ከ100 ዓመታት በኋላም አከራካሪ የሆነው በፍቅረኛዋ ወንጀል በሞት የተቀጣችው ሴት

ኤዲት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኤዲት

እአአ በ1923 ኤዲት ቶምሰን እና ፍሬድሪክ ባይዋተርስ በሞት ተቀጥተዋል።

ፍቅረኛሞች ነበሩ። የኤዲት ባለቤት በስለት ተወግቶ ከተገደለ በኋላ ነው በሞት የተቀጡት።

ሆኖም ግን ኤዲት ባለቤቷ በስለት እንደተወጋ ስለማወቋ አንዳችም ማስረጃ የለም። የሞት ቅጣቱ እስከዛሬ ድረስ አነጋጋሪ የሆነውም ለዚህ ነው።

በለንደን ሆሎዌይ ማረሚያ ቤት ነበረች። የ29 ዓመቷ ኤዲት ለቀናት ማደንዘዣ ሲሰጣት ነበር።

የሞት ቅጣቱ ሊፈጸምባት ጥቂት ሲቀረው “ሁሉም ነገር በቅርቡ ያከትማል” ነበር የተባለችው።

ቅጣቱ የሚፈጸምበት ወንበር ላይ አስቀመጧት። ብዙም ሳትቆይ ሕይወቷ አለፈ።

የ20 ዓመት ዕድሜ የነበረው ፍቅረኛዋ፣ ፔንቶንቪል ማረሚያ ቤት ነበር የታሰረው። እሱም በሞት ተቀጥቷል።

ፍሬዲ ከቅጣቱ ሦስት ወራት በፊት የኤዲት ባለቤት ፐርሲን ደጋግሞ በስለት ወግቷል።

በዕለቱ ኤዲት እና ባለቤቷ ቴአትር አይተው ወደ ቤት እየገቡ ነበር።

ስለ ጥቃቱ ኤዲት እንደማታውቅ ፍሬዲ ደጋግሞ ተናግሯል።

ይህን ጉዳይ ካጠኑ ባለሙያዎች አንዱ እንደሚሉት የኤዲት ወንጀል “ውብ መሆኗ፣ ራሷን የቻለች ሴት መሆኗ፣ የሠራተኛው መደብ መሆኗ እና ለባሏ አለመታመኗ” ነው።

ማኅበረሰቡ ከሞራል መርህ ‘አፈንግጠዋል’ ያላቸውን ሴቶች ከመቅጣት እንደማይታቀብ ያክላሉ።

ታዋቂው ደራሲ ኤድገር ዋለስ “በዚህ አገር ታሪክ በመድልዎ እና በተዛባ የሕዝብ አመለካከት ሳቢያ ያለ በቂ ማስረጃ የተገደለች ሴት ኤዲት ቶምሰን ናት” ይላሉ።

ኤዲት እና ባለቤቷ ፐርሲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኤዲት እና ባለቤቷ ፐርሲ

‘ልዩ መሆን ትፈልግ ነበር’

ኤዲት ከሠራተኛው ማኅበረሰብ የተለየ ሕይወት ነበር ሕልሟ።

የተወለደቸው በ1893 በፈንጆች ገና ቀን በምሥራቅ ለንደን ውስጥ ነው።

ከአምስት ልጆች ኤዲት የበኩር ነበረች። እህቷን እና ሦስት ወንድሞቿን በመንከባከብ እናቷን ታግዝ ነበር።

ትምህርቷን ስትጨርስ ለሥራ ወደ ከተማ ተጓዘች። ተስፈኛ ልብ እና ብሩህ አእምሮ ነበራት።

በካልቶን ኤንድ ፓልመር ሽያጭ ክፍል ተቀጠረች። ብዙም ሳይቆይ ወደ ዋና ግዢ ክፍል አደገች።

ስለ ኤዲት ሁለት መጻሕፍት የጻፈችው ላውራ ቶምሰን “ተርታ ሰው ሆና ልዩ ሰው መሆንን የምትመኝ ሰው ነበረች” ትላለች።

በአውሮፓውያኑ 1916 ፐርሲ ቶምሰንን አገባች። ከአባቷ እና ከባለቤቷም በላይ ደመወዝ ነበራት።

ቤት ለመግዛት አብዛኛውን ገንዘብ ያወጣችው እሷ ብትሆንም፣ ባለቤትነቱ ግን በባለቤቷ ስም ሆነ።

ኤዲት ስታገባ ሥራ ትታ ልጅ እንድታሳድግ ነበር የሚጠበቀው፤ አላደረገችው።

ልዩ የዳንስ ችሎታ የነበራት ኤዲት በለንደን ሆቴሎች ምሽቶቿን ታጣጥም ነበር። በእሷ ማኅበራዊ ደረጃ ላሉ ሰዎች እነዚህ ሆቴሎች ብዙም ቦታ የላቸውም።

