ፈረንሳይ ስለምታስተናገደው የዘንድሮው የፓሪስ ኦሊምፒክ የምናውቃቸው ዋና ዋና ጉዳዮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ተጀምሯል፤ ውድድሩ የተለያዩ አገራትን በሚወክሉ ስፖርተኞች ለሁለት ሳምንታት ያህል ይካሄዳል።
የዚህን ውድድር መጠናቀቅ ተከትሎ ደግሞ አካል ጉዳተኛ ስፖርተኞች የሚሳተፉበት የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ይቀጥላሉ።
በፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ውድድር የሚካሄድ ሲሆን፣ የብሬክ ዳንስ ውድድር ዘንድሮ በኦሊምፒክ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ይታያል።
የፓሪስ ኦሊምፒክ እስከ መቼ ይቆያል?
በአውሮፓውያኑ የበጋ ወቅት የሚካሄደው የፓሪስ ኦሊምፒክ ከሐምሌ 19 እስከ ነሐሴ 5/2016 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ይከናወናል።
አስር ሺህ አምስት መቶ አትሌቶች በሚሳተፉበት በዚህ ውድድር 32 ጨዋታዎች የተካተቱ ሲሆን፣ 329 ሜዳሊያዎች ለሽልማት ተዘጋጅተዋል።
ከዚህ ውድድር መጠናቀቅ ከ17 ቀናት በኋላ አራት ሺህ አራት መቶ አትሌቶች የሚሳተፉበት ፓራሊምፒክስ ይጀምራል።
206 አገራት በኦሊምፒክ ጨዋታዎች፤184 አገራት ደግሞ በፓራሊምፒክስ ጨዋታዎች ይሳተፋሉ።
ፓሪስ ከዚህ ቀደም በአውሮፓውያኑ በ1900 እና በ1924 ኦሊምፒክስ አስተናግዳለች።
የፈረንሳይዋ መዲና ፓሪስ ከለንደን ቀጥሎ የኦሊምፒክ ጨዋታዎችን ሦስት ጊዜ በማስተናገድ በታሪክ ሁለተኛዋ ከተማ ሆናለች።
ለንደን ከዚህ ቀደም በ1908፣ 1948 እና በ2012 ኦሊምፒክስ ማዘጋጀቷ ይታወሳል።
ያለፈው ኦሊምፒክ በጃፓኗ ቶኪዮ ከተማ የተካሄደ ሲሆን፣ ውድድሩ በኮቪድ ምክንያት በአንድ ዓመት ዘግይቶ በአውሮፓውያኑ 2021 ነበር የተከናወነው።

ውድድሩ የት ይከናወናል?
ለኦሊምፒክ ጨዋታዎች በማዕከላዊ ፓሪስ 15 አዳራሾች የተዘጋጁ ሲሆን፣ ለፓራሊምፒክስ ደግሞ 11 አዳራሾች ይሰናዳሉ።
ትራያትሎን፣ የዋና ውድድር እና ፓራ-ትራያትሎን በዋና ከተማዋ ፓሪስ በሚገኘው ሲየን ወንዝ ላይ ይካሄዳሉ።
ስታድ ደ ፍራንስ ዋና ዋናዎቹን የአትሌቲክስ ውድድሮችን፤ የእግር ኳስ ጨዋታዎች ደግሞ ስድስት ክልላዊ ስታድየሞች ያስተናግዳሉ።
በሜዲትሬኒያን ጠረፍ የምትገኘው ማርሴ በባሕር ላይ የሚደረገውን የሴይሊንግ ውድድር ይከናወንባታል።
ደቡብ ፓሲፊክ ላይ የምትገኘው የፈረንሳይ ግዛቷ ታሂቲ ሰርፊንግ የተሰኘውን ውቅያኖስ ላይ የሚካሄድ ስፖርት ታስተናግዳለች።
አዘጋጆቹ እንደሚሉት ጨዋታዎቹ በዋናነት የሚከናወኑት ከዚህ ቀደም በተዘጋጁ አዳራሾች ነው። ይህ ደግሞ ገንዘብ ለመቆጠብ እና የካርበት ልቀት ለመቀነስ ይረዳል።
ውድደሮቹ የሚከናወኑባቸውን አዳራሾች ወጭ 8 ቢሊዮን ዩሮ ገደማ ይሆናል።
ባለፈው ሐምሌ የአዘጋጁ ኮሚቴ ፕሬዝደንት በጀቱ “በቁጥጥራችን ሥር ነው” ብለው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አዳዲስ ጨዋታዎች
ብሬኪንግ የተባለው የዳንስ ዓይነት በፓሪስ ኦሊምፒክ ለመጀመሪያ ጊዜ ይካተታል።
