በሶማሊያ የአይኤስ መሪ እንደሆነ የሚታመነው አብዲቃዲር ሙሚን ማን ነው?

የፎቶው ባለመብት, ISIL
በቅርቡ የአሜሪካ የአፍሪካ ወታደራዊ ማዘዣ ማዕከል (አፍሪኮም) ሶማሊያ ውስጥ አካሄድኩት ባለው የአየር ጥቃት ሦስት የአይኤስ አባላትን መግደሉን ይፋ አድርጓል።
ኤንቢሲ ኒውስ በስም ያልተጠቀሱ ሦስት ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው የአየር ጥቃቱ ዒላማ አሜሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአይኤስ መሪ እንደሆነ የምታምነው አብዲቃዲር ሙሚን የተባለው ግለሰብ ነው።
አፍሪኮም ከሦስት ሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ ከሶማሊያ መንግሥት ጋር በመጣመር ከደቡብ ምሥራቅ ሶማሊያ ቦሳሶ ከተማ 81 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ አካባቢ በተፈጸመው የአየር ጥቃት የአይኤስ አባላት መገደላቸውን ገልጿል።
ነገር ግን የጥቃቱ ዒላማ በሶማሊያ ውስጥ የአይኤስ ዋነኛ ሰው የሆነው አብዲቃዲር ሙሚን ስለመሆኑ፣ እንዲሁም በጥቃቱ ከተገደሉት ሦስት የአይኤስ አባላት መካከል አንዱ ሙሚን ስለመሆኑ ያለው ነገር የለም።
አብዱልቃዲር ሙሚን ማነው?
አሜሪካ በይፋ አብዱልቃዲር ሙሚን በሶማሊያ የአይኤስ መሪ ነው ትላለች። ቃላቸው ለኤንቢሲ ኒውስ የሰጡ ሦስት የአገሪቱ ባለሥልጣናት ግን ግለሰቡ በሶማሊያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የአይኤስ (ግሎባል አይኤስ) መሪ እንደሆነ ይታመናል ይላሉ።
እነዚህ ሦስት ኃላፊዎች እንደሚሉት ምንም እንኳ አይኤስ በሶማሊያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተዋጊ ባይኖረውም፤ ቡድኑ አብዛኞቹ ተዋጊዎቹ ባሉበት ሰሜናዊ ኢራቅ እና ሰሜን ምሥራቅ ሶሪያ በአሜሪካ የሚካሄድበትን ከባድ ጥቃትን መቋቋም ተስኖታል።
ስለዚህም አመራሮቹ በተሻለ ነጻነት እየተንቀሳቀሱ ዓለማቸውን ለማስፈጸም ወደሚችሉባት አፍሪካ፣ በተለይም ጠንካራ መንግሥት ወደ ሌላት ሶማሊያ መሪዎቹን ማዘዋወሩን እንደ አማራጭ ወስዶታል ይላሉ።
ከፍተኛው የአሜሪካ ጦር መኮንን አይኤስ በሶማሊያ ያለው የተዋጊዎች ብዛት ከ200 እንደማይሻገር ቢገልጹም፤ ብድኑ በሊቢያ፣ በዴሞክራቲክ ኮንጎ እና ሞዛምቢክ አጋርነታቸውን ለአይኤስ የሰጡ ቡድኖች መኖራቸውን ይገልጻሉ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት እአአ 2016 ላይ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው አብዲቃዲር ሙሚን በምሥራቅ አፍሪካ ለኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) አጋርነቱን የሰጠ የሶማሊያ ታጣቂ ቡድን መሪ ነው።
የአል-ሸባብ የሃይማኖት መሪ እና መልማይ የነበረው ሙሚን፤ ለአይኤስ አጋርነቱን ገልጾ እና አል-ሸባብን ክዶ ወደ 20 የሚጠጉ ተከታዮቹን ይዞ ከወጣ በኋላ በሶማሊያዋ ፑንትላንድ ግዛት መቀመጫውን አድርጓል።
