በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት የ14 የሐጅ ተጓዦች ሕይወታቸው አለፈ

የሐጅ ተጓዦች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሳዑዲ አረቢያ በሐጅ ጉዞ ወቅት ቢያንስ 14 የዮርዳኖስ ዜጎች በከባድ ሙቀት ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉን ባለስልጣናት ገለጹ።

የዮርዳኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው 14 ዜጎቹ “በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት በጸሃይ ስትሮክ ተጠቅተው” ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን 17 ዜጎቹ ደግሞ አድራሻቸው መጥፋቱን ገልጿል።

የኢራን ቀይ ጨረቃ በበኩሉ አምስት ኢራናውያን የሐጅ ተጓዞች ህይወታቸውን ማጣታቸውን ቢገልጽም የሞታቸውን ምክንያት አልገለጸም ሲል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

የጠፉትን ሰዎች ለማግኘት የሚደረገው ፍለጋ መቀጠሉን የዮርዳኖስ ባለስልጣናት ገልጸዋል።

የዮርዳኖስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በቤተሰቦቻቸው ፍላጎት መሠረት የሟቾችን አስከሬን ለመቅበር ወይም ወደ አገራቸው ለማጓጓዝ ከሳዑዲ ባለስልጣናት ጋር በመሥራት ላይ መሆኑን ገልጿል።

ሐጅ በዓለም ላይ በርካታ ሰዎች ከሚሰባሰቡባቸው ክስተቶች አንዱ ነው። በዚህ ዓመት ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ተጓዦች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን የሳዑዲ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

የድንኳን ቃጠሎ እና መረጋገጥን ጨምሮ በጉዞው ላይ የሰዎች ሕይወት የሚያልፍበት አጋጣሚ አለ። በአብዛኛዎቹ ዓመታት ዋናው ፈተና የሆነው ከኃይለኛው ሙቀት ነው።

በዚህ ሳምንት የሙቀት መጠኑ ከ 46 ዲግሪ በመብለጡ፣ ብዙዎቹ ከቤት ውጭ እና በእግር ጉዞ የሚደረጉ የአምልኮ ሥርዓቶች በተለይ ለአረጋውያን ፈታኝ ሆኖባቸዋል።

የሳዑዲ ብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ማዕከል ኃላፊ አይማን ጉላም “በዚህ ዓመት በሐጅ ወቅት የሚጠበቀው የአየር ንብረት በመካ እና በመዲና ከመደበኛው በላይ ከ1.5 እስከ 2 ዲግሪ (ሴልሽየስ) ይጨምራል” ሲሉ ባለፈው ሳምንት አስጠንቅቀዋል።

ሁለቱ ከተሞች ለአምስት ቀናት በሚቆየው የሐጅ ጉዞ ማዕከል ናቸው።

በአረፋ ተራራ አቅራቢያ በሚገኝ የሕክምና ማዕከል 225 በሙቀት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ሕክምና እንደተሰጣቸው የሳዑዲ ፕሬስ ኤጀንሲ ዘግቧል።

“ይህ ለአካል ከባድ ቢሆንም በጣም በመንፈሳዊነት የተሞላ ነው” ሲል ካናዳዊው የሐጅ ተጓዥ ኔሮን ካን ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግሯል።

የሐጅ ጉዞው ረቡዕ ይጠናቀቃል። የሳዑዲ ባለስልጣናት ውሃ ከማከፋፈል በተጨማሪ ተጓዦች እራሳቸውን ከጸሐይ እንዴት መጠበቅ እንደሚችሉ ምክር ይሰጣሉ።

የሳዑዲ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተጓዦች በቂ ውሃ እንዲጠጡ እና ከቀኑ 4፡00 ሰዓት እስከ 10፡00 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ከቤት ውጭ እንዳይሆኑ ጠይቋል።

ባለፈው አመት ቢያንስ 240 ሰዎች ሞተዋል። በሰዎች ሞት ብዛት አስከፊው የተባለው የሐጅ ጉዞ በ2015 የተመዘገበ ሲሆን ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎችን ሞተዋል።