ብሬክ ዳንሲንግ አሊያም ብሬኪንግ በ1970ዎቹ ኒው ዮርክ ውስጥ የተፈጠረ ጂምናስቲክ አዘል ስፖርት ነው።
ባለፈው የቶኪዮ ውድድር ኦሊምፒክን የተቀላቀሉት ቢኤምኤክስ፣ ስኬትቦርዲንግ፣ ስፖርት ክላይምቢንግ እና ሰርፊንግ የተባሉት ስፖርቶች ዘንድሮም ይቀጥላሉ።
ካራቴ እና ቤዝቦል ደግሞ በዘንድሮው ኦሊምፒካ ላይ አይኖሩም።
የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት
ከዚህ ቀደም በተካሄዱ የኦሊምፒክ ውድድሮች ላይ እንደተለመደው በፓሪስ ኦሊምፒክ አገራትን የሚወክሉ አትሌቶች ሰንደቅ ዓላማቸውን እያውለበለቡ በስታድየም ውስጥ አልታዩም።
በምትኩ ፓሪስ በሚገኘው ሴን ወንዝ ላይ በሚቀዝፍ ግዙፍ ጀልባ በደማቅ መብራት ታጅበው ነው ዝግጅቱ ተሳታፊ መሆናቸውን እና ውድድሩ መጀመሩን ያሳዩት።
መሐል ከተማዋን አቆራርጦ በሚወርደው ወንዝ ላይ የሚቀዝፈው ጀልባ 6 ኪሎ ሜትር ይጓዛል።
ጀልባው ትሮካዴሮ ወደተሰኘ ስታድየሙ አካባቢ ወደ ሚገኘው ፓርክ ካቀና በኋላ የኦሊምፒክ ችቦ ይበራል።
አዘጋጆቹ እንደሚሉት ይህን ማድረግ የሻቱት ሕዝቡ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱን በነፃ እንዲታደም በማሰብ ነው።
ግማሽ ሚሊዮን ተመልካቾች የወንዙን ዳር ተከትለው መክፈቻውን ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሩሲያ ትሳተፋለች?
ሩሲያ እና ቤላሩስ አትሌቶቻቸውን ወደ ፓሪስ እንዳይልኩ ተነግሯቸዋል።
ሞስኮው ዩክሬንን በመውረሯ ነው ከዚህ ውድድር የታገደችው። ቤላሩስ ደግሞ ለሩሲያ በመወገኗ ይህ ዕጣ ደርሶባታል።
ነገር ግን ከእነዚህ አገራት የሚመጡ አትሌቶች በግላቸው መወዳደር ይችላሉ።
የሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ “እስራኤል በጋዛ እያካሄደችው ላለው ጦርነት እንዴት አልታገደችም?” ሲሉ ዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴን ወቅሰዋል።
የኮሚቴው ፕሬዝደንት ቶማስ ባኽ፤ ንፅፅሩ ስህተት ነው ብለው እስራኤል በውድድሩ እንደምትሳተፍ ለሮይተርስ ዜና ወኪል አረጋግጠዋል።
ከአገራቸው የተፈናቀሉ አትሌቶች በስደተኞች የኦሊምፒክ ቡድን ተካተው የሚሳተፉ ይሆናል።
ቶኪዮ በተካሄደው ውድድር ይህ ቡድን ሶሪያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ አፍጋኒስታን እና ካሜሩንን ጨምሮ ከ11 አገራት የተውጣጡ 29 አትሌቶችን አቅፎ ነበር።
ማንኛውም ፕሮግራሙን መታደም የሚፈልግ ግለሰብ ፓሪስ 2024 ወደተሰኘው ድረ-ገፅ አቅንቶ ቲኬት መግዛት ይችላል።
ወደ ስታድየም ገብቶ ውድድሩን ለመታደም 21 ዩሮ ይጠይቃል።
የዩናይትድ ስቴትሷ ሎስ አንጀለስ ከተማ የ2028ን፣ የአውስትራሊያዋ ብሪስበን ደግሞ የ2032ቱን የኦሊምፒክ ውድድሮችን ያስተናግዳሉ።
ሕንድ፣ ፖላንድ፣ ሜክሲኮ እና ኢንዶኔዥያ በ2036 የሚካሄደውን ኦሊምፒክ ለማሰናዳት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።












