ለ4ኛ ጊዜ ለ8ኛ ክፍል ፈተና የተቀመጡት የ76 ዓመቱ አዛውንት - አቶ ኃይሉ ለማ

የፎቶው ባለመብት, AMN
የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት አቶ ኃይሉ ለማ ለአራተኛ ጊዜ የስምንተኛ ክፍል ፈተናን ዘንድሮ ወስደዋል።
ለሚያያቸው አርጅተዋል፤ የፊታቸው ቆዳ ቢሸበሸብም፣ ጥርሳቸውም እያለቀ ቢሆንም፣ ሲናገሩ ግን ድምጻቸው ላይ ያለው ጉልበት የጎረምሳ ነው።
በተለይ ስለትምህርታቸው ሲናገሩ ሌላ ተማሪን ወኔ ያስይዛሉ።
ከትምህርት ቀጥሎ የሚወዱት ግብርና እና ቀረርቶ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ኃይሉ፣ ምንም እንኳ ዘንድሮ የስምንተኛ ክፍል ፈተናን ለአራተኛ ጊዜ ቢፈተኑም እንደሚያልፉ ተስፋ አድርገዋል።
ቢቢሲ- ሦስቴ ወድቀዋል አሉ? እውነት ነው?
አቶ ኃይሉ - አዎ።
ቢቢሲ - ምነው?
አቶ ኃይሉ - አንድ ጊዜ 27 አመጣሁ፣ አንድ ጊዜ ደግሞ 23 አመጣሁ፤ በቀጣዩ ደግሞ 48 አመጣሁ። ያለ ሃምሳ በቀር አያልፍም ተባለ።
ቢቢሲ- አያጠኑም እንዴ ይዘናጋሉ?
አቶ ኃይሉ - አዎ እዘናጋለሁ። ቤትም ውስጥ ደግሞ ልጆች ስላሉኝ እነኛ ልጆችም ያናድዱኛል። ከዚያ እዚያ ስሄድ ሂሳቧንም ምኗንም በደምጽም [በቃልም] በወረቀትም እመልሳለሁ። እና ቤት ስገባ ያንን ነገር መለስ ብዬ ብድግ አላደርገውም።
በአዲስ አበባ ከተማ የ8ኛ ክፍል ፈተና ከሰኔ 4 እና 5/2016 ዓ.ም. ድረስ ሲሰጥ ቆይቷል።
እንደ አዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ መረጃ ከሆነ ፈተናው በከተማዋ በሚገኙ 182 የመፈተኛ ጣቢያዎች ለ86,672 ተማሪዎች ተሰጥቷል።
አቶ ኃይሉ ከእነዚህ ተማሪዎች መካከል አንዱ ናቸው። እድሜያቸው 76 ይሁን እንጅ ዐይናቸው አልፈዘዘም፤ ለትምህርት ያላቸው ሞራል አልደከመም።
“ዐይኔም አልፈዘዘም። ልጆቼም፣ ባለቤቴም ደህና ናቸው። ፈጣሪ ይመስገን።”
የ76 ዓመቱ አዛውንት ኩረጃ እንደማይወዱ እና በራሳቸው ጥረት እና እውቀት ፈተናውን ማለፍ እንደሚፈልጉም አክለው ተናግረዋል።
“ቃል ለምድር ለሰማይ እሰጣለሁ መኮረጅ አልወድም። በራሴ አንጎል ፈጣሪ ከወሰደኝ [ካሳለፈኝ] ይውሰደኝ [ያሳልፈኝ]። የተኮረጀ ነገር ወይ ቁልቁል ይመልሳል፣ ወይ ይጥል ይሆናል እንጂ አይጠቅምም።”
ቢቢሲ- ሌሎች ሲኮርጁ አይተው ይሆን?
አቶ ኃይሉ - እኔ ምንም ያየሁት ነገር የለም። ውስጥ ለውስጥ የሚኮርጁትን አላውቅም። እስካሁን በዐይኔ ያየሁት ነገር የለም። ወረቀት ጽፎ መቀባበልንም፣ መኮረጅም አልጠይቅም። እኔ ያቺኑ 'ቢ' ፣ 'ሲ' ያለችውን መልሷን እየፈለግኩ የአቅሜን እመልሳለሁ።
ቢቢሲ - የትኛው የትምህርት ዓይነት ይከብድዎታል?
