የፍርድ ቤቶችን ሥልጣን ይሻማሉ፣ የዜጎችን መብት ይገድባሉ የተባሉት ረቂቅ አዋጆች የፈጠሩት ስጋት

የተወካዮች ምክር ቤት

ባለፉት ሳምንታት የተለያዩ ረቂቅ አዋጆች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤ ቀርበዋል። ከእነዚህ አዋጆች መካከል ገሚሶቹ ሲጸድቁ ቀሪዎቹ ደግሞ ለሚመለከቷቸው ቋሚ ኮሚቴዎች ተመርተዋል።

ለምክር ቤቱ ከቀረቡት ሕጎች መካከል ሦስት ረቂቅ አዋጆች ከሰሞኑ መነጋገሪያ ሆነዋል። እነዚህ አዋጆች አስፈጻሚ አካሉ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እና ማመልከቻ በገደብ እርምጃዎችን እንዲወስድ መፍቀዳቸው ያመሳስላቸዋል።

እነዚህ ረቂቅ አዋጆች፤ የኢሚግሬሽን አዋጅ ማሻሻያ፣ በወንጀል የተገኘ ንብረት ሕጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀል ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣው ረቂቅ አዋጅ እና የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ናቸው።

በእነዚህ አዋጆች መሠረት አስፈጻሚው አካል ከዚህ ቀደም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ብቻ ይተላለፉ የነበሩ ዕግዶችን እና ውሳኔዎችን መውሰድ ይችላል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሕግ እና የሰብዐዓዊ መብት ባለሙያዎች እነዚህ የሕግ ማሻሻያዎች እና ረቂቆች “በጥንቃቄ ሊታዩ ይገባል” የሚል አስተያየት አላቸው።

አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የሕግ መምህር እና ባለሙያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ፤ “ተቋማትን መገንባት፣ ሕጎች የዜጎችን መብቶች እና ሕገ መንግሥትን ያከበሩ እንዲሆኑ ማድረግን” ታሳቢ ያደረገ የሕግ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ያስታውሳሉ።

እኒሁ የሕግ መምህር “በዚህ ሂደት ብዙ የሪፎርም ሥራዎች ሲሠሩ የፍርድ ቤትን ሥልጣን ማጠናከር፣ አስፈጻሚውን ደግሞ ተጠያቂ እንዲሆን የማድረግ ጥረት ነው የነበረው” ይላሉ።

ባለሙያው “አሁን መልሶ ሥልጣኑን ወደ አስፈጻሚ መውሰድ እና ከፍርድ ቤቱ ማራቅ ተሞክሮ የነበረውን ለውጥ ወደ ኋላ መመለስ ነው” ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ያሬድ ኃይለማርያምም የሕግ ባለሙያውን ስጋት ይጋራሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አቶ ያሬድ እነዚህ አዋጆች “በሕግ አስፈጻሚው እና በሕግ ተርጓሚው መካከል ያለውን የሥልጣን ክፍፍል ሊያዛባ እና ሚዛን ሊያሳጡ ይችላሉ” በማለት ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

ዋና ዳይሬክተሩ “በጣም ወሳኝ የሆኑ የዜጎችን መብቶች የሚመለከቱ ጉዳዮችን ለአስፈጻሚው አካል በዚህ ደረጃ መስጠት የሥልጣን ክፍፍሉን እንዲዛባ ያደርገዋል፤ ምክንያቱም በመጀመሪያ ደረጃ ያለው አስፈጻሚ አካል ላይ ከአቅም ባለፈ የሚነሱ የገለልተኝነት ጥያቄዎች አሉ” ሲሉ ያስረዳሉ።

“አስፈጻሚው አካል ሙሉ በሙሉ ከገዢው ፓርቲ ነጻ ነው ተብሎ በማይገመትመት ሁኔታ” ውስጥ መኖሩን የሚያወሱት አቶ ያሬድ፤ “[አስፈጻሚው አካል] ከገለልተኝነትም አልፎ ሕጎችን እና የሕግ የበላይነትን በአግባቡ የማስከበር ክፍተት እንዳለበት በየጥናቱ ሁሉ የሚገለጽ ነው” ሲሉ ይናገራሉ።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆኑት አቶ ያሬድ እንዲህ ዓይነት አዋጆች የሥልጣን ክፍፍሉን ከማዛባት በተጨማሪ “ለፍርድ ቤቶች የተሰጠውን ዓይነት ተገዳዳሪ ሥልጣን [ለአስፈጻሚው] መስጠት ለከፍተኛ ጥሰት በር ይከፍታል” ይላሉ።

