የሶማሊያ መንግሥት ወታደሮች እና አልሻባብ ከባድ ውጊያ እያካሄዱ መሆኑ ተዘገበ

የወታደር መኪና

የፎቶው ባለመብት, AFP

በሶማሊያ መንግሥት ወታደሮች እና በአልሻባብ ታጣቂዎች መካከል ሙዱግ በተባለው በአገሪቱ ማዕከላዊ ክልል ውስጥ ከባድ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑ ተዘገበ።

ከአል ቃኢዳ ጋር ግንኙነት ያለው ታጣቂው ቡድን አልሻባብ፣ ዛሬ ረቡዕ ማለዳ በመንግሥት ወታደሮች ላይ ፈጸምኩት ባለው ጥቃት ወደ ሁለት መቶ የሚደርሱ ወታደሮችን ገድያለሁ ብሏል።

በርካታ የሶማሊያ አካባቢዎችን ተቆጣጥሮ የሚገኘው አልሻባብ በጥቃቱ ከ190 በላይ የሶማሊያ መንግሥት ወታደሮችን መግደሉን ቢገልጽም አሃዙ በገለልተኛ ወገን አልተረጋገጠም።

የሶማሊያ መንግሥት በማዕከላዊ እና በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ሰፊ ቦታዎችን በተቆጣጠረው እስላማዊው ታጣቂ ቡድን ላይ ባለፉት ወራት ጥቃቶችን ሲያካሂድ ቆይቷል።

የአልሻባብ ታጣቂዎች በማዕከላዊ ሶማሊያ ውስጥ በምትገኝ አንድ መንደር ላይ ሰፍረው በነበሩ የመንግሥት ኃይሎች ድንገተኛ ጥቃት የፈጸሙት ዛሬ ማለዳ ነው።

ታጣቂው ቡድን ጥቃቱን የከፈተው የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ፍንዳታ በማድረስ ሲሆን፣ በማስከተልም እስከ ንጋት የቀጠለ ከባድ ውጊያ መካሄዱ ተዘግቧል።

የዐይን እማኞች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ በሙዱግ ክልል ውስጥ በምትገኘው አንድ መንደር ፍንዳታዎች እና ከባድ የተኩስ ልውውጥ ሰምተዋል።

አሁን በመንግሥት ወታደሮች ላይ ድንገተኛ ጥቃት በአልሻባብ የተፈጸመበት አካባቢ በሶማሊያ መንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ስር የገባችው ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር።

ባለፈው ዓመት ወደ ሥልጣን የመጡት ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሚሐሙድ ከአል ቃኢዳ ጋር ግንኙነት ባለው ታጣቂው አልሻባብ ላይ ከወራት በፊት ወታደራዊ ዘመቻ ሲከፍቱ ቡድኑን በወራት ውስጥ ለማጥፋት ቃል ገብተው ነበር።

ደካማውን የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት ክፉኛ እየተፈታተነ ያለው አልሻባብ ከባድ የቦምብ ጥቃቶችን በዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት በመፈጸም የመንግሥት ባለሥልጣናትን፣ የፀጥታ ኃይሎችን እንዲሁም ሰላማዊ ሶማሊያውያንን ሲገድል ቆይቷል።

መንግሥት በቡድኑ ላይ ባለፉት ወራት ባካሄደው ዘመቻ ጥቂት የማይባሉ ቦታዎችን ማስለቀቅ ቢችልም፣ አሁንም በርካታ የሶማሊያ አካባቢዎች በአልሻባብ ቁጥጥር ስር ይገኛሉ።

በእስላማዊ ታጣቂዎች ስጋት ውስጥ የገባውን የሶማሊያን መንግሥት ለመጠበቅ እና ለማጠናከር በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር የተለያዩ አገራት ወታደሮች በአገሪቱ ተሰማርተው ይገኛሉ።

እነዚህ ከአስር ዓመታት በላይ በሶማሊያ ውስጥ አልሻባብን ሲዋጉ የቆዩት የአህጉራዊ ድርጅቱ ኃይሎች ቀስ በቀስ ይዞታቸውን ለሶማሊያ ሠራዊት እያስረከቡ ሲሆን፣ ባለንበት የአውሮፓውያን ዓመት ማብቂያ ላይ ከፊሎቹ ከሶማሊያ ይወጣሉ ተብሏል።