የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል ተሳታፊዎችን መለየት መጀመሩን አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, AMECO/Youtube
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ግጭት ምክንያት የዘገየውን የምክክር ተሳታፊዎች ልየታ ማስጀመሩን አስታወቀ።
በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች እየተከናወነ ያለው ተሳታፊዎችን የመለየት ሥራ “ከሦስት እስከ አራት ሳምንታት” ባለው ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኮሚሽኑ ገልጿል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ የምክክሩ አንዱ ምዕራፍ የሆነውን አጀንዳ ማሰባሰብ ከቀናት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ ማጠናቀቁ ይታወሳል። ኮሚሽኑ ወደዚህ ምዕራፍ የተሻገረው በሀገሪቱ ከሚገኙ 1,300 በላይ ወረዳዎች ውስጥ ከ850 ገደማ በሆኑት ተሳታፊዎች ከለየ በኋላ ነው።
ኮሚሽኑ፤ ይህንን ተሳታፊዎችን የመለየት ሥራ ግጭት እየተካሄደበት በሚገኘው በአማራ ክልል እና የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን በተካሄደበት የትግራይ ክልል አለማከናወኑን ገልጾ ነበር። በሁለቱ ክልሎች ይህ የምክክር ሂደት ያልተከናወነው “ባለው ወቅታዊ ሁኔታ” ምክንያት እንደሆነ ኮሚሽኑ አስታውቆ ነበር።
በአማራ ክልል ያለው “የፀጥታ ሁኔታ አስቸጋሪ እና ፈታኝ” እንደሆነ ለቢቢሲ የተናገሩት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል አቃባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ፤ በክልሉ “አንጻራዊ ሰላም አለመኖሩ” ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ የተሳታፊዎች ልየታ እንዲዘገይ ካደረጉ “መሠረታዊ ምክንያቶች” መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በክልሉ ውስጥ “አንጻራዊ ሰላም” ባይረጋገጥም ኮሚሽኑ፤ “ባለው ሁኔታ ውስጥ የሚቻለውን መሥራት” ተገቢ ሆኖ እንዳገኘው ቃል አቀባዩ ተናግረዋል። በዚህም መሠረት ኮሚሽኑ ክልሉን በአራት ክላስተሮች ከፍሎ ሂደቱን እያከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
እንደ አቶ ጥበቡ ገለጻ፤ ኮሚሽኑ ለተሳታፊዎች ልየታ ሲባል የአማራ ክልልን የከፈለው ጎንደር፣ ጎጃም፣ ደብረ ብርሃን እና ደሴ በሚሉ ክላስተሮች ነው። በእነዚህ ክላስተሮች ስር ከሚገኙ ከ260 በላይ ወረዳዎች የተውጣጡ እና ተሳታፊዎችን ለመለየት እገዛ የሚያደርጉ ተባባሪ አካላት ሥልጠና እንደተሰጣቸውም ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, National Dialogue Commission
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሌሎችም ክልል እና ከተማ አስተዳደሮች ተሳታፊዎችን ለመለየት እገዛ የሚያደርጉለት ተባባሪ አካላት ከሰባት ተቋማት የተመረጡ ግለሰቦች ናቸው።
ከተባባሪ አካላቱ ውስጥ የወረዳ አስተዳደር ተወካይ፣ ዕድሮች፣ የሃይማኖት መሪዎች እና ዳኞች ይገኙበታል። የሲቪክ ማኅበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የመምህራን ማኅበር ተወካዮችም ከተባባሪ አካላቱ መካከል ናቸው።
በአማራ ክልል ከሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡት ተባባሪ አካላት ሥልጠናውን ከወሰዱ በኋላ ወደየመጡበት ወረዳ ተመልሰው ተሳታፊ የመለየት ሥራ መጀመራቸውን ቃል አቃባዩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“በእነዚህ [አራት] ክላስተሮች ተባባሪ አካላቱ ሥልጠና ወስደው፤ አሁን እነዚህ ሠልጣኞች ወደ የወረዳዎቻቸው ተመልሰው ሥራዎችን እያከናወኑ ነው። ኮሚሽኑም በቅርብ ክትትል እያደረገ ነው። ስለዚህ በአማራ ክልል የተሳታፊ ልየታው እየተከናወነ ነው” ሲሉ በአማራ ክልል የኮሚሽኑ ሥራ ያለበትን ደረጃ አስታውቀዋል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ በተባባሪ አካላት እገዛ የሚመርጣቸው ተሳታፊዎች አስር የማኅበረሰብ ክፍሎችን የሚወከሉ ናቸው።