አቶ ያሬድ ይህን ሃሳባቸውን በንድፈ ሃሳብ አስደግፈው ያስረዳሉ።

የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በቅጡ ባልሰፈነባቸው አገራት የአስፈጻሚው አካል “ለኃይል የቀረበ ነው” ሚሉት አቶ ያሬድ፣ ይኸው አስፈጻሚ አካል “ያልተመጣጠኑ የሚባሉ እርምጃዎችን በብዙ ጉዳዮች ላይ የሚወስድ አካል” መሆኑን ያነሳሉ።

እንደ አቶ ያሬድ ገለጻ የሕግ አውጪ እና ሕግ ተርጓሚ አካላት የሚያደርጉት የቅርብ ክትትል “የአስፈጻሚው አካል አቅም ከሕግ ማዕቀፍ እንዳይወጣ እና ተጠያቂ እንዲሆን” ያደርጋል።

“በመርኅ ደረጃ የሕግ አስፈጻሚው ሥልጣን ላይ ካለው ፓርቲ ገለልተኛ እንዲሆን ይጠበቃል” የሚሉት አቶ ያሬድ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ ግን ወደዚያ የደረሰ አለመሆኑን” ይጠቅሳሉ።

አቶ ያሬድ “የዳበረ የፖለቲካ እና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በሌለበት እና ተጠያቂነት ባልሰፈነበት” እነዚህን የሕግ ማዕቀፎች ማዘጋጀት “መንግሥት ሊወስዳቸው የሚፈልጋቸውን ማቀቢያ እርምጃዎችን የሕግ ሽፋን እንደመስጠት ነው” ሲሉ ይሞግታሉ።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች “ከሕገ መንግሥቱ ጋር ይቃረናሉ የሚሏቸው የመብት ጥሰቶች” በእነዚህ አዋጆች “ሕጋዊ ሽፋን ሰጥቶ በሕግ የተደገፉ መብት ጥሰቶች” የማድረግ አዝማሚያ መሆኑንም አቶ ያሬድ በአጽንኦት ይናገራሉ።

የረቂቅ አዋጆቹ ይዘት ምንድን ነው?

ከሦስቱ ረቂቅ አዋጆች ለፓርላማ በመቅረብ ቀዳሚ የሆነው የኢሚግሬሽን አዋጅን ለማሻሻል የተዘጋጀው ረቂቅ ነው።

ከ21 ዓመታት በፊት የጸደቀውን ኢሚግሬሽን አዋጅ የሚያሻሽለው ይህ ረቂቅ አዋጅ፤ ማንኛውም ሰው ከአገር እንዳይወጣ የማገድ ሥልጣንን ለኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር የሚሰጥ ነው።

በ1995 ዓ.ም. የወጣው የኢሚግሬሽን አዋጅ “ማንኛውም ሰው ከኢትዮጵያ እንዳይወጣ ሊታገድ የሚችለው በሕግ መሠረት በፍርድ ቤት ሲታዘዝ ብቻ ነው” ሲል ይደነግጋል።

በሥራ ላይ ያለውን አዋጅ የሚያሻሽለው ረቂቅ ይህን ሥልጣን ለኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት በተደራቢነት ይሰጣል።

ማሻሻያ አዋጁ “የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ከሚመለከታቸው የደኅንነት አገልግሎት እና ሕግ አስከባሪ አካላት ከሚያገኘው መረጃ ወይም አገልግሎቱ በራሱ ከሚያገኘው መረጃ በመነሳት በብሔራዊ ጥቅም እና ደኅንነት ላይ ሊቀለበስ የማይችል ግልጽ እና ድርስ የሆነ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል ሁኔታ መኖሩን ሲያምን ማንኛውም ሰው ከአገር እንዳይወጣ ማገድ ይችላል” ሲል አስቀምጧል።

ረቂቅ አዋጁ አክሎም “አገልግሎቱ ከአገር እንዳይወጣ ያገደውን ሰው ይዞ የሚያቆይ ከሆነ ፍርድ ቤት መቅረቡን ማረጋገጥ አለበት” ይላል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሕግ መምህር እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ይህን በማሻሻያ ረቁቁ ላይ የተካተተውን ድንጋጌ ይተቻሉ።

የሕግ መምህሩ “ሰዎች ከአገር እንዳይወጡ የሚለውን ትዕዛዝ ለአንድ የመንግሥት ሹመኛ መስጠት ብርቱ ዘፈቀደኝነት (Arbitrariness) ነው” ይላሉ።