የአሜሪካ የደኅንነት መረጃዎችን እንደሚያመለክቱት ከሆነ የሙሚን ዕድሜ በ70ዎቹ መጀመሪያ ላይ ይገኛል። ግለሰቡ እአአ በ1950-53 እንደተወለደ ይታመናል።
በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ መጀመሪያ የወቅቱ የሶማሊያ አምባገነን መሪ ሲያድ ባሬ በተለያዩ ቡድኖች በተከፈተባቸው ጥቃት ተሸንፈው ከሥልጣን ሲወገዱ እና ሶማሊያ ወደ የእርስ በርስ ጦርነት ስትገባ ሙሚን ከአገር ተሰዶ አውሮፓ መግባቱ ይነገራል።
ሙሚን ጦርነትን ሸሽቶ ስዊድን ለተወሰኑ ዓመታት ከኖረ በኋላ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም በማምራት በሌስትር እና ለንደን ከተሞች ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ኖሯል።
በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ቆይታው ወቅት ትዳር መሥርቷል። ሌስተር እና ለንደን ከተማ በሚገኙ መስጅዶች ውስጥም የሃይማኖት መሪ ሆኖም አገልግሏል።
ይሁን እንጂ በ2000ዎቹ አጋማሽ ሙሚን ከጽንፈኛ ቡድኖች ጋር ግንኙት ሳይኖረውም አይቀርም በሚል የዩኬ የአገር ውስጥ ደኅንነት ተቋም ኤምአይ5 ምርመራ ሲከፈትበት ወደ ሶማሊያ ሸሽቶ ተመለሰ።
አብዲቃዲር ሙሚን ወደ ሶማሊያ ከተመለሰ በኋላ እአአ 2006 ላይ በደቡባዊ ሶማሊያ ውስጥ የአል ሻባብ መነሻ የሆነው እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረትን ተቀላቀለ።

የፎቶው ባለመብት, ISIL
በ2000ዎቹ አጋማሽ ላይ በሶማሊያ ካለው የእስር በእርስ ጦርነት ጋር በተያያዘ ሕገ-ወጥነትን ለማስቀረት ሲባል የሃይማኖት መሪዎች እና የአገር ሽማግሌዎች ሥርዓት ለማስፈን እና ጥፋተኞችን ተጠያቂ ለማድረግ በሚል እስላማዊ ፍርድ ቤቶችን ከአል ሻባብ ጋር ተባብረው ማቋቋማቸው ይታወሳል።
የፍርድ ቤቶቹ አባል የሆነው ሙሚን በተለየ በፑንትላንድ እና በደቡባዊ ሶማሊያ ከተሞች እየተዘዋወረ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን ሲሰጥ እንደነበር ይነገራል።
ከሶማሊያ ግዛቶች መካከል አንዷ የሆችነው የፑንትላንድ አስተዳደር ውስጥ የደኅንነት ኃላፊ የሆኑ ግለሰብ ለቢቢሲ ሶማሊኛ ሲናገሩ “በተለይ በቦሳሶ ከተማ በሚገኙ መስጅዶች ያስተምር ነበር። በዚያ ወቅትም ቢሆን አሁን ላይ ያለው ዓይነት አመለካከት ነበር የሚያረምደው” ብለዋል።
በስም መጠቀስ ያልፈለጉ የሶማሊያ የደኅንነት ባለሥልጣን በእስላማዊ ፍርድ ቤቶቹ እና በአል-ሸባብ መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ሲለያዩ ሙሚን ከጽንፈኛው ቡድን ጋር ማበረን መረጠ ይላሉ።
ለዓመታትም “ወጣቶቹ” የሚል የአረብኛ ስያሜ ያላቸው የአል-ሸባብ የሃይማኖት መሪ እንዲሁም መልማይ ሆነ። ሙሚን የአል-ሸባብ አመራር ከሆነ በኋላም በአደባባይ የዩናይትድ ኩንግደም ፓስፖርቱን ሲያቃጥል ታይቷል።
“አሸባሪው አብድልቃዲር ሙሚን”
