በዘንድሮ የሃጅ ጉዞ ላይ የአምስት ኢትዮጵያውያን ሕይወት ማለፉ ተገለጸ

መካ

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

ለሃይማኖታዊ ጉዞ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ያቀኑ አምስት ኢትዮጵያውያን በህመም እና በመኪና አደጋ ሕይወታቸውን እንዳጡ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ገለጸ።

በዘንድሮ የሃጅ ጉዞ ተሳታፊ ከነበሩት ኢትዮጵያን ውስጥ “አንድ አዛውንት” በመኪና አደጋ እና አራቱ ደግሞ “በነበረባቸው ህመም እና [በጉዞ] መጨናነቅ” ህይወታቸውን እንዳጡ የምክር ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ዩሱፍ ጌታቻው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ የሱፍ በመኪና አደጋ ምክንያት ህይወታቸው ያለፈው ኢትዮጵያዊ ቀብራቸው በዚያው በሳዑዲ አረቢያ እንደተፈጸም ጠቅሰዋል።

“የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሆስፒታል ሄዶ ሟቹ ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን አረጋግጧል። ያለውን ዶክመንት [ለሳዑዲ አረቢያ መንግስት] ስለሰጠ እዚያው ተቀብረዋል። ቤተሰቦቹንም አርድቷል” ብለዋል።

ሆኖም የተቀሩት ኢትዮጵያዊን “በሳዑዲ ሕግ መሰረት ቤተሰብ እስኪመጣ፣ አንድአንድ ነገሮች እስኪጣሩ ድረስ [ሳይቀበሩ] ይቆያሉ” ሲሉም አክለዋል።

በዘንድሮ 1445ኛው የሃጅ ጉዞ 12 ሺህ ኢትዮጵያውያን ተሳትፈዋል። ለዚህ ሃይኖታዊ ጉዞ ከዓለም ዙሪያ ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ወደ ሳዑዲ አረቢያ ተጉዘዋል።

በጉዞው ቢያንስ 900 የተለያዩ አገራት ዜጎች ህይወታቸውን እንዳጡ እና አብዛኞቹ ከሙቀት ጋር በተያያዘ መሞታቸውን ኤኤፍፒ የዲፕሎማቲክ ምንጮችን ጠቅሶ በዚህ ሳምንት አጋማሽ ዘግቦ ነበር።

ከሟቾች መካከል አብዛኞቹ አፍሪካውያን ሲሆኑ ቢያንስ 323ቱ ግብፃውያን መሆናቸውን ሁለት የአረብ ዲፕሎማቶች ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።

በሳዑዲ አረቢያ ያለው ሙቀት እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ እና ለተጓዦች አስቸጋሪ እንደነበር አቶ የሱፍ ተናግረዋል።

“ከፍተኛ ሙቅት ነበር። አንዳንዴ እስከ 50 [ዲግሪ ሴንቲግሬድ] የሚደርስበት ጊዜ አለ” ያሉት አቶ ዩሱፍ፤ በሙቀቱ ምክንያት ግን “ከኢትዮጵያውያን ሁጃጆች [ተጓዦች] አንድም የሞተ የለም። ምክንያቱም በአብዛኛው ኢትዮጵያዊያኑ የመጡበት አከባቢ ሞቃታማ በመሆኑ ይህንን አየር ሊቋቋም የሚችል ተፈጥሯዊ ባህሪ ያላቸው ይመስለኛል” ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህ ዓመት 1.6 ሚሊዮን የውጭ አገር ዜጎችን ጨምሮ ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ሐጃጆች ወደ ሳዑዲ አረቢያ በተደረገው የሐጅ ጉዞ መሳተፋቸውን የሳዑዲ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

እሑድ ዕለት 2 ሺህ 700 ከሙቀት ጋር የተያያዙ ክስተቶች ተመዝግበዋል።

የሐጅ ጉዞው ባበቃበት ሰኞ ዕለት በመካ ታላቁ መስጂድ የሙቀት መጠኑ እስከ 51.8 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ደርሶ እንደነበር የሳዑዲ አረቢያ ቴሌቪዥን ዘግቧል።

በሙስሊሞች ሕይወት ውስጥ በጣም አስፈላጊ የሆነው የሐጅ ጉዞ ሥርዓት ከአምስቱ የእስልምና እምነት አምዶች መካከል አንዱ ነው።

አቅም ያላቸው ሙስሊሞች በሕይወት ዘመናቸው ቢያንስ አንድ ጊዜ ይህንን ጉዞ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

አንድ ተጓዥ በሃጅ ጉዞ ላይ ሕይወቱ ሲያልፍ ምን ይደረጋል?

አንድ ሰው በሃጅ ጉዞ ላይ በምንም አይነት ምክንያት ሕይወቱ ቢያልፍ ሞቱ ለሃጅ ሚሺን ሪፖርት ይደረጋል።

እጅ ላይ በሚጠለቀው ወይም አንገት ላይ በሚንጠለጠለው መታወቂያ የሟቹ ግለሰብ ማንነት ይለያል። ከዚያ በሃኪም የሞት ምክንያቱ ተለይቶ የሳውዲ አረቢያ መንግሥት የሞት ሰርተፊኬት ይሰጣል።

ሕይወቱ ላለፈው ሰው በእስልምና ሃይማኖት ትልቅ ስፍራ በሚሰጣቸው በመካ በሚገኘው መስጂድ አል-ሃራም ወይም በመዲና በሚገኘው የነብዩ መስጅድ ጸሎት ይደረጋል።

ሟቾች

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

የሳዑዲ መንግሥት ሙሉ ወጪውን ሸፍኖ አስክሬኑ ታጥቦ እና ተጠቅልሎ ማቀዝቀዣ ውስጥ ይገባል።

የቀብር ሥነ-ስርዓቱም የሟቹ ማንነት ከሚገልጽ ማስታወሻ ጋርይፈጸማል። የሟች ቤተሰብ ፍላጎት ካላቸው የመቃብር ቦታውን መጎብኘት ይችላሉ።

ቀይ ጨረቃ በሃጅ ጉዞ ላይ ሕይወታቸው ያሚልፍ ሰዎች “ክብራቸውን በሚመጥን መልኩ የቀብር ስርዓታቸው መፈጸሙን” አረጋግጣለሁ ይላል።