ሞቃዲሾ ውስጥ በተፈጸመ ጥቃት የአረብ ኤምሬትስ እና የባህሬን የጦር መኮንኖች ተገደሉ

በጥቃቱ የተገደሉ የኤምሬትስ መኮንኖች አስከሬን ወዲያው ወደ አገራቸው ተወስዷል

የፎቶው ባለመብት, WAM

የምስሉ መግለጫ, በጥቃቱ የተገደሉ የኤምሬትስ መኮንኖች አስከሬን ወዲያው ወደ አገራቸው ተወስዷል

በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ በሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ በተፈጸመ ጥቃት የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ እና የባህሬን መኮንኖችን ጨምሮ አምስት የጦር መኮንኖች መገደላቸው ተገለጸ።

ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ በተፈጸመው ጥቃት ሦስት የኤምሬትስ፣ አንድ የባሕሬን እና የሶማሊያ የጦር መኮንኖችን ጨምሮ ቢያንስ አምስት ሰዎች መገደላቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ቢቢሲ ሶማሊኛ አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ካልፈቀዱ የደኅንነት እና የስለላ ባለሙያ ባገኘው መረጃ መሠረት በጥቃቱ ከተገደሉት የአረብ ኤምሬትስ የጦር መኮንኖች መካከል ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ይገኙበታል።

በሶማሊያ ውስጥ ኤምሬቶች ካላት ሚና አንጻር ወሳኝ ሚና የነበራቸው ከፍተኛው ወታደራዊ መኮንን ኮሎኔል ሞሐመድ አል ማንሱር በጥቃቱ ከተገደሉት አንዱ ናቸው በማለት ምንጩ ገልጸዋል።

ከዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ መንግሥት የወጣ መግለጫ እንዳመለከተው “የሽብር ድርጊት” ባለው ጥቃት የተገደሉት መኮንኖች የሶማሊያ ኃይሎችን በማሠልጠን ተልዕኮ ላይ ሳሉ ነበር።

ጥቃቱን የፈጸመው ግለሰብ ወደ ወታደራዊ ሠፈሩ በመግባት አሠልጣኞችን ዒላማ በማድረግ ተኩስ ከፍቶ ነው አምስት ሰዎችን ገድሎ ሁለት ሌሎችን ማቁሰሉን አንድ ወታደራዊ መኮንን እና የሆስፒታል ሠራተኛን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል።

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ጥቃቱን “አስከፊ የሽብር ድርጊት” በማለት አውግዘው፣ ሶማሊያን ከሽብርተኝነት ነጻ በማውጣት እና ሠራዊቱን መልሶ በመገባት ሂደት መስዋዕትነት የከፈሉ ላሏቸው መኮንኖች አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

የጥቃቱን አስመልክቶ መግለጫ ያወጣው የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ የመከላከያ ሚኒስቴር ከተገደሉት መኮንኖች አሃዝ ውጪ ዝርዝር መረጃ ያልሰጠ ሲሆን፣ ጥቃቱን ለመመርመር “ከሶማሊያ መንግሥት ጋር የሚያደርገው ትብብር እንደሚቀጥል” አመልክቷል።

በአረብ ኤምሬትስ በሚመራው የጦር ሰፈር ውስጥ ተኩስ ከፍቶ መኮንኖችን የገደለው እና ጉዳት ያደረሰው አህመድ በሚል ስም ብቻ የተገለጸው አዲስ ሠልጣኝ ወታደር ጥቃቱን በፈጸመበት ጊዜ ተተኩሶበት ተገድሏል።

“ወታደሩ አሠልጣኝ የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ እና የሶማሊያ ወታደራዊ መኮንኖች በጸሎት ላይ ሳሉ ነበር ተኩስ የከፈተው። በጥቃቱ አራት የኤምሬትስ መኮንኖች ሲቆስሉ፣ አራት የሶማሊያ ወታደሮች ተገድለዋል” ሲል አንድ መኮንን ለሮይተርስ ገልጿል።

መኮንኑ ጨምሮም ጥቃት ፈጻሚው ወታደር በሶማሊያ እና በአረብ ኤምሬት ተመልምሎ ወደ ሥልጠና ከመግባቱ በፊት ከአል ሻባብ የከዳ የቡድኑ አባል ነበር።

ከአል ቃኢዳ ጋር ትስስር ያለው አል ሻባብ ባወጣው መግለጫ ለጥቃቱ ኃላፊነቱን የወሰደ ሲሆን፣ ተዋጊዎቹ 17 ወታደሮችን መግደላቸውን ገልጿል።

ከተገደሉት ወታደራዊ መኮንኖች በተጨማሪም አስር የሶማሊያ ወታደሮች ቆስለው ወደ ህክምና መወሰዳቸውን የሆስፒታል ምንጮች ለሮይተርስ ተናግረዋል።

አል ሻባብ ሰፊ የሶማሊያ ግዛትን ተቆጣጥሮ በደካማው የሶማሊያ መንግሥት ላይ ዋና ከተማዋን ጨምሮ ከአስር ዓመታት በላይ የሽምቅ ጥቃቶችን ሲፈጽም ቆይቷል።

ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በከፈቱት ተከታታይ ዘመቻ አልሻባብ ከባድ ሽንፈት ገጥሞት ከአንዳንድ ይዞታዎቹ ለመልቀቅ ተገዷል።

ቢሆንም ግን ቡድኑ አሁንም በመንግሥት ኃይሎች እና በሌሎችም ላይ ከባድ ጥቃቶችን እየፈጸመ ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑን ቀጥሏል።