ላውራ “ዘመነኛ ሴት ናት። ቄንጠኛ ናት። ተስፋዋ ትልቅ ነው። በባሏ ሳይሆን በእሷ ስም ቤት እንዲኖራት ትፈልግ ነበር” ስትል ትገልጻታለች።

በዘመኑ በነበሩ አሳሪ ሕጎች ለመገዛት አልፈቀደችም። ስምንት ዓመት ከእሷ ከሚያንስ ቆንጆ ወንድ ጋር ፍቅር ጀምራም ነበር።

ፍሬድሪክ የኤዲትን ቤተሰብ ያውቃቸዋል። ለእረፍት ኤዲትን፣ ባለቤቷን እና የኤዲትን እህት ሊጠይቅ ሄዶ ነው ፍቅራቸው የተጠነሰሰው።

ለተወሰኑ ሳምንታት ከእነኤዲት ጋር እንዲኖር ሲጋበዝ ፍቅራቸው ጦፈ።

ገዳይ ፍሬዲ (ከግራ)፣ ኤዲት እና ሟች ፐርሲ (ከቀኝ) በአንድ ላይ

የፎቶው ባለመብት, René Weis

የምስሉ መግለጫ, ገዳይ ፍሬዲ (ከግራ)፣ ኤዲት እና ሟች ፐርሲ (ከቀኝ) በአንድ ላይ

የኤዲት ደብዳቤዎች

ፐርሲ ኤዲትን ሲመታት ጣልቃ የገባው ፍሬዲ ከቤቱ ወጥቶ ሌላ ቦታ ተዛወረ። ፐርሲ በአንድ ወቅት ከአንድ የቤት ጥግ ወደሌላው ወርውሮ ክፉኛ ጎድቷታል።

ኤዲት እና ፍሬዲ ቢራራቁም ደብዳቤ ይጻጻፉ ነበር።

የኤዲት ደብዳቤዎች ስሜቷን በግልጽ የሚያትቱ ናቸው። ስለ ዕለት ከዕለት ሕይወት ከማውራት ተነስታ ስለ ወሲብ፣ ጽንስ ስለማቋረጥ እና ራስን ስለማጥፋት ያወራችበት ደብዳቤ ይጠቀሳል።

መጽሐፍ ማንበብ ስለምትወድ ራሷን ከልብ ወለድ ገጸ ባሕሪያት አንዷ አድርጋ ትሥልም ነበር።

እንደ ገጸ ባሕሪ ሆና የፐርሲን ምግብ መርዛ ወይም በምግቡ የመስታወት ስብርባሪ ጨምራ ስለመግደል ትጽፍ ነበር።

ከደብዳቤዎቿ በአንዱ እንዲህ ትላለች፦

“ትላንት ሦስት ባሎች ያጣች ሴት አገኘሁ። የሞቱት በጦርነት አይደለም። ሁለቱ በውሃ ሲሰጥሙ አንዱ ራሱን አጠፋ። ሌሎች የማውቃቸው ሰዎች ግን አንድ ባልም መገላለግል አልቻሉም። እንዴት ያለ ኢ-ፍትሐዊ ዓለም ነው።”

በሌላ ደብዳቤዋ እንዲህ ትላለች፦

“ብሩህ የሆኑ መብራቶችን ልጠቀም እወዳለሁ። ምንም ውጤት ግን አላመጡም። ላንተም ልልክልህ ነበር። ግን አልሆነም።”

የዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ለንደን ፕሮፌሰር ረኔ ዌስ “እነዚህ ቃላት የፍቅር ናቸው” ይላሉ።

ፍሬዲ ከግድያው ጋር በተያያዘ በፖሊስ ቁጥጥር ስር በዋለበት ጊዜ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፍሬዲ ከግድያው ጋር በተያያዘ በፖሊስ ቁጥጥር ስር በዋለበት ጊዜ