አቶ ኃይሉ - እንግዲህ አማርኛ እናገር የለ፣ ትምህርት ላይ ግን አማርኛ እና እንግሊዝኛው ትንሽ ከበድ ይለኛል። እሱንም እንግዲህ አለማጥናቴ ነው።
ቢቢሲ- አማርኛ ሲናገሩ ግን እኮ ደንቀፍ አይሉም።
አቶ ኃይሉ - እውነትህን ነው። አንዳንዴ ቤቴም የሚመጡ መልካም መልካም የመንግሥት ሠራተኞች አሉ። ሲመጡ ታድያ ይህ ነገር እንዲህ ነው? ብለው ትንሽ ጫር ጫር አድርገው ይሰጡኛል። . . . በዚያን ጊዜ ናቅ አድርጌ እተዋለሁ። መናቄ ነው የጎዳኝ።

የፎቶው ባለመብት, AMN screen shot
በአርሲ ሮቤ ተወልደው ያደጉት አቶ ኃይሉ በልጅነታቸው ቤተሰቦቻቸው የሃይማኖት ትምህርት እንዲማሩ ይፈልጉ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ነገር ግን የአቶ ኃይሉ የልጅነት ልብ የነበረው ከትምህርት ውጪ ግብርና ላይ ነበር።
“በልጅነቴ ቤተሰቦቼ ትምህርት ቤት ሲያስገቡኝ እየጠፋሁ አያቶቼ ዘንድ እሄድ ነበር” የሚሉት አቶ ኃይሉ “መልካም ሴት እወዳለሁ። እርሻ እወዳለሁ እያልኩ ስሸልል ቤተሰቦቼ ሊድሩኝ ወሰኑና አገባሁ።”
አቶ ኃይሉ በወታደራዊው የደርግ መንግሥት ብሔራዊ ውትድርና እንዲዘምቱ መገደዳቸውን ገልጸው፤ ከዚያ ሲመለሱም ግብርና ላይ ማተኮራቸውን ያወሳሉ።
የሰባት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ኃይሉ በ1990 ዓ.ም. ነው ወደ አዲስ አበባ የመጡት።
“በአራዳ ክፍለ ከተማ ይኽው እየሠራሁበት፣ እየበላሁበት፣ እየጠጣሁበት፣ እየተመጻደኩ፣ ልጆቼንም እያሳደኩ፣ ሰርጉንም እየሰረግኩ፣ ዓለም የሚያየውንም እያየሁበት ነው” ይላሉ በኩራት።
የሚማሩት ደግሞ መሃል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ቅድስተ ማርያም ቤተክርስትያን ሸዋ ዳቦ አካባቢ የሚገኘው አፄ ናኦድ ትምህርት ቤት ነው።
ሦስት ጊዜ ስምንተኛ ክፍልን በመውደቃቸው የተነሳ “ከእኔ ጋር እየተማሩ የነበሩት አልፈውኝ ሄደዋል። ብዙ ናቸው። 9ኛም፣ አስረኛም የደረሱ አሉ” ብለዋል ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ።
አቶ ኃይሉ በቤትም፣ በቤተክርስቲያንም በሥራ ቦታም ቢሆን የቻሉትን ያህል ለማጥናት እንደሚሞክሩ ይናገራሉ።
“ቤተ ክርስቲያን ስሄድ ደጀ ሰላሙ ላይ ስቀመጥ አጥንቼ አውቃለሁ። አንድ ሁለት ቀን። ማኅሌት ስገባ ግን እንደዚያ አላደርግም።”
“ባልንጀሮቼ የደረሱበት እደርሳለሁ ነው የእኔ ምኞት” የሚሉት የአቶ ኃይሉ የመማር ምኞት ጎብጠው ከዘራ እስኪይዙ፣ ቤት እስኪውሉ ድረስ ይዘልቃል።
ቢቢሲ - እንግዲህ ዘንድሮ ቢያልፉ አራት ዓመት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አጠናቅቀው ዩኒቨርስቲ ሲገቡ 80 ዓመት ይሆኖታል።
አቶ ኃይሉ - አይደለም ሰማኒያ፣ ዘጠና ዓመት ቢሆነኝም ምንም የምዘናጋ አይመስለኝም።
ቢቢሲ - ከትንንሽ ልጆች ጋር ተቀምጠው ሲማሩ፣ በዕድሜ ልዩነቱን ሲያዩት ምቾት የሚነሳ ነገር የለውም?
አቶ ኃይሉ - ከትንንሽ ልጆች ጋር ስቀመጥ እንዲያውም ደስ ነው የሚለኝ።
ቢቢሲ - ለምን?
አቶ ኃይሉ - ልጆቼ ናቸዋ! ግማሾቹ የልጅ ልጆቼ ስለሚሆኑ ደስ ነው የሚለኝ።
ቢቢሲ - በዚህ ዕድሜዎ ለምን ይማራሉ አይሉም ጓደኞችዎ? ከእንግዲህ ወዲያ ተምረው ምን ሊያደርጉ ነው የሚል የለም?
