ዜሌንስኪ ሩሲያ ከዩክሬን ጠቅልላ ከወጣች “የሰላም ንግግር ነገ መጀመር እንችላለን” አሉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ የሩሲያ ጦር ከአገሪቱ ግዛቶች ጠቅልሎ የሚወጣ ከሆነ ኪዬቭ ከሞስኮ ጋር “የሰላም ንግግር ነገ መጀመር ትችላለች” አሉ።
ዜሌንስኪ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም በስዊትዘርላንድ በተጠራ ስብሳባ ማጠቃለያ ላይ ባደረጉት ንግግር የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ይህን ጦርነት የማስቆም ፍላጎት ጨርሶ የላቸውም ብለዋል።
ፑቲንን በወታደራዊ አማራጭም ሆነ በዲፕሎማሲያዊ መንግድ ማስቆም አለብን ሲሉ ዜሌንስኪ ጨምረው ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው ከሩሲያ ጋር ለገቡት ጦርነት ከምዕራባውያኑ የሚያገኙት ድጋፍ በቂ አለመሆኑን ገልጸው የስዊትዘርላንዱ ስብሰባ ግን ዓለም አቀፉ ማሕብረሰብ ለአገራቸው የሚሰጠው ድጋፍ አለመቀነሱን ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
በስዊትዘርላንዱ ስብሰባ የዩናይትድ ኪንግደም፣ የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የካናዳ መሪዎች እና የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንትን ጨምሮ ከ90 በላይ አገራት ተሳታፊ ሆነዋል።
ጦርነቱን ለማስቆም ለሁለት ቀናት ሲካሄድ በቆየው ውይይት ሩሲያ አልተጋበዘችም። ቻናይ በበኩሏ በስብሰባው ሞስኮ የማትገኝ ከሆነ ለመገኘት ፍቃደኛ አይደለሁም ብላ ቀርታለች።
ለሁለት ቀናት ሲደረግ የነበረው ስብሰባ ሲጠናቀቅ ተሳታፊዎች ባወጡት የውሳኔ ሃሳብ ላይ የዩክሬን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲከበር ጠይቀው ሞስኮ ዩክሬንን በኒውክለር ጦር መሳሪያ ማሸበር ማቆም አለባት ብለዋል።
ይሁን እንጂ የስብሰባው ተሳታፊ ከሆኑ አገራት መካከል ሕንድ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሳዑዲ አረቢያ በውሳኔ ሃሳቡ ላይ ፊርማቸውን አላኖሩም።
ይህ የውሳኔ ሃሳብ በሩሲያ ቁጥጥር ስር የሚገኘው የዛፖሬዢያ የኒውክለር ማብላያ ጣቢያ ተመልሶ በዩክሬን ቁጥጥር ስር እንዲገባ ጠይቋል።
የሩሲያን ዘመቻም “ጦርነት” ሲል ይገልጸዋል። ሠነዱ በሁለቱ አገራት መካከል የእስረኛ ለውውጥ እንዲደረግ እንዲሁም ሞስኮ “አፍና” የወሰደቻቸውን ልጆች እንድትለቅ ይጠይቃል።
ይህ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ከመደረጉ ከሁለት ቀናት ቀደም ብሎ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን ላይ ለከፈቱት ዘመቻ ማብቂያ ይሆናል ያሉትን ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠው ነበር።
የዩክሬን መንግሥት በሩሲያ ከተያዙት አራቱ ክልሎች ማለትም ከዶኔስክ፣ ሉሃንስክ፣ ኼርሶን እና ዛፖሬዢያ ለቆ መውጣት እንዲሁም ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል የመሆን ፍላጎቷን ጨርሳ መተው አለባት ሲሉ ቭላድሚር ፑቲን ለተኩስ አቁም ስምምነት ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጠዋል።
“ኪዬቭ በእነዚህ ቅደመ ሁኔታዎች ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ ዝግጁ ስትሆን በእኛ በኩል ተኩስ እንዲቆም እና ድርድር እንዲጀመር ትዕዛዝ እናስተላልፋለን” ብለዋል ፑቲን።
ይሁን እንጂ ይህ የፑቲን ቅድመ ሁኔታ በዩክሬንም ሆነ በምዕራባውያን አገራት ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።