የፐርሲ መገደል

በጥቅምት 1922 (እአአ) ኤዲት እና ፐርሲ ፊልም ሲያዩ አመሹ። ወደ ቤታቸው እየተጓዙ ሳለ አንድ ሰው ተጠጋቸው።

ኋላ ላይ ፖሊስ ሲጠይቅ ኤዲት ተገፍታ ወድቃ እንደነበረ እና ባሏን መሬት ተዘርሮ እንዳገኘችው ተናግራለች።

ፖሊስ የ32 ዓመቱን ፐርሲ ሰውነት ሲመረምር በስለት መወጋቱን አወቀ። የፐርሲ ወንድም ፖሊሶች ፍሬዲን እንዲያዋሩ ነገረ።

የፍሬዲ ቤት ሲፈተሽ የኤዲት የፍቅር ደብዳቤዎች ተገኙ።

ኤዲት ፍሬዲን ፖሊስ ጣቢያ ስታየው “ለምን ይሄን አደረገ? ይሄን እንዲያደርግ አልፈለኩም። አምላኬ ሆይ ምን ላድርግ? እውነቱን መናገር አለብኝ” አለች።

ፐርሲ እንዲሞት እንደምትሻ ኤዲት የጻፈቻቸው ደብዳቤዎችም ተገኙ። ፍሬዲ ፐርሲን በስለት እንደወጋው አመኗል።

ፐርሲ ሲገፋው ራሱን ለመከላከል እንደሞከረም ፍሬዲ ተናግሯል።

ኤዲት እንደምትከሰስ ሲነገረው ግን “እሷ ምን አጠፋች? ስለ ድርጊቱ የምታውቀው ነገር አልነበረም” ሲል ተቃውሟል።

የፍርድ ሂደቱን ለመከታተል በርካታ ሰው ይሰበሰብ ነበር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የፍርድ ሂደቱን ለመከታተል በርካታ ሰው ይሰበሰብ ነበር

የፍርድ ሂደቱ

ደብዳቤዎቻቸው በየጋዜጣው ሲወጡ ሁለቱም ዝነኛ ሆኑ።

በኅዳር 1922 ፍርድ ቤት ሲቀርቡ አካባቢው በሰው ተጨናንቆ ነበር። ዘጠኝ ቀን የዘለቀውን የፍርድ ሂደት ለመከታተል መቀመጫ ቦታ የሚገዙም ነበሩ።

ፀሐፊ ቤቨርሊ ኒኮላር በወቅቱ ጋዜጠኛ ነበር። በ1973 ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ “ክርስቶስ በሮማውያን ዘንድ ለፍርድ የቀረበበት ጊዜ ነበር የሚመስለው” ብሏል።

በፍርድ ሂደቱ እንደ ማስረጃ የቀረበው ደብዳቤው ነበር። ደብዳቤዎቹ በፍርድ ቤት እየተነበቡ ሲጠቀሱም ነበር።

“እነዚያ የግል ምሥጢር የሆኑ ደብዳቤዎች በአደባባይ መነበባቸው ያሳዝነኛል። ሊያሰቃዩዋቸውም ፈልገው ይመስለኛል” ትላለች ላውራ።

የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ያለቀበት ጊዜ መሆኑ ሰዎች ኤዲትን እንዲጠሏት ምክንያት እንደሆነ ፕሮፌሰር ረኔ ይናገራሉ።

“እንግሊዝ ውስጥ በጦርነት ባሎቻቸውን ያጡ ሴቶች ብዙ ናቸው። ይህች ሴት ከእነዚህ ሴቶች አንጻር ራስ ወዳድ ተደርጋ ተወስዳለች። ጥሩ ሴት፣ ገንዘብ፣ ባል፣ ምግብ፣ ቴአትር ወዘተ በሕይወቷ እያለ አንድ ወንድ አልበቃኝም ብላ ያደረገችውን እዩ እየተባለ ነበር” ይላሉ።

ሕዝቡ ፍሬዲን “ኤዲትን ወዶ እንደተንገላታ ሰው” ሲያይ ኤዲትን ግን እንደኮነናት ያስረዳሉ።

ኤዲት ከመገደሏ በፊት የቆየችበት እስር ቤት

የፎቶው ባለመብት, Museum of London/Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኤዲት ከመገደሏ በፊት የቆየችበት እስር ቤት

የሞት ፍርድ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኤዲትን የጠላው ሕዝቡ ብቻ ሳይሆን ዳኛው ጀስቲስ ሸርማን ጭምርም ነበሩ።

