ገንዘቡ ወደ ኢኮኖሚው መግባቱ እንደሆነ ጠቅሰው ይከራከራሉ።

ባለፉት ዓመታት በየዓመቱ በመቶ ቢሊዮን ብሮችን ከብሔራዊ ባንክ ሲበደር የቆየው የኢትዮጵያ መንግሥት “ዘግይቶም ቢሆን” ነገሩን ተረድቶ በአዲሱ ረቂቅ ላይ ይህንን ገደብ ማቀመጡን እንደሚደግፉት ገልጸዋል። በረቂቅ አዋጁ ላይ ይህ ገደብ የተቀመጠው ብሔራዊ ባንክ ከመንግሥት ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት በሚዘረዝረው የሕጉ ክፍል ላይ ነው።

አዲሱ ረቂቁ፤ ከቀድሞው አዋጅ በተለየ ሁኔታ ብሔራዊ ባንክ “በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለፌዴራል፣ ለክልል፣ ለማንኛዉም የታችኛው የመንግሥት የአስተዳደር እርከን፣ የከተማ አስተዳደር ወይም የመንግሥት ተቋም ብድር” መስጠት እንደማይችል ያስቀምጣል።

የፌደራል መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ ብድር ማግኘት የሚችለው ከ12 ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የሚመመለስ “የኦቨር ድራፍት አገልግሎት” እንደሆነ በረቂቁ ላይ ሰፍሯል። ይህ አይነቱ የብድር አሰጣጥ መንግሥት በተገደበ ጊዜ ውስጥ የተገደበ መጠን ያለው ገንዘብ እንዲያገኝ የሚያስችለው መሆኑን የሚያስረዱት ዶ/ር አብዱልመናን፤ በብዙ አገራት የተለመደ አሠራር መሆኑን ገልጸዋል።

በነባሩ አዋጅ ላይ የሚወሰደው ብድር በምን ያህል ጊዜ ውስጥ እንደሚመለስ አለመደንገጉን የሚያስታውሱት የፋይናንስ ተንታኙ፤ “የኢትዮጵያ መንግሥት በሕይወት ዘመኑ እስከ ሰኔ 2023 ድረስ ወደ 564 ቢሊዮን ብር ከብሔራዊ ባንክ ተበድሯል። መቼ እንደሚመለስ አይታወቅም። የተወሰነው እንደውም ወለድ አይከፈልበትም” ሲሉ አሁን ያለውን አሰራር አስረድተዋል።

አዲሱ ረቂቅ በአንጻሩ መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ በኦቨር ድራፍት አገልግሎት ማግኘት የሚችለው ገንዘብ “ካለፉት ሦስት የበጀት ዓመታት አማካይ ዓመታዊ ጠቅላላ የመንግሥት የአገር ውስጥ ገቢ ከ15 በመቶ መብለጥ” እንደሌለበት አስፍሯል።

ለምሳሌ፤ በ2015 በጀት ዓመት የፌደራል መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ የወሰደው ቀጥታ ብድር 130 ቢሊዮን ብር ነው። አሁን የተዘጋጀው አዋጅ በዚያ ዓመት ሥራ ላይ ውሎ የነበረ ቢሆን ግን መንግሥት ከባንኩ ማግኘት ይችል የነበረው ብድር በግማሽ ይቀንሳል። በአዲሱ አዋጅ ገደብ መሰረት በ2015 መንግሥት መበደር ይችል የነበረው 63.4 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው።

መንግሥት ከባንኩ የሚወስደው ገንዘብ “በገንዘብ ፖሊሲ ተመን ላይ ተመሥርቶ የሚሰላ የወለድ ተመን” እንደሚጣልበት ያሰፈረው አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ረቂቅ አዋጅ፤ ገንዘቡ በ12 ወራት ውስጥ መመለስ እንዳለበትም ይደነግጋል።

