የተባበሩት መንግሥታት ሄሊኮፕተር እና ተሳፋሪዎች በአል ሸባብ ቁጥጥር ሥር ዋሉ

የአል ሸባብ ታጣቂዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የበረራ ሠራተኞችን ጨምሮ ስምንት ሰዎችን የጫነ የተባበሩት መንግሥታት ሄሊኮፕተር በታጣቂው አል ሸባብ ቁጥጥር ሥር መዋሉን ምንጮች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ሄሊኮፕተሩ ማዕከላዊ ሶማሊያ በአል ሸባብ ቁጥጥር ሥር ካለ ሥፍራ ማረፉን ተከትሎ ነው ሠራተኞቹ በቡድኑ ቁጥጥር ሥር የዋሉት።

በሶማሊያ የተባበሩት መንግሥታት ሚሽን [ዩኤንሶም] በኮንትራክት የያዘው ሄሊኮፕተር አስቸኳይ ሕክምና ለመስጠት በሄደበት “የአቪየሽን ክስተት” እንደገጠመው አረጋግጧል።

ዩኤንሶም፤ ምንም እንኳ የአል ሸባብን ስም ባይጠቅስም “ምላሽ ለመስጠት ሙከራ እያደረግን ነው” ብሏል።

ኤኤፍፒ የዜና ወኪል የተባበሩት መንግሥታትን ማሕደር ተመልክቶ በሠራው ዘገባ ሄሊኮፕተሩ በገጠመው እክል ምክንያት ከዱሳምሬብ ደቡብ ምስራቅ 70 ኪሎ ሜትር አቅጣጫ አርፏል ብሏል።

የዜና ወኪሉ አክሎ በሄሊኮፕተሩ ውስጥ የተባበሩት መንግሥታት ሠራተኞች ሳይሆኑ ተቀጥረው የሚሠሩ ሶስተኛ ወገን ኮንትራክተሮች እንደነበሩ ዘግቧል።

በሄሊኮፕተሯ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ዜግነት እስካሁን ግልጥ አይደለም። እርግጥ ቁጥራቸውም ስንት እንደሆነ አልታወቀም።

ከተሳፋሪዎቹ መካከል አንድ ግብፃዊ ሲገደል ሁለቱ ደግሞ ማምለጣቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

አብዛኛው ማዕከላዊ እና ደቡባዊ የሶማሊያ ክፍል በታጣቂው አል ሸባብ ቁጥጥር ሥር ነው የሚገኘው።

አልሻባብ ሶማሊያ ውስጥ በስፋት የሚንቀሳቀስ ታጣቂ ኢስላማዊ ቡድን ሲሆን፣ ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው በይፋ ይናገራል።

የጋልሙዱግ ክልል ፀጥታ ሚኒስትር መሐመድ አብዲ ሄሊኮፕተሩ በአል ሸባብ ቁጥጥር ሥር መዋሉን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ሁለት ሶማሊያዊያን እና በርካታ የውጭ ሀገር ዜጎች ሄሊኮፕተሯ ውስጥ እንደነበሩ የሶማሊ ጦር መኮንን ሜጀር ሐሰን አብዲ አዳን ለሮይተርስ ተናግረዋል።

“በተጨማሪ የሕክምና ቁሳቁሶችን የጫነ ሲሆን ጉዳት የደረሰባቸውን ወታደሮች ከጋልጉዱድ ግዛት ይዞ ለመውጣት ነበር ወደ ሥፍራው ያቀናው” ብለዋል።

ሄሊኮፕተሩ ዊሲል ወደተሰኘችው ከተማ እያቀና ነበር። ሥፍራው መንግሥት ከአል ሸባብ ታጣቂዎች ጋር የሚፋለምበት ነው።

የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ፕሮግራም [ደብሊውኤፍፒ] ረቡዕ ምሽት በማሕበራዊ ሚድያ ገፁ በለጠፈው መልዕክት ሄሊኮፕተሩ “የደብሊውኤፍፒ አይደለም፤ የተባበሩት መንግሥታት የአየር ሰብዓዊ እርዳታ አገልግሎትም አይደለም። የደብሊውኤፍፒ ሠራተኞችም በውስጡ የሉም” ብሏል።

ድርጅቱ አክሎ ወደ ሥፍራው የሚያደርገውን በረራ ሙሉ በሙሉ ማቋረጡን ገልጧል።

የሶማሊያ መንግሥት በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አል ሸባብ የተሰኘው ኢስላማዊ ታጣቂ ቡድን ላይ የሚያደርገውን ዘመቻ አጠናክሮ ቀጥሏል።

ቡድኑ በሶማሊያ ውስጥ የብዙ ሰዎችን ሕይወት ያጠፉ በርካታ የቦምብ እና የደፈጣ ጥቃቶችን ሲፈጽም ቆይቷል።

አልሻባብ ከሶማሊያ ባሻገር ኬንያ ውስጥ ተደጋጋሚ ከባድ የሽብር ጥቃቶችን የፈጸመ ሲሆን፣ ጥቃቱ እስከ ኡጋንዳ ድረስ የዘለቀ ነው።