ሶማሊያ እና ቱርክ የወታደራዊ ትብብር ስምምነት ተፈራረሙ

የሶማሊያ እና የቱርክ የመከላከያ ሚኒስትሮች (አብዲካዲር ሞሐመድ ኑር እና ያሳር ጉለር)

የፎቶው ባለመብት, Abdulkadir Mohamed Nur

የምስሉ መግለጫ, የሶማሊያ እና የቱርክ የመከላከያ ሚኒስትሮች (አብዲካዲር ሞሐመድ ኑር እና ያሳር ጉለር)

የሶማሊያ እና የቱርክ መንግሥታት በተለያዩ ወታደራዊ ዘርፎች ትብብር ለማድረግ ስምምነት መፈራረማቸውን ይፋ አደረጉ።

ይዘቱ በዝርዝር ያልተገለጸው የሁለቱ አገራት ስምምነት የመከላከያ ሚኒስትሮቻቸው በተገኙት መፈረሙን የሶማሊያ የዜና ወኪል እና የቱርክ መከላከያ ሚኒስቴር ገልጸዋል።

የሶማሊያ ዜና ወኪል (ሶና) ታሪካዊ ሲል የገለጸው ስምምነት የተፈረመው ሞቃዲሹ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር በደረሰችው የባሕር ጠረፍ የማግኘት ስምምነት ከአዲስ አበባ ጋር ውጥረት ውስጥ በገባችበት ወቅት ነው።

ስምምነቱ በቱርክ መዲና አንካራ በሚገኘው የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ሲፈረም የቱርክ የመከላከያ ሚኒስትር ያሳር ጉለር “ሶማሊያ በአፍሪካ የቱርክ ወሳኝ አጋር ነች” ብለዋል።

ሚኒስትሩ ከሶማሊያው አቻቸው ጋር ውጤታማ የሆነው ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸው፣ በበውይይታቸው ላይ “የሶማሊያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት አስፈላጊነት ላይ ተነጋግረናል” ስለማለታቸው የቱርክ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የሶማሊያ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው ስምምነቱ የሶማሊያን እና የቀጠናውን ደኅንነት የማጠናከር ዓላማ ያለው ነው ብሏል።

የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር አብዲካዲር ሞሐመድ ኑር “ለሶማሊያ ሕዝብ እና መንግሥት የቱርክ መንግሥት ለሚያደርገው የማይቋረጥ ወንድማዊ ድጋፍ” ምስጋና ማቅረባቸውን የዜና ወኪሉ ዘግቧል።

ሁለቱ የመከላከያ ሚኒስትሮች በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ የመከላከያ እና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸውን እንዲሁም የሁለቱን አገራት የሁለትዮሽ ወታደራዊ ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውን ከስምምነቱ መፈረም በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።

የሶማሊያው መከላከያ ሚኒስትር አብዱልቃዲር ሙሐመድ ኑር በአንካራ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል የቱርክ አቻቸውን አመስግነው፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን እአአ 2011 ላይ ሶማሊያን ከጎበኙ በኋላ ይበልጥ መጠናከር ጀምሯል ብለዋል።

የሶማሊያው መከላከያ ሚኒስትር በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰው ስምምነት ተከትሎ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ስምምነቱ “ሽብርን ለመዋጋት እና ወታደራዊ የፋይናንስ” ትብብርን እንደሚጨርም አመልክተዋል።

ቱርክ አሁን ከሶማሊያ ጋር ውዝግብ ከገባቸው ኢትዮጵያ ጋር ከሁለት ዓመት በፊት ወታዳራዊን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ስምምነቶችን መፈራረሟ ይታወሳል።

ከአንድ ወር በፊት እራሷን ነጻ አገር አድርጋ ያወጀችው ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ የባሕር መተላለፊያ ለመስጠት እና ከኢትዮጵያ የአገርነት እውቅናን ለማግኘት የተፈራረመችው ስምምነት የሶማሊያ መንግሥትን አስቆጥቷል።

በዚህም ሳቢያ ሶማሊያ ኢትዮጵያ ከግዛት አካሌ ጋር ስምምነት በማድረግ ሉዓላዊነቴን ተጋፍታለች ስትል በመውቀስ ጉዳዩን ወደ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት የወሰደች ሲሆን፣ ቱርክን ጨምሮ የተለያዩ አገራትም የሶማሊያ ሉዓላዊነት እንዲከበር ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።