ሴቶች፣ ወጣቶች፣ እድሮች፣ የማኅበሰረብ መሪዎች እንዲሁም የመንግሥት እና የግል ድርጅት ሠራተኞች ተሳታፊ ከሚመረጥባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች መካከል ናቸው። መምህራን፣ በባህል እና በሙያቸው ምክንያት የተገለሉ እንዲሁም ተፈናቃዮችም ተሳታፊ ይመረጥላቸዋል።
ራሳቸውን የሚገልጹበት ዋና መተዳደሪያ ያላቸው ሰዎች በሚል ምድብ ውስጥ ገብተው በዋነኛነት የሚጠቀሱት አርሶ እና አርብቶ አደሮችም በተመሳሳይ ተሳታፊ የሚወከልላቸው የሕብረሰተብ ክፍሎች ናቸው።
በእያንዳንዱ ወረዳ እነዚህን የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚወክሉ አስር ተሳታፊዎች ከተመረጡ በኋላ አመቺ ወደ ሆኑ የዞን ከተሞች ተሰባስበው ወረዳቸውን በመወከል የአጀንዳ ሀሳቦችን የሚሰጡ ተወካዮችን ይመርጣሉ።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል ይህንን ሂደት እያከናወነ ያለው “ክልሉ ያለበት ወቅታዊ ሁኔታ ለኮሚሽኑ ሥራዎች ፈታኝ” በሆነበት ጊዜ ውስጥ መሆኑን የሚናገሩት ቃል አቀባዩ አቶ ጥበቡ፤ ይሁንና ሥራዎች እየተከናወኑ ያሉት “በአጠቃላይ የሚገኘው ውጤት ላይ ተፅእኖ በማያሳድር መልኩ” እንደሆነ አስረድተዋል።
በኦሮሚያ ክልል ተሳታፊዎች በተለዩበት ወቅት ከፀጥታ ጋር የተያያዘ ተመሳሳይ ሁኔታዎች በገጠሙ ጊዜ ተሳታፊዎችን እንደ አዳማ፣ ጅማ እና ሻሸመኔ ያሉ ከተሞች በማጓጓዝ ሂደቱ እንደተከናወነ አስታውቀዋል። በአማራ ክልልም ተመሳሳይ አይነት አካሄድ ይተገበር እንደሆነ ከቢቢሲ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ጥበቡ፤ ይህ አይነቱ አካሄድ “መሬት ላይ ያሉ ነገሮችን ግምት ውስጥ እየገባ የሚተገበር” እንደሆነ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, National Dialogue Commission
ቃል አቃባዩ፤ “በአማራ ክልልም በተሰጣቸው ሥልጠና፣ በኮሚሽኑ አሠራር መሠረት ወረዳ ላይ ሕብረተሰቦቹን እየለዩ ያሉት ተባባሪ አካላቶቹ ናቸው። ስለዚህ ከተለየ በኋላ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ ገብተው በምን አካሄድ ብንሄድበት ይበልጥ ውጤታማ ይሆናል የሚለው በቀጣይ ታይቶ በኮሚሽኑ በኩል የሚወሰን እና የሚተገበር ይሆናል” ሲሉም ሀሳባቸውን አብራርተዋል።
በአማራ ክልል ከፀጥታ ችግር ባሻገር “ከሎጂስቲክስ እና ትራንስፖርት” ጋር የተያያዙ ጉዳዮች መኖራቸውን አቶ ጥበቡ ጠቅሰዋል። እነዚህን ሁሉ ከግምት ውስጥ በማስገባት በክልሉ የሚከናወነውን የተሳታፊዎች ልየታ “ከሦስት እስከ አራት ሳምንታት ባለ ጊዜ ውስጥ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ” መሆኑን ገልጸዋል።
የተሳታፊ ልየታ ያልተደረገበት ሌላኛውን ክልል - ትግራይን - በተመለከተ፤ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በክልሉ “ሁኔታዎች አመቺ ሲሆኑ በፍጥነት ተንቀሳቅሶ ተሳታፊዎችን የመለየት ሥራውን ለመጀመር የሚያስችል ዝግጅት” እያደረገ መሆኑን አቶ ጥበቡ ተናግረዋል።
በክልሉ የተሳታፊ ልየታ ‘መቼ ይጀመራል?’ የሚለው ግን “ኮሚሽኑ ብቻውን የሚያቅደው [ጉዳይ] እንዳልሆነ” ገልጸዋል።
የምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ውይይቶችን ማድረጋቸውን የጠቀሱት ቃል አቀባዩ፤ “ከጊዜያዊ አስተዳደሩ እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶቹ ቀጥለው ሁኔታዎቹ በተመቻቹ በማናቸውም ጊዜ ኮሚሽኑ የሚጀምር ይሆናል” ብለዋል።
“ነገር ግን ኮሚሽኑ ‘በዚህ ጊዜ በትግራይ ክልል ላይ ይህንን እሠራለሁ’ ብሎ ለማቀድ የተቸገረባቸው ሁኔታዎች” መኖራቸውን ያስረዱት አቶ ጥበቡ፤ “ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ብቻ ሳይሆን ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር ተገናኝቶ መነጋገር የሚፈልጉ ጉዳዮች አሉ” ብለዋል።