አቶ ኃይሉ - እንደሱ የሚሉኝን ኧረ የታባታችሁ ! . . . አናንተ እንደኔ አትማሩም፣ ሄዳችሁ በጠጅ ቤት እና በድራፍት ቤት ትንቀባረሩ የለ እናንተ። እኔ በጠጅ እና በድራፍት ቤት የምንቀባረር መሰለህ። ከተማሪዎቹ ጋር እና ከመምህራኖቼ ጋር ቁጭ ብዬ ተነጋግሬ መግባቱ ደስታዬ ነው እላቸዋለሁ።

የፎቶው ባለመብት, amn
“አቅም እስካለኝ ድረስ አላቋርጥም. . .”
አቶ ኃይሉ በስተርጅና ለትምህርት ያላቸው ፍላጎት ማደጉ በቤተሰብ አባሎቻቸው መካከል እኩል ተቀባይነት አላገኘም።
“ቤተሰቦቼ መማሬን አልወደዱልኝም። ‘በስተርጅና የሚማረው ለምንድን ነው?’ ይላሉ። ተምሮ የት ሊቀጠር፣ ምን ዓይነት ደሞዝስ ሊያገኝ ነው? ሲሉ ቅሬታ ያቀርባሉ። እኔ ደግሞ ከሚገኘው ደሞዝ ይልቅ እውቀቱ ይቀድማል ስል እመልስላቸዋለሁ።”
ምንም እንኳ የአቶ ኃይሉ ልጆች በአባታቸው በስተርጅና ትምህርት ቤት መመላለስ ደስተኛ ባይሆኑም አሁንም አርሲ የሚገኙት ባለቤታቸው ግን እንደሚያበረታቷቸው ይገልጻሉ።
“ባለቤቴ ‘ተማር፤ ከጀመረከው አይቀር ከዳር አድርሰው’ ትለኛለች። ይህንን ከእርሷ ስሰማ ደስ ይለኛል። ትንሹ ወንድ ልጄም ‘አባዬ በርታ’ ይለኛል።”
ቢቢሲ፡ የመማር ጥቅሙ ግን ምንድን ነው?
አቶ ኃይሉ - በጣት ከመፈረም ድኛለሁ። እድሜ ለመንጌ [መንግሥቱ ኃይለማሪያም]። ከጨለማ ነው የወጣሁት። ይህ ነጻ ያወጣኝን [ትምህርት] ቦታው ልድረስ [ልጨርሰው]፣ ወረቀቱንም፣ ሕዝቡ የሚያነበውን እንግሊዙንም፣ ሂሳቡንም፣ አካባቢ ሳይንሱንም በዐይኔ ልያቸው። በእንግሊዝኛ ቢያቅተኝ በአማርኛ አነባቸዋለሁ።
ቢቢሲ - አስጠኚ አለዎት?
አቶ ኃይሉ - ምንም የለኝም?
ቢቢሲ - ዩኒቨርስቲ ቢገቡ ምን መሆን ይፈልጋሉ?
አቶ ኃይሉ - ዐይኔ ደህና ከሆነ ያኔ አንብቤ ጽፌ፣ እንዲህ አንደምናገረው በጽሁፍም እንደልቤ ጽፌ በምላሴ ብቻ ከምናገር በጽሁፍ መልስ ሰጥቼ ብዬ አስባለሁ።
አቶ ኃይሉ “በሞትኩ ጊዜም በስተርጅና የተማረው ተብዬ ስሜ እንዲታወስ ነው የምፈልገው። ከዚህ ባሻገር ደግሞ ታዳጊዎች እና አዋቂዎች ይህ ሽማግሌ እንኳ ከተማረ ለምን እኛ አንማርም? ብለው እንዲነሳሱ እፈልጋለሁ” ይላሉ።
የ76 ዓመቱ አዛውንት አቶ ኃይሉ በዚህ ዓመት ለአራተኛ ጊዜ የስምንተኛ ክፍል ፈተናን ሲወስዱ አልፋለሁ ብለው ተስፋ አድርገዋል።
“አቅም እስካለኝ፣ ምርኩዝ እስከምይዝ አልያም እስትንፋሴ እስክትቆም ድረስ ትምህርት አላቋርጥም።”
ከቢቢሲ ጋር የነበራቸውንም ቆይታ ሲያበቁ አዛውንትነታቸውንም፣ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ መሆናቸውንም አልዘነጉም።
“መንግሥት በአልጋው፣ ቄስ በደብሩ፣ አዛውንቱን በአካባቢ በሰላም ይቆይልን። ጉድ ባይ!"
ረዥም ሳቅ . . .












