ፈረንሳይ ጽንስ የማቋረጥ መብትን በሕገ መንግሥቷ በማስፈር የመጀመሪያዋ አገር ሆነች

የፎቶው ባለመብት, TOM NICHOLSON/REX/SHUTTERSTOCK
የፈረንሳይ ምክር ቤት ጽንስ የማቋረጥ መብት በአገሪቱ የበላይ ሕግ ውስጥ እንዲካተት በመወሰን ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ እንዲደረግ ውሳኔ አሳለፈ።
በዚህም አውሮፓዊቷ አገር ፈረንሳይ ጽንስ የማቋረጥ መብትን በሕገ መንግሥቷ ውስጥ በማስፈር በዓለም የመጀመሪያዋ አገር ሆናለች።
ይህ ጽንስ የማቋረጥ መበት አንቀጽ በ1958 (እአአ) ዘመናዊው የአገሪቱ የበላይ ሕግ ውስጥ እንዲካተት የፈረንሳይ ፓርላማ አባላት በሕገ መንግሥቱ ላይ ማስተካከያ እንዲደረግ አዘዋል።
ውሳኔውን ፓርላማው 780 ለ 72 በሆነ ከፍተኛ የድምጽ ድጋፍ የተቀበለው ሲሆን፣ ይህንንም ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን “ለዓም መልዕክት ያስተላለፈ የፈረንሳይ ኩራት” አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
በርካታ የዓለም አገራት የሥነ ተዋልዶ ጤና መብትን የተመለከቱ ሕግጋት ቢኖሯቸውም፣ ፈረንሳይ ግን ጽንስን የማቋረጥ መብትን በግልጽ በሕገ መንግሥቷ ውስጥ በማካተት ብቸኛዋ ሆናለች።
ሴቶች ጽንስ ለማቋረጥ እንዲችሉ ነጻነትን ይሰጣል የተባለው አንቀጽን ፈረንሳይ እንደ አገር በተመሠረተችበት ዘመናዊው ሕገ መንግሥቷ ውስጥ ለማካተት የሚደረገው ማሻሻያ 25ኛው ይሆናል።
ከዚህ በፊት በፈረንሳይ ሕገ መንግሥት ላይ የመጨረሻው የማሻሻያ አንቀጽ የተካተተው በ2008 (እአአ) ነበር።
አሁን ጽንስ ማቋረጥ ሕገ መንግሥታዊ እውቅና ያለው መብት መሆንን በተመለተ በተሰበሰበ የሕዝብ አስተያየት ውስጥ ከተሳተፉ ሰዎች 85 በመቶ የሚሆኑት ድጋፍ ሰጥተዋል።
በፓርላማው የቀኝ ክንፍ ፖለቲከኞች ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የጽንስ ማቋረጥ ጉዳይን ሕገ መንግሥታዊ ያደረጉት ለመጪው ምርጫ ጥቅም ያስገኝልኛል በማለት ነው ሲሉ ቢቃወሙትም ሳይሳካላቸው ቀርተዋል።
ውሳኔውን የሚተቹት ምንም እንኳን ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ስህተት ባይሆንም፣ ነገር ግን አስፈላጊ አይደለም በማለት እርምጃው ፕሬዝዳንቱ የግራ ክንፍ ፖለቲካቸውን ለማጠናከር የሚያደርጉት ሙከራ ውጤት ነው ብለውታል።
ጽንስ የሟቋረጥ መብት ከአውሮፓውያኑ 1975 ጀምሮ በፈረንሳይ ውስጥ በሕግ እውቅና ያለው ነው።
ከዚያን ጊዜ አንስቶ ሕጉ ለዘጠኝ ጊዜ ሲሻሻል የቆየ ሲሆን፣ በእያንዳንዱ ማሻሻያ ወቅት ትኩረት የተደረገው ጽንስ የማቋረጥ አገልግሎትን ማስፋት ላይ ነበር።
በፈረንሳይ ውስጥ የሚወጡ ሕጎች ሕገ መንግሥታዊነት ላይ ውሳኔ የሚሰጠው ሕገ መንግሥታዊ ምክር ቤት ከዚህ ሕግ ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት ጥያቄ አንስቶ አያውቅም።
በፈረንሳይ ጽንስ የማቋረጥ መብት በሕግ እውቅና የነበረው ቢሆንም፣ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ እንዲካተት ፍላጎት የተፈጠረው ከሁለት ዓመት በፊት በአሜሪካ የተላላፈውን ውሳኔ ተከትሎ ነው።
በአውሮፓውያኑ 2022 የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጽንስ የማቋረጥ መብት እንዲነሳ ያደረገ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት እያንዳንዱ የአሜሪካ ግዛት ጽንስ ማቋረጥን የማገድ መብት ተሰጥቶታል።
በፈረንሳይ የጽንስ ማቋረጥ መብት በሕገ መንግሥት ውስጥ እንዲሰፍር በአገሪቱ ምክር ቤት የተላለፈው ውሳኔ በበርካቶች ዘንድ ድጋፍን አግኝቷል።
የሴቶች መብት ተከራካሪዋ አን ሲሴል ሜይልፈርት ውሳኔው የሴቶችን መብት በተመለከተ ከፈረንሳይ አልፎ በዓለም ዙሪያ ወሳኝ መልዕከት የሚያስተላለፍ ነው ስትል የተሰማትን ደስታ ገልጻለች።
ነገር ግን ይህንን ውሳኔ ሁሉም በበጎ አልተቀበለውም፣ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አሁንም በጽንስ ማቋረጥ ላይ ስታሰማው የቆየችውን ተቃውሞ እየደገመች ነው።
ከቫቲካን ተቋም የወጣው መግለጫ “የሰውን ሕይወት ለማጥፋት ምንም ዓይነት ‘መብት’ ሊኖር አይችልም” በማለት በፈረንሳይ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን መሪዎች የቀረበውን ተቃውሞ ደግሞታል።
ጨምሮም “በዚህ የታሪክ ክፍል ሁሉም መንግሥታት እና የሃይማኖት ተቋማት የሰው ልጅን ሕይወት መጠበቅ ከሁሉ ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ መሆኑን ለማሳየት የቻሉትን ሁሉ እንዲያደርጉ” ጥሪ አቅርበዋል።