“ለመንግሥት የተሰጠ ጊዜያዊ ኦቨር ድራፍት የመክፈያ ጊዜው ሲደርስ ሊከፈል ይገባል እንጂ አይተላለፍም” ሲልም በገንዘቡ አመላለስ ላይ አጽንኦት ይሰጣል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሎጎ

የፎቶው ባለመብት, National Bank of Ethiopia

ከዚህም ባሻገር የፌደራል መንግሥት በቀጣዩ ዓመት ተጨማሪ ገንዘብ ማግኘት የሚችለው በዚህ አገልግሎት የወሰደውን ገንዘብ “በተቀመጠለት የመክፈያ ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ የተከፈለ እንደሆነ ብቻ” መሆኑን ይገልጻል። ከረቂቅ ጋር የቀረበው ማብራሪያ ይህ አንቀጽ የተካተተው “ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲውን በአግባቡ በመተግበር የዋጋ መረጋጋት ማስፈን እንዲችል ነው” በማለት እንደሆነ ያስረዳል።

የፋይናንስ ተንታኙ ዶ/ር አብዱልመናን፤ መንግሥት ገንዘቡን ካልከፈለ ሳይከፍል ተጨማሪ እንዳይወስድ መደረጉን ቢደግፉትም “ከዚህም ጠበቅ ያለ አንቀጽ” ረቂቁ ውስጥ ቢካተት ምርጫቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

“ለምሳሌ [መንግሥት] በብሔራዊ ባንክ ተቀማጭ ገንዘብ አለው። የማይከፍል ከሆነ ወዲያውኑ [ከተቀማጩ] እንዲቀነስበት የሚያደርግ አንቀጽ ቢኖር ጥሩ ነበር” ሲሉ የተሻለ የሚሉትን አማራጭ አቅርበዋል።

ለምክር ቤቱ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ልቅ የነበረው የመንግሥት ብድር ላይ ገደብ ቢያስቀምጥም “ከአቅም በላይ የሆነ ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ” መንግሥት ከገደቡ በላይ የሆነ ገንዘብ ከብሔራዊ ባንክ ሊጠይቅ እንደሚችል አስቀምጧል።

ረቂቁ፤ “ቢያስቀምጥም “ከአቅም በላይ የሆነ ሁኔታ’” በማለት ከሚያስቀምጣቸው ጉዳዮች ውስጥ “ያልተጠበቀ የማኅበረሰብ ጤና፣ የተፈጥሮ አደጋ እና ድርቅ” ይገኙበታል።

“አግባብነት ያለውን ሕግ መሠረት አድርጎ የታወጀ አጠቃላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወይም በፌዴራል መንግሥት ገቢ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ጉልህ የውጭ የኢኮኖሚ ለውጦችም” ተጨማሪ ብድር ለማግኘት የሚያስችሉ ሁኔታዎች ናቸው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እነዚህን ሁኔታዎች መሠረት በማድረግ ተጨማሪ ብድር የሚሰጠው፤ “የዋጋ መረጋጋትን የማረጋገጥ ዓላማ ሳይጣረስ፣ የፌዴራል መንግሥትን የመንግሥት ብድር ጣሪያ ባከበረ መልኩ” እንደሆነ ሰፍሯል።

የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ፤ ይህ ዓይነቱ አማራጭ አሠራር “ከዓለም አቀፍ የተሻለ ተሞክሮ አኳያ የማይመከር” እንደሆነ አልሸገገም። ይሁንና ይህ የልዩ ሁኔታ አሠራር በረቂቅ ውስጥ እንዲካተት የተደረገው የአገሪቱን “ተጨባጭ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት” እንደሆነ ይጠቅሳል።

ይህ ዓይነት ድንጋጌ መኖሩን በበጎ የሚመለከቱት ዶ/ር አብዱልመናን በበኩላቸው፤ “ይህም ቢሆን ግን ግልፅነት፣ ጥብቅ መሆን ያስፈልጋል። መንግሥት ማንኛውንም ክፍተቶች አላግባብ ሊጠቀም ይችላል” ብለዋል።