የመንቀሳቀስን ሕገ መንግሥታዊነት ያስታወሱት ባለሙያው፤ “ሕገ መንግሥታዊ መብት ደግሞ የሚገደበው የሕግ መሠረት ኖሮት ፍርድ ቤት በሚሰጠው ትዕዛዝ ብቻ ነው መሆን ያለበት። እንጂ አስፈጻሚው ዝም ብሎ ደስ ባለው ጊዜ የሚወስነው አይደለም” ይላሉ።

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 32፤ “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ አገሪቱ ውስጥ ሚገኝ የውጭ ዜጋ በመረጠው የአገሪቱ አካባቢ የመዘዋወር እና የመኖሪያ ቦታ የመመሥረት፣ እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከአገር የመውጣት ነጻነት አለው” ሲል ይደነግጋል።

አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ይህ ሕገ መንግሥታዊ መብት “በቅርብ ጊዜ ደጋግመን እንደሰማነው በተለያየ ምክንያት በሌለ ሕግም በአስፈጻሚው አካል በኩል በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት እየተስተጓጎለ ዜጎች የተለያየ ችግር ሲገጥማቸው ይታያል” ይላሉ።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አክለውም፤ “ከዚህ በፊት በበቂ የሕግ መሠረት ላይ ያልተመሠረተ ግን ተግባራዊ ሲያደርጉት የነበረውን ሥልጣን ሕጋዊ ማድረግ ወይም ወደ ሕግ መቀየር የነበረውን ጥሰት እና ጫና ሕጋዊ መልክ እንደማስያዝ ነው የሚሆነው” ሲሉ ያክላሉ።

ይህን የማሻሻያ አዋጅ ድንጋጌ የሚተቹት የሕግ እና የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎቹ ብቻ አይደሉም። የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቱ አቶ ፉዓድ ኪያርም ድንጋጌውን የተመከለከተ ስጋት እንዳላቸው ባለፈው ሳምንት አርብ ለተወካዮች ምክር ቤት ገልጸዋል።

የምክር ቤቱ የሕግ እና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ረቂቁን አስመልከቶ ባካሄደው የሕዝብ ውይይት ላይ አቶ ፉዓድ፤ “ምክር ቤቱም ሆነ ቋሚ ኮሚቴው [ረቂቅ ማሻሻያ አዋጁን] seriously [በአጽንኦት] ሊያዩት ይገባል ብዬ አስባለሁ” ሲሉ ተደምጠዋል።

የመንቀሳቀስ መብት ሕገ መንግሥታዊ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ፉዓድ፣ ይህ መብት ግን “exception ሊደረግበት እንደሚችል ግልጽ ነው” ብለዋል።

የተወካዮች ምክር ቤት

የፎቶው ባለመብት, HoPR/FB

የምስሉ መግለጫ, የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግንቦት 22 የኢሚግሬሽን አዋጅ ማሻሻያን ረቂቅ ላይ በተወያየበት ወቅት

ሰዎች ከአገር እንዳይወጡ የሚሰጡ የዕግድ ትዕዛዞች በዋነኝነት የፍርድ ቤት ሥልጣን እንዲሆን የተደረገበት ምክንያት “ሰዎች መብታቸውንም እንዲያስከብሩ ክርክርም ካለ በዚያው ልክ ክርክራቸውን እንዲያቀርቡ” መሆኑን አቶ ፉዓድ ጠቅሰዋል።

አቶ ፉዓድ “ፍርድ ቤት ዜጎች ከአስፈጻሚው አካል ጋር ሚዛኑን የጠበቀ ክርክር የሚያደርጉበት ቦታ ነው” ሲሉ የዳኝነት አካሉ በዜጎች እና በአስፈጻሚው አካል መካል የሚጫወተውን ሚና አስረድተዋል።

“ዕግዱ በፍርድ ቤት ብቻ ይሁን” የሚል ክርክር እንደማያቀርቡ የጠቀሱት አቶ ፉአድ፤ “ነገር ግን ለዋና ዳይሬክተሩ ሥልጣን ሲሰጥ ቋሚ ሥልጣን ነው የሰጠው እስከመቼ ነው የሚያግደው? ካገደ በኋላ ፍርድ ቤት ያቀርባል ወይ? ክርክር ይደረግበታል ወይ? የሚለው የለም” ሲሉ ተደምጠዋል።

ከኢምግሬሽን አዋጅ ረቂቅ አስር ቀናት በኋላ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ሰኔ 4/2016 ዓ.ም. ለምክር ቤቱ የቀረቡ ሌሎች ሁለት ረቂቅ አዋጆችም በተመሳሳይ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለአስፈጻሚ አካሉ የሚሰጡት ሥልጣን አለ።

