የፍትህ ሚኒስትሩ ያለ ፍርድ ቤት ማመልከቻ ንብረት እንዲታገድ እንዲያዙ የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ

የፍትህ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሕንጻ

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Justice/FB

የምስሉ መግለጫ, የፍትህ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሕንጻ

የንብረት መወረስ ሊያስከትል ከሚችል ምርመራ እና ክስ ጋር በተያያዘ የፍትህ ሚኒስትር ወይም እሳቸው የሚወክሏቸው ኃላፊ ለሦስት የሥራ ቀናት ንብረት እንዲታገድ ትዕዛዝ እንዲሰጡ የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ።

ትዕዛዙ የሚሰጠው “[ሚኒስትሩ] የሚታገደው ንብረት በተፋጠነ ሁኔታ ሊሸሽ ወይም ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙን ሊያሳጠው የሚችል ድርጊት መኖሩን ሲያምንበት” መሆኑን በረቂቁ ላይ ሰፍሯል።

ይህን ሥልጣን ለፍትህ ሚኒስትሩ የሚሰጠው እና ለተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ነው። በስምንት ክፍሎች እና በ57 አንቀጾች የተዋቀረው ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ የቀረበው ማክሰኞ ሰኔ 4/2016 ዓ.ም. ነው።

ረቂቅ አዋጁ ምንጩ ያልታወቀ ንብረትን ስለማስለመስ፣ በንብረት ማስመሰል ሂደት ምርመራ ስለሚከናወንበት ሁኔታ እና ሥነ ሥርዓት እንዲሁም ስለ ንብረት ማገድ እና መያዝ ድንጋጌዎችን ይዟል። ንብረት የመውረስ እና የማስተዳደር ጉዳዮችን የያዙ ድንጋጌዎችም በረቂቅ አዋጁ ውስጥ ተካተዋል።

የአዋጁ ዋነኛ ዓላማ፤ “የወንጀል ፍሬ የሆኑ ንብረቶችን እና ገንዘቦችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመያዝ፣ ለማገድ፣ ለመውረስ ወይም ለማስተዳደር” የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ማበጀት መሆኑ የረቂቅ አዋጁ ማብረራሪያ ያስረዳል።

የንብረት ማገድ እና መያዝን የተመለከተው የረቂቅ አዋጁ ክፍል ንብረት ሊታገድ ስለሚችለበት አግባብ በዝርዝር ያብራራል።

በረቂቁ ድንጋጌ መሠረት “የንብረት መውረስ ሊያስከትል የሚችል ምርመራ እየተካሄደ ከሆነ፣ ክስ ከቀረበ፣ በተከሳሹ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ከተሰጠ ወይም ሌላ በቂ የሆነ ምክንያት ሲኖር” ንብረቱ እንዲታገድ ወይም እንዲያዝ ለፍርድ ቤት ማመልከቻ ሊቀርብ እንደሚችልት ያትታል።

ይህን ማመልከቻ የሚያቀርበው ዐቃቤ ሕግ ወይም መርማሪ ስለመሆኑም ረቂቅ አመልክቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይህ ድንጋጌ ቢኖርም፤ “የሚታገደው ንብረት በተፋጠነ ሁኔታ ሊሸሽ ወይም ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙን ሊያሳጠው የሚችል ድርጊት መኖሩን ሲያምንበት” የፍትህ ሚኒስትር ንብረቱ እንዲታገድ ትዕዛዝ ሊሰጡ እንደሚችሉ ረቂቁ ላይ ሰፍሯል።

የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ ይህ የንብረትን እንዲታገድ ትዕዛዝ የመስጠት ሥልጣን ለሚኒስትሩ የተሰጠው፤ “በሦስት ቀናት ውስጥ የዕግድ ማመልከቻ ለፍርድ ቤት እንደሚያቀርብ በማሰብ” መሆኑን ያብራራል።

የፍትህ ሚኒስትር የዕግድ ትዕዛዙን ከሰጡ በኋላ ባሉት ሦስት የሥራ ቀናት ውስጥ የፍርድ ቤት ዕግድ መጠየቅ እንዳለበት ረቂቅ አዋጁ ያትታል። ማክሰኞ ሰኔ 4/2016 ዓ.ም. ለፓርላማ የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ አክሎም “የፍርድ ቤት ዕግድ ካልተጠየቀ ትዕዛዙ በራሱ ጊዜ ቀሪ ይሆናል” ይላል።

በተጠቀሰው ሦስት የሥራ ቀናት የዕግድ አቤቱታ ለፍርድ ቤት የቀረበ እንደሆነ፤ የዕግድ ትዕዛዙ አቤቱታው ከቀረበበት ቀን ጀምሮ ፍርድ ቤት ውሳኔ እስከሚሰጥበት ቀን ድረስ ጸንቶ እንደሚቆይ ረቁቁ ያስረዳል።

ረቂቁ “የማገድ ትዕዛዝ ማመልከቻ የቀረበለት ፍርድ ቤት አቤቱታው ከቀረበበት ቀን ጀምሮ ባሉት አስራ አምስት ቀናት ጊዜ ውስጥ ይወስናል” ይላል።

ሆኖም ግን ፍርድ ቤቱ በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ውስጥ ትዕዛዝ ካልሰጠ “ተገቢ ነው ብሎ ለሚወስነው የጊዜ ገደብ” ተጨማሪ የዕግድ ጊዜ የመስጠት ሥልጣን በአዋጁ ተሰጥቶታል።

ዐቃቤ ሕግ በሦስት ምክንያቶች ንብረት ታግዶ እንዲቆይ ለፍርድ ቤት ሊያመለክት እንደሚችል ረቂቁ ላይ ተገልጿል።

በረቂቁ ላይ የሰፈሩት እነዚህ ምክንያቶች “ንብረቱ በማንኛውም ሰው ይዞታ ውስጥ ቢቆይ በንብረቱ ላይ ሊደርስ የሚችል ጉዳት የማይኖር ከሆነ” ለንብረቱ ኢኮኖሚያዊ ጥበቃ የተሻለ እንደሆነ ወይም በንብረቱ ልዩ ባህሪ ምክንያት ባለበት መቆየቱ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ” የሚሉ ናቸው።