በሶማሊያ የአይኤስ አባላት የሆኑ 6 ሞሮኳውያን ሞት፣ አንድ ኢትዮጵያዊ ደግሞ እስር ተፈረደባቸው

የፎቶው ባለመብት, SOCIAL MEDIA
ለአይኤስ ለመዋጋት ወደ ሶማሊያ ገብተው ተይዘዋል የተባሉ ስድስት ሞሮኳውያን በሞት እንዲቀጡ ሲወሰንባቸው አንድ ኢትዮጵያዊ ደግሞ የ10 ዓመት እስር ተፈረደበት።
የተከሳሾቹን ጉዳይ የተመለከተው የሶማሊያ ወታደራዊ ፍርድ ቤት በአይኤስ አማካይነት በአገሪቱ ውስጥ ተሰማርተው ተገኝተዋል ብሎ ውሳኔ የሰጠባቸው ስድስት ሞሮኳውያን፣ አንድ ኢትዮጵያዊ እና ሁለት ሶማሊያውያን ናቸው።
ሞት የተፈረደባቸው የሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ሞሮኮ ዜጎች በአንድ ወር ውስጥ ይግባኝ አቅርበው ተቀባይነት ካላገኙ በጥይት ተረሽነው ፍርዱ ተግባራዊ ይሆናል።
የወታደራዊው ፍርድ ቤት ምክትል ሊቀመንበር ኮሎኔል አሊ ኢብራሂም “ግለሰቦቹ ወደ ሶማሊያ የመጡት አይሲስ [ኤይኤስ] ደም እንዲያፈስ እና አገሪቱን እንዲያወድም ለማገዝ ነው” ማለታቸው ተዘግቧል።
ሞት የተፈረደባቸው ሞሮኳውያን አይኤስን እንዲቀላቀሉ መታለላቸውን እና ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እንዲደረግ መጠየቃቸውን የተከሳሾቹ ጠበቃ ተናግረዋል።
የግለሰቦቹ ክስ የታየባት የከፊል ራስ ገዟ የፑንትላንድ ባለሥልጣናት ወደ አይኤስ ሊቀላቀሉ ነበር የተባሉ የውጭ ዜጎችን ሲከሱ እና ቅጣት ሲበይኑ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ተብሏል።
ወታደራዊው ችሎት ሞት ከፈረደባቸው ስድስት ሞሮኳውያን ጋር የአንድ ኢትዮጵያዊ እና የሶማሊያዊ ጉዳይን ተመልክቶ በእያንዳንዳቸው ላይ የ10 ዓመት እስር ሲበይን፣ ሌላኛው ሶማሊያዊ ደግሞ በቂ ማስረጃ አልቀረበበትም በማለት በነጻ አሰናብቷል።
ክሱን ሲከታተሉ ከነበሩት ዓቃብያነ ህግ መካከል አንዱ ለቢቢሲ ሶማሊኛ እንደገለጹት፣ ታጣቂዎቹ የተያዙት የፑንትላንድ የንግድ ማዕከል ከሆነችው ቦሳሶ በስተምሥራቅ በሚገኝ ተራራማ ቦታ ላይ ነው።
ተራሮቹ አይኤስ ጠንካራ ይዞታ መሆናቸው የሚነገር ሲሆን፣ በስፍራውም ቡድኑ ወታደራዊ ሠፈር አለው።
በሶማሊያ የአይኤስ ቅርንጫፍ ከዘጠኝ ዓመት በፊት የተመሠረተው ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት ካለው እና የአገሪቱ ዋነኛው ጂሃዲስት ቡድን ከሆነው ከአልሻባብ ተገንጥለው በወጡ ታጣቂዎች ነው።
በሶማሊያ ያለው የአይኤስ ቡድን ከነዋሪዎች ገንዘብ በማስገደድ የሚሰበስብ ሲሆን፣ አነስተኛ መጠን ያላቸው ጥቃቶችን አልፎ አልፎ የሚፈጽም መሆኑን የአሜሪካ ብሔራዊ መረጃ ጽህፈት ቤት አመልክቷል።
ነገር ግን የሞት ቅጣቶች እንዲቀሩ በርካታ የሶማሊያ እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቡድኖች ጥሪ ሲያቀርቡ ቢቆዩም፣ ከሽብርተኝነት ጋር በሚገናኝ ወንጀል በሚዙ ሰዎች ላይ የሞት ቅጣት መበይን የተለመደ ነው።
የመብት ቡድኖች ባለፈው የካቲት ወር ባወጡት ሪፖርት መሠረት ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት በሶማሊያ በ55 ሰዎች ላይ የሞት ቅጣት ተፈጽሟል።
ከእነዚህም ውስጥ 23 የሞት ቅጣቶች የተፈጸሙት በፑንትላንድ እና በዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ ውስጥ ነው።












