ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ለፍትህ በጋራ የቆሙበት የግሪንፊል ሕንጻ የእሳት አደጋ

 የግሪንፊል ኢትዮ- ኤርትራ ቡድን አባላት
የምስሉ መግለጫ, የግሪንፊል ኢትዮ- ኤርትራ ቡድን አባላት

ከሰባት ዓመታት በፊት በግሪንፊል ሕንጻ ላይ በደረሰው የእሳት አደጋ ከሞቱት 72 ሰዎች መካከል በርካታ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ይገኙበታል።

በአደጋው 12 ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል ግማሾቹ ሕጻናት ናቸው።

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የጦርነት ታሪክ ቢኖራቸውም ይህንን ሐዘናቸውን በጋራ ለመወጣት እና ፍትህ ለመጠየቅ በአንድነት ቆመዋል።

አሁን ላይ ቤተሰቦቻቸውን ያጡበትን ሰባተኛ ዓመት ለመዘከር እየተዘጋጁ ሲሆን፣ የዚህ አደጋ የመጨረሻ የምርመራ ሪፖርት ለሕዝብ ይፋ የሚሆንበትን ቀን እየተጠባበቁ ነው።

በድርያ እና ወንድሟ ሳዲቅ
የምስሉ መግለጫ, በድርያ እና ሳዲቅ በእሳት አደጋው እህታቸውንና የእህታቸውን ባል እንዲሁም የጥንዶቹን ሦስት ልጆች አጥተዋል።

በድሪያ ጀማልን ጨምሮ የተወሰኑት የሟቾች ቤተሰቦች ከዚህ በፊት ወደ መገናኛ ብዙኃን ዘንድ ቀርበው ተናግረው አያውቁም።

በድሪያ የ35 ዓመት እህቷን ኑራን እና የ33 ዓመቱን የእህቷን ባለቤት ሐሺምን በአደጋው አጥታለች።

የኑራ እና የሐሺም ሦስት ልጆችም ሞተዋል። የመጀመሪያ ልጃቸው ያህያ 13 ዓመቱ የነበረ ሲሆን፣ ፍርዳውስ 12 ዓመቷ እና ታናሹ ያቆብ ደግሞ 6 ዓመቱ ነበር።

በድሪያ እነዚህን ቤተሰቦች “ምርጥ ቤተሰቦች” ስትል ነው የምትገልጻቸው። “ማንም በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዲያልፍ አልመኝም። አምስት የቤተሰብ አባላትን በአንድ ጊዜ ማጣት አእምሮዬንም አካሌንም ጎድቶታል” ስትል የደረሰባትን ከፍተኛ ሐዘን ተናግራለች።

ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት ወደ ኋላ ተመልሳም ከእህቷ ጋር ጠዋት ላይ አውርተው በሚቀጥለው ቀን ማታ እንዳጣቻት ታስታውሳለች።

“መልካም ቤተሰቦች”

የበድሪያ ወንድም ሳዲቅ አደጋ ሲከሰት ‘ባላችሁበት ሁኑ’ የሚለው የለንደን የእሳት አደጋ ደንብን አጥብቆ ይተቻል። በወቅቱ የእሳት አደጋ ሠራተኞች በሥፍራው ከደረሱ በኋላ ቤተሰቦቹ ካሉበት እንዳይወጡ ተነግሯቸው ነበር።

ሳዲቅ የቤተሰብ አባላቱ እንደተባሉት እዚያ ባይቆዩ ኖሮ አሁን በሕይወት ይኖሩ ነበር ብሎ ያምናል።

“ሃይማኖት፣ ቋንቋ ሳይገድባት ከሁሉም ሰው ጋር ትግባባ ነበር። ሁሉም በጥሩ ሁኔታ ያደጉ ጥሩ ቤተሰቦች ነበሩ” ሲል ቤተሰቡብ ያስታውሳል።

“የኑራ ሴት ልጅ ልክ እንደ እናቷ ጎበዝ ነበረች። ከቢልጌትስ ፋውንዴሽን ሽልማት አግኝታለች። ለቤተሰቦቿ ብቻ ሳይሆን የአገርም ሐብት መሆን ትችል ነበር” ይላል።

ሳዲቅ እና በድሪያ ያደጉት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ጥር ወር ላይ በተካሄደው የግሪንፊል የእሳት አደጋ ክስተት ላይ ምስክርነት በተሰጠበት ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ በተደረገው የኢትዮ-ኤርትራ ቡድን አባልም ናቸው።

በጊዜው ተጋጅቶ የነበረው ሁነት ለሟች ቤተሰቦች ሊከፈል ይገባል ለተባለው የብዙ ሚሊዮን ፓውንድ ካሳ ድርድር ላይ ተሳታፊ ከሆኑት አካላት ጋር ፊት ለፊት ተገናኝተው እንዲያወሩ ዕድል የፈጠረ ነበር።

በቡድኑ ውስጥ የኬኒሲንግተን እና ቼልሲ ሮያል ቦሮ፣ የለንደን የእሳት አደጋ መከላከያ ብርጌድ እንዲሁም ግሪንፊል ሕንጻ እድሳት ላይ ተሳትፎ የነበራቸው እንደ አርኮኒክ፣ ሴሎቴክስ እና ኪንግስፓን ተካተው የነበረ ሲሆን፣ በወቅቱ አርኮኒክ ተወካይ አልላከም ነበር።