ፍርዱ ከመሰጠቱ በፊትም “ማንኛውም ጤናማ ሰው ሊያስብ እንደሚችለው ድርጊቱ አንገሽግሿችኋል ብዬ አምናለሁ” ብለዋል።

ኤዲት ተጨባጭ ማስረጃ አልቀረበባትም። የፐርሲ ሰውነት ሲመረመር መርዝም ይሁን የመስታወት ስባሪ አልተገኘበትም።

የኤዲት ስህተት ደብዳቤዎች መጻፏ ነበር። ዐቃቤ ሕግ ቃሏን ወደ ማስረጃነት ጠምዝዞ አቀረበ።

ኤዲት እና ፍሬዲ ጥፋተኛ ተባሉ።

“ፍርዱ የተዛባ ነው። ይህች ሴት ጥፋተኛ አይደለችም” ሲል ፍሬዲ በፍርድ ቤቱ ይጮህ ነበር።

ኤዲት የሞት ፍርዱን ስትሰማ እያለቀሰች ነበር ከፍርድ ቤት የተወሰደችው።

የፍሬዲን ሕይወት ለማዳን ፊርማ ሲሰባሰብ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲፈርሙ፣ ከኤዲት ጎን ግን የቆመ አልነበረም።

“ሴቶች ስለሚፈሯት ጠሏት። ወንዶች ይወዷታል ብለው ስላሰቡ ጠሏት። የሚያዝናለት ጠፋ። ለመትረፍ ዕድል አልነበራትም” ትላለች ላውራ።

ራሷን የፆታ እኩልነት አቀንቃኝ የምትለው ሬቤካ ዌስት የተባለች ሴት ሳትቀር “ኤዲት አሳዛኝ፣ አስቀያሚ” ናት ብላ ጻፈች።

ኤዲት ከተገደለች በኋላ ሴቶች ለአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዊልያም ብሪግማን የምስጋና ደብዳቤ ይጽፉ ነበር። የኤዲትን ሕይወት በማትረፍ ‘የሴቶችን ክብር ባለማስደፈሩ’ ነው ምስጋና የላኩት።

ኤዲት ሴቶች ስለሚደርስባቸው ፍረጃ ከእስር ቤት ሆና ደብዳቤ ትጽፍ ነበር። ለቤተሰቦቿ ከተጻፉ ደብዳቤዎቿ አንዱ እንዲህ ይላል፦

“ሁሉም ነገር ዛሬ የሚያከትም ይመስላል። ማሰብ አልቻልኩም። ከድቅድቅ ጨለማ ጋር የተፋጠጥኩ ይመስለኛል። ዐይኔም ሐሳቤም ከጨለማው አሻግሮ ማየት አይችልም። ባልፈጸምኩት ድርጊት ቅጣት እየተፈጸመብኝ ነው፤ በማላውቀው ነገር።”

ላውራ እንደምትለው፣ የሞት ፍርድ የተላለፈባቸውን ሴቶች ለመስማት ዕድል ቢኖርም የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንድትገደል መወሰናቸው ያሳዝናል።

የኤዲትን መኖር “ትዳርን የሚያፈርስ እምቢተኝነት” ብለው ነበር ያመኑት።

ኤዲት በመጨረሻ ከቤተሰቦቿ ጎን እንድትቀበር ተደርጓል
የምስሉ መግለጫ, ኤዲት በመጨረሻ ከቤተሰቦቿ ጎን እንድትቀበር ተደርጓል

‘አሁን ከቤተሰቧ ጋር ናት’

በ1923 የእነኤዲት ቤት ለሽያጭ ሲቀርብ ብዙዎች የኤዲትን ዕቃዎች ለመውሰድ ሲሻሙ ነበር።

ፕሮፌሰር ረኔ፣ ኤዲት ይቅር እንድትባል ለዓመታት ታግለዋል። በ2019 አስክሬኗ ከቤተሰቦቿ ጋር እንዲቀበር ተደርጓል።

“የእናቷን ምኞት ማሳካት ነበር ሕልሜ። ቢያንስ አሁን ከቤተሰቦቿ ጋር ተቀላቅላለች” ይላሉ።

ኤዲት የሞት ፍርድ ከተላለፈባት 100 ዓመታት ቢያልፍም ጉዳዩ አሁንም ድረስ ማኅበረሰባዊ ዋጋ እንዳለው ላውራ ታምናለች።

“ጭፍን ፍረጃ አሁንም እንዳልተወገደ ማኅበረሰቡ መገንዘብ አለበት። መልኩን ይቀያይራል እንጂ አይጠፋም” ትላለች።

የኤዲትን ታሪክ “ጥሩ ማስጠንቀቂያ የሚሆን ታሪክ” ስትል ነው የምትገልጸው።

“አሁንም ሰዎችን ከታሪክ የመደምሰስ ዘመን ላይ ነን። ኤዲትም እንደዚያ ነው የተሰረዘችው። አስፈሪ አካሄድ ቢሆንም ማኅበረሰቡ ግን አሁንም ያደርገዋል” ትላለች ላውራ።