በሶማሊያ ከሽብር ቡድኖች ጋር ግንኙነት አላቸው የሚባሉ ሰዎችን በጥብቅ የምትከታተለው አሜሪካ አብዲቃዲር ሙሚንን እአአ 2016 ላይ “ዓለም አቀፍ አሸባሪ ግለሰብ” ስትል ፈርጃዋለች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግለሰቡ በአሜሪካ፣ በአሜሪካ ዜጎች፣ በአገሪቱ ብሔራዊ ደኅንነት፣ የውጭ ፖሊሲ ወይም ኢኮኖሚ ላይ አደጋ ሊጥል ይችላል በሚል ነው “አሸባሪ ግለሰብ” ብሎ የፈረጀው።
ይህ ፍረጃም ሙሚን በአሜሪካ ያለውን ንብረት ከማገዱ በተጨማሪ፣ የትኛውም አሜሪካዊ ከሙሚን ጋር ማንኛውንም ዓይነት ግብይትም ሆነ ግንኙነት እንዳይፈጽም ይከለክላል።
ነገር ግን አብዲልቃዲር ሙሚን ከአል-ሸባብ ጋር ብዙም አልዘለቀም። በሶማሊያ ብቻ እና በምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ ከሚንቀሳቀሰው ቡድን በመውጣት ፊቱን ወደ ዓለም አቀፉ አይኤስ አዞረ።
ሙሚን ወደ አይኤስ ሲቀላቀል ቡድኑ በአቡ በከር አል-ባግዳዲ የሚመራ እስላማዊ መንግሥት (ካሊፌት) በኢራቅ መመሥረቱን ይፋ ካደረገ አንድ ዓመት ሆኖት ነበር። በዚያ ወቅትም አይኤስ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በባሕረ ሰላጤው አገራት ውስጥ ሰፊ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ነበር።
ይህንንም ተከትሎ ሙሚን እአአ 2015 ማብቂያ ላይ በሶማሊያ የአይኤስ ተወካይ በመሆን ቡድን በማዋቀር ዙሪያ የአይኤስ መሪ ከነበረው አል-ባግዳዲ ጋር ንግግር ማድረጉ ይታመና።

የፎቶው ባለመብት, AFP
የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ድረ-ገጽ ላይ እንደተመለከተው በሶማሊያ የአይኤስ ክንፍ (አይኤስ-ሶማሊያ) በሙሚን አማካይነት ከአል-ሸባብ በተገነጠሉ ቡድኖች ተመሥርቶ ከተቋቋመ በኋላ በአይኤስ እውቅና ያገኘው በአውሮፓውያኑ 2018 ነበር።
አይኤስ-ሶማሊያ ልክ እንደ አይኤስ ሁሉ ለእስላማዊ ሕግጋት ጥብቅ ትርጓሜ በመስጠት የአይኤስ የአፍሪካ ካሊፌት ለመመሥረት እንደሚሠራ ይነገርለታል።
ሙሚን ለአል-ቃይዳ አጋርነቱን ከሰጠው አል-ሸባብ ተገንጥሎ ከአይኤስ ጎን መቆሙ በአል-ሸባብ በጠላት ተደርጎ ተፈርጇል።
በዚህም አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን ተከታዮቹን ይዞ በፑንትላንድ ተራራማ አካባቢዎች ከሶማሊያ መንግሥት እና ጥምር ኃይሎች እንዲሁም ከአል-ሸባብ ተዋጊዎች ተሸሽጎ ዓመታትን አስቆጥሯል።
ሙሚን የአይኤስ ተወካይ ነኝ በማለት በእስላማዊ ቡድኑ ውስጥ መከፋፈልን ፈጥሯል በሚል አል-ሸባብ አምርሮ የሚፋለመው ጠላቱ አድርጎ ይመለከተዋል።
የአሜሪካ መንግሥት መረጃ እንደሚያሳየው ሙሚን ዕድሜያቸው ከ10 እስከ 15 የሚሆኑ ወንዶችን እያገተ በመውሰድ በራሱ አስምህሮ በመቅረጽ ወታደራዊ ሥልጣን እንዲወስዱ ያደርጋል።
ሙሚን በቅርብ ዓመታት በይፋ ታይቶ አያውቅም። ለመጨረሻ ጊዜም እአአ 2019 ላይ ቡድኑ በለቀቀው ቪዲዮ ላይ በፑንትላንድ ተራራማ አካባቢዎች ሆኖ ታይቷል።
በቅርቡ በአሜሪካ መራሹ ፀረ-ሽብር እንቅስቃሴ (አፍሪኮም) የአየር ጥቃት የመፈጸሙ ዜና የተሰማው በ70ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው ሙሚን ከባድ የጤና መቃወስ ገጥሞታል እየተባለ በሚነገርበት ጊዜ ነው።
