ምርጫ ቦርድ፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ የተለጠፉ የብልፅግና ፓርቲ ማስታወቂያዎች እንዲነሱ አሳሰበ

የብልፅግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ በቤኒሻንጉም ጉሙዝ ክልል

የፎቶው ባለመብት, Mandra woreda communication/FB

የምስሉ መግለጫ, በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ማንድራ ወረዳ የተደረገ የብልፅግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ ከቀናት በኋላ ቀሪ ምርጫ በሚደረግበት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሚገኙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተለጠፉ የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ማስታወቂያዎችን እንዲያነሳ ፓርቲውን አሳሰበ።

ምርጫ ቦርድ፤ ይህንን ትዕዛዝ የሰጠው ማክሰኞ ሰኔ 4/2016 ዓ.ም. ለብልፅግና ፓርቲ በጻፈው ደብዳቤ ነው። በቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ተፈርሞ የወጣው ይህ ደብዳቤ መነሻ ያደረገው፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሚንቀሳቀሰው ቦሮ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ) የቀረበለትን ቅሬታ ነው።

ብልፅግና እና ቦዴፓን ጨምሮ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቀጣዩ ሳምንት እሁድ ሰኔ 16/2016 ዓ.ም. ለሚካሄደው የስድስተኛው ዙር ቀሪ ምርጫ የምረጡኝ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ ናቸው። የአፋር፣ ሶማሌ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች በዚሁ ዕለት ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫዎችን ያካሂዳሉ።

በ2007 ዓ.ም. በተደረገው አገራዊ ምርጫ በተመረጡ የምክር ቤት አባላት እየተዳደረ ያለው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፤ በክልሉ ምክር ቤት ውስጥ ካለው 99 መቀመጫዎች ውስጥ ከሦስት ዓመት በፊት በተደረገው ምርጫ አዲስ ተወካይ የተተካው በ28ቱ ላይ ብቻ ነው።

በዚህም ምክንያት ከትግራይ ክልል ውጪ ባሉ ክልሎች እና በፌደራል ደረጃ መንግሥት ሲመሠረት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በቀድሞው ምክር ቤት መመራት ቀጥሏል።

ምርጫ ባልተደረገባቸው 71 የክልሉ ምክር ቤት መቀመጫዎች እና አራት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች የሚወከሉ ዕጩዎችን ለመምረጥ ፓርቲዎች ከሚያዝያ 21 እስከ ሰኔ 11 ድረስ ቅስቀሳ እንዲያደርጉ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ አውጥቷል።

ቦዴፓ፤ በቅስቀሳ ሂደቱ ላይ ቅሬታ ያቀረበው “የብልፅግና ፓርቲ የምርጫ ምልክት የሆነው አምፖል እና የብልፅግና ዕጩ ተወዳዳሪዎች ፎቶ በየመንግሥት መሥሪያ ቤቱ እና በሕዝብ ተቋማት ላይ እየተለጠፉ [ነው]” በሚል እንደሆነ በቦርዱ ደብዳቤ ላይ ተጠቅሷል።

የብልፅግና ፓርቲ የምርጫ ምልክት እና ዕጩዎችን የያዙ ማስታወቂዎች “በወረዳ እና በቀበሌ መስተዳደር ቢሮዎች፣ በጤና ተቋማት እና በትምህርት ቤቶች ላይ” መለጠፋቸውን የቦዴፓ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ተሰማ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይህ ድርጊት በተለይም በክልሉ በሚገኘው መተከል ዞን እንደተስተዋለ የሚገልጹት አቶ ዮሐንስ፤ በዞኑ በሚገኙ ሰባት የምርጫ ክልሉሎች “በሙሉ” በሚገኙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በር፣ መስኮት እና ግድግዳ ላይ የብልፅግና ፓርቲ ማስታወቂያዎች በመጥቀስ ከስሰዋል።

ምርጫ ቦርድ በጻፈው ደብዳቤ ላይ እነዚህ ማስታወቂዎች እንዲነሱ የጠየቀው በ2011 ዓ.ም. በወጣው የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ላይ የሚገኙ ሁለት አንቀጾችን በመጥቀስ ነው።

ቦርዱ የጠቀሰው የመጀመሪያው አንቀጽ የምርጫ ውድድር እንቅስቃሴ ስለተከለከለባቸው ቦታዎች የተደነገገበትን የሕግ ክፍል ነው።

አንቀጹ የምረጡኝ ቅስቀሳ ወይም ዘመቻ ማድረግ የተከለከለ እንደሆነ ከጠቀሳቸው ቦታዎች ውስጥ “የመንግሥት ወይም የሕዝብ መደበኛ ሥራ በመከናወን ላይ የሚገኙባቸው የመንግሥት እና የሕዝብ ተቋማት ሥራቸውን በሚያከናውኑበት መደበኛ የሥራ ሰዓት እና ቦታ” የሚለው ይገኝበታል።

በተጨማሪም ስለ ሙስና ተግባር በደነገገው የሕጉ ክፍል ላይ የሚገኝ ንዑስ አንቀፅ በምርጫ ቦርድ ደብዳቤ ላይ ተጠቅሷል።

ይህ ንዑስ አንቀፅ “ማንኛውም የሥራ ኃላፊ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ በሚመራው ወይም በሚሠራበት ተቋም አግባብ ያልሆነ ድጋፍ ወይም እርዳታ በመጠቀም ዕጩ ተወዳዳሪን ማስተዋወቅ ወይም የሌሎች ተወዳዳሪዎችን የማስተዋወቅ ዕድል ማደናቀፍ” እንደሌለበት የደነገገ ነው።

በእነዚህ ሕጎች መሠረት በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ የፓርቲ እና ዕጩ ቅስቀሳ ማድረግ በሕግ የተከለከለ ተግባር መሆኑን በደብዳቤው ላይ ያሰረፈው ቦርዱ፤ “አላግባብ የተለጠፉት የብልፅግና ፓርቲ ምርጫ ምልክት የሆነው አምፖል እና የብልፅግና ዕጩ ተወዳዳሪዎች ፎቶ እንዲነሱ” ሲል ፓርቲውን አሳስቧል።

ቦርዱ ሰኔ 16 ምርጫ በሚያደርግባቸው ሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ እምርጃ እንዲወሰድ ጠይቋል።

ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ከብልፅግና ፓርቲ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ፤ ከከተማ ውጪ በመሆናቸው በአሁኑ ሰዓት ጉዳዩን አጣርተው መናገር እንደማይችሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።