በወንጀል የተገኘ ንብረት ሕጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀል ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣው ረቂቅ አዋጅ፤ በአዋጁ የተጠቀሱ ወንጀሎችን ለመመርመር ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መገናኛዎች እና ደብዳቤዎች የመጥለፍ ሥልጣን ለመርማሪዎች ይሰጣል።

ረቂቅ አዋጁ “መርማሪ አካል አስቸኳይ ሁኔታ ካጋጠመው በአካባቢው ያለውን እና የሚመለከተውን የዐቃቤ ሕግ ተቋም የበላይ ኃላፊ በማስፈቀድ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የምርመራ ዘዴዎችን በመጠቀም መረጃ ሊሰበስብ ይችላል” በማለት ያትታል።

በመተሳሳይ ቀን ለምክር ቤቱ በቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ላይም ይኽው ሥልጣን ለመርማሪ አካል ተሰጥቷል።

ከዚህ በተጨማሪም በንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጁ ላይ የንብረት መወረስ ሊያስከትል ከሚችል ምርመራ እና ክስ ጋር በተያያዘ ፍትሕ ሚኒስትሩ ወይም እሳቸው የሚወክሏቸው ኃላፊ ለሦስት የሥራ ቀናት ንብረት እንዲታገድ ትዕዛዝ እንዲሰጡ ይፈቅዳል።

ትዕዛዙ የሚሰጠው “ሚኒስትሩ ወይም በሚኒስትሩ የሚወከል ኃላፊ የሚታገደው ንበረት በተፋጠነ ሁኔታ ሊሸሽ ወይም ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙን ሊያሳጣው የሚችል ድርጊት መኖሩን ሲያምነበት” መሆኑ በረቂቅ አዋጁ ላይ ተደንግጓል።

የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ ይህ ንብረት እንዲታገድ ትዕዛዝ መስጠት ሥልጣን ለፍትህ ሚኒስትሩ የተሰጠው፤ “በሦስት ቀናት ውስጥ የዕግድ ማመልከቻ ለፍርድ ቤት እንደሚያቀርብ በማሰብ” መሆኑን ያብራራል።

ከዕግድ ትዕዛዙ መተላለፍ በኋላ በሦስት የሥራ ቀናት ውስጥ የፍርድ ቤት ዕግድ ካልተጠየቀ ትዕዛዙ በራሱ ጊዜ ቀሪ እንደሚሆን ረቂቅ አዋጁ ላይ ሰፍሯል።

እነዚህ ሁለት አዋጆች “በዜጎች ንብረት እና privacy (ግለኝነት) ላይ አደጋ ሊጥሉ የሚችሉ” መሆናቸውን አቶ ያሬድ ያነሳሉ።

አቶ ያሬድ የሁለቱን አዋጆች ውስንነት ሲያብራሩ “[ሰዎች] የሚጠቀሟቸውን መገናኛዎች መከታተል አሁንም ቢሆን በተግባር በብዙ መልኩ የሚፈጸሙ ቢሆንም፤ በሕግ መልክ ሲወጡ ደግሞ እንደዚሁ ለፀጥታ አካላት እና ለአስፈጻሚው አካል በጣም ከፍተኛ የሆነ በቀላሉ ሊገራ የማይችል ሥልጣን ስለሚሰጥ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት አንደኛ the right to privacyን አደጋ ላይ ይጥላል” ይላሉ።

የሰብዓዊ መብት ባለሙያው “ዜጎቸም ያልምንም በቂ [ምክንያት] በጥርጣሬዎች መነሻነት ብቻ ንብረታቸው ሊታገድባቸው ወይም ሊወስድባቸው ይችላል” ሲሉ ስጋታቸውን አጋርተዋል።

ሁለቱ አዋጆች ለምክር ቤት በቀረቡበት ወቅት ተቃዋሚውን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ተወካይ የሆኑት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ “ተቃዋሚዎች እና መንግሥትን የሚተቹ ተቋማትም በእንደዚህ ዓይነት ሕጎች ሰለባ ሆነው ብዙ ጉዳት ደርሶባቸዋል” ሲሉ ተደምጠዋል።

ዶ/ር ደሳለኝ አዋጆቹ “በትክክል የወንጀል ፍሬ የሆኑ ነገሮችን ብቻ ለይቶ ለመከታተል እና የፖለቲካ መሳሪያ ተደርገው ደግሞ ተቃዋሚዎችን ማሳደጃ እንዳይሆኑ ተገቢ ድንጋጌዎች እንዲካተቱባቸው እንዲደረግ” አሳስበዋል።