የፑንትላንድ ግዛት የደኅንነት ኃላፊ ለቢቢሲ ሶማሊኛ ሲናገሩ፤ ሙሚን ለሕክምና ወደ ምዕራብ አፍሪካ አገራት በቅርቡ ተጉዟል የሚል መረጃ አለ።
የአይኤስ-ሶማሊያ ጥቃቶች
አብዲቃዲር ሙሚን ታዳጊዎችን አግቶ፣ የራሱን አስምህሮ ታዳጊዎች ላይ በመጫን እና ወታደራዊ ሥልጠና እንዲወስዱ ከማስገደዱ በተጨማሪ በርካታ ጥቃቶችን መፈጸሙን የአሜሪካ መንግሥት መረጃ ያሳያል።
አይኤስ-ሶማሊያ ነጋዴዎን አስገድዶ በግብር መልክ ገንዘብ በመቀበል እንዲሁም ዘረፋዎችን በመፈጸም የሽብር ተግባራቱን ፋይናንስ ያደርጋል ተብሎ ይከሰሳል።
አይኤስ-ሶማሊያ ጥቃት የሚፈጽመው አልፎ አልፎ ነው። የሚፈጽማቸው ጥቃቶችም ከቅርብ ርቀት ላይ ግለሰቦችን መግደል እና በተቀጣጣይ ነገሮች ፍንዳታ መፍጠር ናቸው።
ባለፉት ዓመታት አይኤስ-ሶማሊያ የሶማሊያ መንግሥት ባለስልጣናት፣ በሶማሊያ የሚገኙ ሰላም አስከባሪዎች፣ አል-ሸባብ፣ የፑንትላንድ ግዛት የፀጥታ ሰዎች እና የተጠየቁትን ገንዘብ ለመክፈል ፍቃዳኛ ያልሆኑ ነጋዴዎች ላይ ጥቃት ሲፈጽም ቆይቷል።
ይሁን እንጂ ከአውሮፓውያኑ 2021 ጀምሮ የፑንትላንድ አስተዳደር በዚህ ቡድን እና በአል-ሸባብ ላይ እየወሰደ በሚገኘው የተጠናከረ ዘመቻ በአይኤስ-ሶማሊያ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ቁጥር ቀንሷል።
ሙሚን ሚና በቀጣናው
አንዳንድ ያልተረጋገጡ መረጃዎች አቡ በከር አል ባግዳዲን የተካው የኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ካሊፌት መሪ የሆነው ኤሚር አቡ ሐፍስ አል-ሐሼሚ አል-ቁራሺ በየመን በኩል ከሶሪያ ወይም ከኢራቅ ወደ ሶማሊያዋ ከፊል ራስ ገዝ ፑንት ላንድ ገብቷል ሲሉ ቆይተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም አብዲቃዲር ሙሚን ከሶማሊያ ባሻገር የአጠቃላዩ ኢስላሚክ ስቴት የመሪነት (ካሊፋ) ቦታን እንዲይዝ በቡድኑ ሥልጣን አግኝቷል ቢባልም፣ ነገር ግን በተጨባጭ ይህንን የሚያረጋግጥ መረጃ አልተገኘም።
የሶማሊያው አይኤስ የአል ሻባብን ያህል ጠንካራ ሳይሆን ለረጅም ጊዜ የቆየ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ግን በአገሪቱ ውስጥ ካሉት በመቶዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎች በተጨማሪ በየመን በኩል ከሌሎች አገራት የመጡ ተዋጊዎች እየተቀላቀሉት እንደሆነ ይነገራል።
ይህ ቡድን አማካይ በሆነው ቦታ ላይ ሶማሊያ ውስጥ ከመገኘቱ አንጻር በእስያ ውስጥ ከየመን አስከ አፍጋኒስታን ያለውን የአይኤስ ቡድን እንቅስቃሴን በምሥራቅ አፍሪካ አገራት ውስጥ ከሚገኙት ተመሳሳይ ቡድኖች ጋር በማገናኘት በኩልም ሚና እናዳለው ይታመናል።
በሙሚን የሚመራው አይኤስ-ሶማሊያ ቡድን በአፍሪካ ውስጥ በሶማሊያ፣ በሞዛምቢክ እና በዲሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ ለሚገኙ የአይኤስ ተዋጊዎች የሚውል የጦር መሳሪያ እና የገንዘብ ድጋፎችን በማስተላለፍ ተሳትፏል የሚል መረጃ አለ።