መሐመድኑር ቱኩ እና የሦስት ዓመት ልጁ አማያ

የፎቶው ባለመብት, Family handout

የምስሉ መግለጫ, መሐመድኑር ቱኩ እና የሦስት ዓመት ልጁ አማያ በአደጋው ሕይታቸውን አጥተዋል።

ኤርትራዊው ኢብራሒም ቶኩ በግሪንፊል የምስክርነት ሳምንት ሂደት ላይ ተገኝቶ ነበር።

ኢብራሒም በአደጋው ወንድሙን መሐመድኑር ቶኩን እና የወንድሙን ባለቤት አማል አድመዲንን እንዲሁም የሦስት ዓመቷን የወንድሙን ልጅ አማያን አጥቷል። እነአማልን ለመጠየቅ ቤታቸው የነበረችው የአማል የእህት ልጅም በአደጋው ሞታለች።

ኢብራሒም ከወንጀል ምርመራ ውጤት በፊት በቀረበው የ150 ሚሊዮን ፓውንድ ካሳ ላይ ቅሬታ አለው።

በኤርትራ የሚገኙት እናቱ ምንም ዓይነት ካሳ ማግኘት እንዳልቻሉም ተናግሯል።

“አሁን ላይ ስለ ካሳ የሚወራው እንዴት ነው?” ሲልም ይጠይቃል።

“መጀመሪያ የወንጀል ምርመራውን ውጤት እስከ መጨረሻው ማየት አለባችሁ። ከዚያ ስለካሳ ትጠይቃላችሁ” ብሏል።

ኢብራሒም ጨምሮም “ምን ያህል ጥፋተኛ እንደሚሆኑ አናውቅም። ስለ ገንዘብ ማሰብ ፍትህ አይደለም” ይላል።

ኢብራሒም ቶኩ ከግሪንፊል ሕንጻ አጠገብ የተነሳው ፎቶ
የምስሉ መግለጫ, ኢብራሒም ቶኩ ከግሪንፊል ሕንጻ አጠገብ የተነሳው ፎቶ

የጳውሎስ ተክሌ ወንድ ልጅ ይስሐቅም በአደጋው ሕይወቱን አጥቷል። ይስሐቅ የ5 ዓመት ልጅ ነበር።

“በልቤ ያለው ሐዘን አሁንም ትኩስ ነው” ይላል ጳውሎስ።

“በአደጋው ሰሞን ፍትህ ለማግኘት ስንታገል ነበር፤ ነገር ግን አሁን ላይ ይህ ቡድን አሰባስቦናል፤ ረድቶናል። መረጃዎችን መለዋወጥ እንችላለን” ሲልም በጋራ መሰባሰባቸው የሚኖረውን ጥቅም ተናግሯል።

አንድ ላይ መሰባሰብ እና መገናኘትን ለእርሱ እንደቀላል አያየውም። “እንደ ቴራፒ [ሕክምና] ነው” ይላል።

ከዚህ ሁነት ባሻገር ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን የግሪንፊል ቡድን አባላት ለማኅበራዊ ጉዳዮች፣ መረጃ ለመለዋወጥ እና እርስ በርስ ለመደጋገፍ በመደበኛነት ይገናኛሉ።

በዓላትንም በጋራ ያከብራሉ።

የቡድኑ አስተርጓሚ ዳንኤል በየነም ከአደጋው በኋላ ከፖሊስ እና ከባለሥልጣናት መረጃዎችን ለማግኘት እና የሕግ ሂደቶችን ለመከታተል ይረዳቸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ረጅም እና ውስብስብ በሆነው የግሪንፊል ሕንጻ የእሳት አደጋ የምርመራ ሂደት ላይ እገዛ አድርጎላቸዋል።

ቋንቋ ትልቁ ተግዳሮት እንደሆነ የሚናገረው ዳንኤል “በጉዳት ላይ የሕግ ሥርዓቱን አለመረዳት እና ራስን መግለጽ አለመቻል ከባድ ነው” ይላል።

ግሪንፌል

ፍትህን ጥበቃ . . .

በዚህ አደጋ እንደተጎዱ በርካታ ሰዎች ይህ ቡድንም የአደጋውን የመጨረሻ የምርመራ ሪፖርት ምን እንደሚያካትት በጉጉት እየጠበቁ ነው።

በድሪያ “ላለፉት ስድስት ዓመታት በየቀኑ ሂደቱን እከታተላለሁ። እንደማንኛውም ሰው ሪፖርቱ ምን ይዞ እንደሚመጣ እየተጠባበቅኩ ነው” ብላለች።

በተወሰነ መልኩም ቢሆን ፍትሐዊ እንደሚሆን ተስፋ አድርጋለች።

ሳዲቅ በበኩሉ ሪፖርቱ ዳግም መጉላላት እና ፍትህ ማጣት እንዳይከሰት እንደሚያደርግ ተስፋ ሰንቋል።

“ቤተሰቦቻችንን አጥተናል፤ ፍትህ አላገኘንም ነበር። አሁንም ፍትህን እየጠበቅን ነው” ብሏል ሳዲቅ።

የአደጋው የመጨረሻ የምርመራ ውጤት እአአ መስከረም 4/2024 ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።